ኤፌሶን 5:3-10
ማንኛውም የዝሙት ወይም የርኩሰት ወይም የሥሥት ነገር ከቶ በመካከላችሁ አይነሣ፤ ይህ ቅዱስ ለሆነው ለእግዚአብሔር ሕዝብ አይገባምና። የሚያሳፍርና ተራ የሆነ ንግግር፣ ዋዛ ፈዛዛም ለእናንተ ስለማይገባ በመካከላችሁ አይኑር፤ ይልቁንስ የምታመሰግኑ ሁኑ። ደግሞም ይህን ዕወቁ፤ ማንም አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም ስግብግብ፣ ይኸውም ጣዖት አምላኪ በክርስቶስና በእግዚአብሔር መንግሥት ርስት የለውም። ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ቍጣ በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣው በእንደዚህ ዐይነት ነገር ነው። ስለዚህ እንዲህ ካሉ ጋር አትተባበሩ። ቀድሞ ጨለማ ነበራችሁ፤ አሁን ግን በጌታ ብርሃን ናችሁ። እንደ ብርሃን ልጆች ኑሩ፤ የብርሃኑ ፍሬ በበጎነት፣ በጽድቅና በእውነት ሁሉ ዘንድ ነውና። እንዲሁም ጌታን ደስ የሚያሰኘውን ፈልጉ።
ኤፌሶን 5:3-10