ዕንባቆም 3:16-19
እኔ ሰማሁ፤ ልቤም ደነገጠብኝ፤ ከንፈሬ ከድምፁ የተነሣ ተንቀጠቀጠ፤ ፍርሀት እስከ ዐጥንቴ ዘልቆ ገባ፤ እግሬም ተብረከረከ፤ ሆኖም በሚወርረን ሕዝብ ላይ እስኪመጣ ድረስ፣ የጥፋትን ቀን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ። ምንም እንኳ የበለስ ዛፍ ባያፈራ፣ ከወይን ተክልም ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራም ዛፍ ፍሬ ባይሰጥ፣ ዕርሻዎችም ሰብል ባይሰጡ፣ የበጎች ጕረኖ እንኳ ባዶውን ቢቀር፣ ላሞችም በበረት ውስጥ ባይገኙ፣ እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በድነቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ። ጌታ እግዚአብሔር ኀይሌ ነው፤ እግሮቼን እንደ ዋላ እግሮች ያደርጋል፤ በከፍታዎችም ላይ ያስሄደኛል።
ዕንባቆም 3:16-19