1 ጴጥሮስ 4:7-14
የሁሉ ነገር መጨረሻ ተቃርቧል፤ ስለዚህ መጸለይ እንድትችሉ ንቁ አእምሮ ይኑራችሁ፤ ራሳችሁንም የምትገዙ ሁኑ። ፍቅር ብዙ ኀጢአትን ይሸፍናልና፣ ከሁሉ በላይ እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ያለ ማጕረምረም እንግድነት ተቀባበሉ። እንደ ታማኝ የእግዚአብሔር ልዩ ልዩ ጸጋ መጋቢ እያንዳንዱ ሰው በተቀበለው የጸጋ ስጦታ ሌላውን ያገልግል። ከእናንተ ማንም የሚናገር ቢኖር እንደ እግዚአብሔር ቃል ይናገር፤ የሚያገለግልም ቢኖር እግዚአብሔር በሚሰጠው ብርታት ያገልግል፤ ይኸውም እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት እንዲከብር ነው። ክብርና ኀይል ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን፤ አሜን። ወዳጆች ሆይ፤ እንደ እሳት የሚፈትን ብርቱ መከራ በመቀበላችሁ እንግዳ ነገር እንደ ደረሰባችሁ በመቍጠር አትደነቁ፤ ነገር ግን ክብሩ በሚገለጥበት ጊዜ ደስታችሁ ታላቅ እንዲሆን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች በመሆናችሁ ደስ ይበላችሁ። ስለ ክርስቶስ ስም ብትሰደቡ፣ የክብር መንፈስ የሆነው የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ስለሚያርፍ ብፁዓን ናችሁ።
1 ጴጥሮስ 4:7-14