ቈላስይስ 1:15-23
እርሱ የማይታየው አምላክ አምሳል ነው፤ ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው፤ ሁሉ ነገር በእርሱ ተፈጥሯል፤ በሰማይና በምድር ያሉ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ኀይላት፣ ገዦች ቢሆኑ ወይም ባለሥልጣናት፣ ሁሉም ነገር በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሯል። እርሱ ከሁሉ በፊት ነው፤ ሁሉም ነገር በአንድ ላይ ተያይዞ የጸናው በእርሱ ነው። እርሱ አካሉ የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ነው፤ በሁሉ ነገር የበላይነት ይኖረው ዘንድ እርሱ የመጀመሪያ፣ ከሙታን መካከልም በኵር ነው። እግዚአብሔርም ሙላቱ ሁሉ በእርሱ ይሆን ዘንድ ወድዷልና፤ በመስቀሉ ላይ በፈሰሰው ደሙ ሰላምን በማድረግ በምድርም ሆነ በሰማይ ያለውን ነገር ሁሉ በእርሱ በኩል ከራሱ ጋር አስታረቀ። ከክፉ ባሕርያችሁ የተነሣ ቀድሞ ከእግዚአብሔር የተለያችሁ በዐሳባችሁም ጠላቶች ነበራችሁ። አሁን ግን ነውርና ነቀፋ የሌለባችሁ ቅዱሳን አድርጎ በእርሱ ፊት ሊያቀርባችሁ፣ በክርስቶስ ሥጋ በሞቱ በኩል አስታረቃችሁ፤ ይህም የሚሆነው በእምነታችሁ ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ በመቆም ከሰማችሁት የወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ ጸንታችሁ ብትኖሩ ነው። እናንተ የሰማችሁትና ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ የተሰበከውም ወንጌል ይኸው ነው፤ እኔም ጳውሎስ ለዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆንሁ።
ቈላስይስ 1:15-23