ቲቶ 1:7-14
ቲቶ 1:7-14 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ኤጲስ ቆጶስ የእግዚአብሔር ሥራ ባለዐደራ እንደ መሆኑ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባል፤ ይኸውም ትምክሕተኛ፣ ግልፍተኛ፣ ሰካራም፣ ጨቅጫቃና ተገቢ ባልሆነ መንገድ ለጥቅም የሚሮጥ ሊሆን አይገባም። ከዚህ ይልቅ እንግዳ ተቀባይ፣ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድድ፣ ራሱን የሚገዛ፣ ቅን፣ ቅዱስና ጠንቃቃ ሊሆን ይገባል። ሌሎችን ትክክል በሆነው ትምህርት እንዲያበረታታና ይህንኑ ትምህርት የሚቃወሙትን ይወቅሥ ዘንድ እንደ ተማረው በታመነ ቃል የሚጸና መሆን አለበት። ዐመፀኞች፣ ለፍላፊዎችና አታላዮች የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ በተለይም እነዚህ ከተገረዙት ወገን ናቸው። እነዚህን ዝም ማሠኘት ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ትክክል ባልሆነ መንገድ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ማስተማር የማይገባቸውን ነገር በማስተማር ቤተ ሰብን ሁሉ በመበከል ላይ ናቸው። ከራሳቸው ነቢያት አንዱ ስለ እነርሱ ሲናገር፣ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፣ ክፉ አውሬዎችና ሰነፍ ሆዳሞች ናቸው” ብሏል። ይህ ምስክርነት እውነት ነው፤ ስለዚህ አጥብቀህ ገሥጻቸው፤ ይኸውም ትክክለኛ እምነት እንዲኖራቸውና የአይሁድን ተረት ወይም ከእውነት የራቁትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳያዳምጡ ነው።
ቲቶ 1:7-14 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ኤጲስ ቆጶስ (የቤተ ክርስቲያን መሪ) የእግዚአብሔርን ሥራ በዐደራ የተቀበለ ስለ ሆነ የማይነቀፍ መሆን አለበት፤ እንዲሁም የማይኰራ፥ በቶሎ የማይቈጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ መሆን አለበት። ይልቅስ እንግዳ ተቀባይ፥ መልካም የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ራሱን የሚቈጣጠር፥ ትክክለኛ፥ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ፥ በመጠን የሚኖር ይሁን። እውነተኛውን ትምህርት በማስተማር ለመምከርና ለተቃዋሚዎችም መልስ ለመስጠት እንዲችል በተማረው መሠረት በአስተማማኝ ቃል ይጽና። ብዙ ሰዎች፥ ይልቁንም ከአይሁድ ወገን የሆኑ የግዝረትን ሥርዓት የሚከተሉ፥ የማይታዘዙ፥ በከንቱ የሚለፈልፉና የሚያታልሉ አሉ። እነዚህን ሰዎች ዝም ማሰኘት ይገባል፤ እነርሱ በሚያሳፍር ትርፍ ለማግኘት የማይገባውን ነገር እያስተማሩ ቤተሰቦችን በሙሉ ያናውጣሉ። ከእነርሱ አንዱ የሆነው የገዛ ራሳቸው ነቢይ “የቀርጤስ ሰዎች ሁልጊዜ ውሸታሞች፥ ክፉ አውሬዎች፥ ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው” ብሎአል። ይህም ምስክርነት እውነት ነው፤ ስለዚህ የተሟላ እምነት እንዲኖራቸው እነዚህን ሰዎች ገሥጻቸው። የአይሁድን ተረት እንዳይከተሉና እውነትን የሚቃወሙትን ሰዎች ትእዛዝ እንዳይሰሙ በብርቱ ገሥጻቸው።
ቲቶ 1:7-14 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ኤጲስቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤ እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል። የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸተኞች፥ ክፉዎች አራዊት፥ በላተኞች፥ ሥራ ፈቶች ናቸው፤” ብሎአል። ይህ ምስክር እውነተኛ ነው። ስለዚህ ምክንያት የአይሁድን ተረትና ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን ሰዎች ትእዛዝ ሳያዳምጡ፥ በሃይማኖት ጤናሞች እንዲሆኑ በብርቱ ውቀሳቸው።
ቲቶ 1:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ኤጲስቆጶስ፥ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ፥ የማይነቀፍ ሊሆን ይገባዋልና፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፥ ነውረኛ ረብ የማይወድ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚገዛ ይሁን፤ ሕይወት በሚገኝበት ትምህርት ደግሞ ሊመክር ተቃዋሚዎቹንም ሊወቅስ ይችል ዘንድ፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። የማይታዘዙና ከንቱ የሚናገሩ የሚያታልሉ ይልቁንም ከተገረዙት ወገን የሚሆኑ ብዙ ናቸውና፤ እነዚህም ስለ ነውረኛ ረብ የማይገባውን እያስተማሩ ቤቶችን በሞላው ስለ ሚገለብጡ፥ አፋቸውን መዝጋት ይገባል። የገዛ ራሳቸው ነቢይ የሆነ ከእነርሱ አንዱ፦ የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸተኞች፥ ክፉዎች አራዊት፥ በላተኞች፥ ሥራ ፈቶች ናቸው ብሎአል። ይህ ምስክር እውነተኛ ነው። ስለዚህ ምክንያት የአይሁድን ተረትና ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን ሰዎች ትእዛዝ ሳያዳምጡ፥ በሃይማኖት ጤናሞች እንዲሆኑ በብርቱ ውቀሳቸው።
ቲቶ 1:7-14 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ኤጲስ ቆጶስ እንደ እግዚአብሔር መጋቢ ነቀፋ የሌለበት ሊሆን ይገባዋል፤ የማይኮራ፥ የማይቆጣ፥ የማይሰክር፥ ጠበኛ ያልሆነ፥ ለገንዘብ የማይስገበገብ፥ ነገር ግን እንግዳ ተቀባይ፥ በጎ የሆነውን ነገር የሚወድ፥ ጠንቃቃ፥ ጻድቅ፥ ቅዱስ፥ ራሱን የሚቈጣጠር ይሁን፤ እውነተኛውንም ትምህርት ለመምከርና ተቃዋሚዎቹን ለመገሠጽ እንዲችል፥ እንደተማረው በታመነ ቃል ይጽና። የማይታዘዙና ከንቱ ነገርን የሚያወሩ የሚያታልሉ በተለይም ከተገረዙት ወገን የሆኑ ብዙ ሰዎች አሉና፤ እነዚህም ማስተማር የማይገባቸውን በማጭበርበር የሚገኘውን ጥቅም እያስተማሩ ቤተሰቦችን በሞላ አውከዋልና፥ እነርሱን ዝም ማሰኘት ይገባል። ከእነርሱ አንዱ የሆነው የገዛ ራሳቸው ነቢይ፦ “የቀርጤስ ሰዎች ዘወትር ውሸታሞች፥ ክፉ አውሬዎች፥ ሥራ ፈት ሆዳሞች ናቸው፤” ብሏል። ይህ ምስክርነት እውነት ነው። በዚህም ምክንያት እነርሱን አጥብቀህ ገሥጽ፤ ይህን የምታደርገው በእምነት ረገድ እንዲጸኑና በአይሁድ ተረቶችና እውነትን በማይቀበሉ በሰዎች ትእዛዛት እንዳይጠመዱ ነው።