ሩት 3:1-11

ሩት 3:1-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አማትዋም ኑኃሚን አለቻት፦ ልጄ ሆይ፥ መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። እንግዲህ ታጠቢ፥ ተቀቢ፥ ልብስሽን ተላበሺ፥ ወደ አውድማውም ውረጂ፣ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። በተኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፥ ተጋደሚም፣ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል። ሩትም፦ የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ አለቻት። ወደ አውድማውም ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፣ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፣ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። እርሱም፦ ማን ነሽ? አለ። እርስዋም፦ እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፣ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ አለችው። ቦዔዝም አላት፦ ልጄ ሆይ፥ በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፣ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ፥ አትፍሪ፣ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።

ሩት 3:1-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ከዚህ በኋላ ዐማቷ ኑኃሚን ሩትን እንዲህ አለቻት፤ “ልጄ ሆይ፤ የሚመችሽን ቤት እንድፈልግልሽ አይገባኝምን? ከሴቶች ሠራተኞቹ ጋራ ዐብረሽ የነበርሽበት ቦዔዝ፣ ዘመዳችን አይደለምን? ዛሬ ማታ በዐውድማው ላይ ገብስ ያበራያል፤ ተጣጠቢ፤ ሽቱ ተቀቢ፤ እንዲሁም የክት ልብስሽን ልበሺ፤ ከዚያም ወደ ዐውድማው ውረጂ፤ ይሁን እንጂ በልቶና ጠጥቶ እስኪያበቃ ድረስ፣ እዚያ መሆንሽን እንዳያውቅ ይሁን። በተኛም ጊዜ፣ የሚተኛበትን ቦታ ልብ ብለሽ እዪና ሄደሽ እግሩን ገልጠሽ ተኚ፤ ከዚያም የምታደርጊውን ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም፣ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ተነሥታ ወደ ዐውድማው ወረደች፤ ዐማቷ አድርጊ ያለቻትንም ሁሉ አደረገች። ቦዔዝ በልቶ ጠጥቶ ከጨረሰና ደስም ከተሠኘ በኋላ፣ ራቅ ካለው የእህል ክምር አጠገብ ለመተኛት ሄደ። ሩት በቀስታ ከአጠገቡ ደረሰች፤ እግሩንም ገልጣ ተኛች። እኩለ ሌሊት ላይ ሰውየውን አንዳች ነገር አስደነገጠው፤ ገልበጥ ሲልም አንዲት ሴት እግርጌው ተኝታ አገኘ። እርሱም፣ “አንቺ ማነሽ?” ሲል ጠየቀ። እርሷም፣ “እኔ አገልጋይህ ሩት ነኝ፤ መቤዠት የሚገባህ ቅርብ የሥጋ ዘመድ አንተ ነህና ልብስህን ጣል አድርግብኝ” አለችው። እርሱም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ፤ እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ ከዚህ በፊት ካደረግሽው ይልቅ ያሁኑ በጎነትሽ ይበልጣል፤ ባለጠጋም ሆነ ድኻ፣ ወጣት ወንድ ፈልገሽ አልሄድሽምና። አሁንም ልጄ ሆይ፤ አትፍሪ፤ የምትጠይቂውን ሁሉ አደርግልሻለሁ፤ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት መሆንሽንም የአገሬ ሰው ሁሉ ያውቀዋል።

ሩት 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አማትዋም ኑኃሚን አለቻት “ልጄ ሆይ! መልካም እንዲሆንልሽ ዕረፍት አልፈልግልሽምን? አሁንም ከገረዶቹ ጋር የነበርሽበት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ትበትናል። እንግዲህ ታጠቢ፤ ተቀቢ፤ ልብስሽን ተላበሺ፤ ወደ አውድማውም ውረጂ፤ ነገር ግን መብሉንና መጠጡን እስኪጨርስ ድረስ ለሰውዮው አትታዪው። በትኛም ጊዜ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፤ ገብተሽም እግሩን ግለጪ፤ ተጋደሚም፤ የምታደርጊውንም እርሱ ይነግርሻል።” ሩትም “የተናገርሽኝን ሁሉ አደርጋለሁ፤” አለቻት። ወደ አውድማውም ወረደች፤ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፤ ሩትም በቀስታ መጣች፤ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፤ ዘወርም አለ፤ እነሆም፥ አንዲት ሴት በእግርጌው ተኝታ ነበረች። እርሱም “ማን ነሽ?” አለ። እርስዋም “እኔ ባሪያህ ሩት ነኝ፤ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባሪያህ ላይ ዘርጋ፤” አለችው። ቦዔዝም አላት “ልጄ ሆይ! በእግዚአብሔር የተባረክሽ ሁኚ፤ ባለጠጋም ድሀም ብለሽ ጐበዛዝትን አልተከተልሽምና ከፊተኛው ይልቅ በመጨረሻው ጊዜ ቸርነት አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ በአገሬ ያሉ ሕዝብ ሁሉ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።

ሩት 3:1-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አማትዋ ናዖሚ ሩትን እንዲህ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ የቅርብ ዘመዳችን ነው፤ እነሆ! እርሱ ዛሬ ማታ ገብስ ይወቃል፤ ስለዚህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፤ የክት ልብስሽንም ልበሺ፤ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። የት እንደሚተኛ ካረጋገጥሽ በኋላ፥ እንቅልፍ ሲወስደው ወደ እርሱ ቀረብ በዪና ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ሩት ወደ አውድማው ሄዳ ልክ ዐማትዋ እንደ ነገረቻት አደረገች። ቦዔዝ ከበላና ከጠጣ በኋላ ደስ ብሎት ነበር፤ ወደ ገብሱም ክምር ሄዶ ጋደም አለና አንቀላፋ፤ ሩትም በቀስታ ወደ እርሱ ተጠጋች፤ ልብሱንም ገለጥ አድርጋ በእግሩ አጠገብ ተኛች። ወደ እኩለ ሌሊት ገደማም ቦዔዝ ድንገት ነቅቶ ሲገላበጥ አንዲት ሴት በግርጌ ተኝታ በማግኘቱ ተደነቀ፤ “አንቺ ማን ነሽ?” ብሎም ጠየቃት። እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! አገልጋይህ እኔ ሩት ነኝ፤ አንተ የቅርብ ዘመድ ስለ ሆንክ ለእኔ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት አለብህ፤ ስለዚህ ልብስህን ባገልጋይህ ላይ ጣል አለችው።” ቦዔዝም እንዲህ አላት፤ “ልጄ ሆይ! እግዚአብሔር ይባርክሽ፤ አሁን በምታደርጊው ነገር ከዚህ በፊት ለዐማትሽ ካደረግሽው የሚበልጥ ታማኝነት አሳይተሻል፤ ብትፈልጊ ኖሮ ወደ ሀብታም ወይም ወደ ድኻ ወጣት መሄድ ትችይ ነበር፤ ነገር ግን ይህን ማድረግ አልፈለግሽም፤ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ ከእንግዲህ ወዲህ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ መልካም ሴት መሆንሽን ያውቃሉ፤ የምትፈልጊውን ሁሉ አደርግልሻለሁ።

ሩት 3:1-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አማቷም ናዖሚ አለቻት፦ “ልጄ ሆይ! መልካም ይሆንልሽ ዘንድ የተመቻቸ ኑሮ የምትኖሪበትን ሁናቴ ልፈልግልሽ ይገባል። አሁንም ስትቃርሚ አብረውሽ የነበሩት ሴቶች የሚያገለግሉት ቦዔዝ ዘመዳችን አይደለምን? እነሆ፥ እርሱ በዛሬ ሌሊት በአውድማው ላይ ገብሱን በመንሽ ይበትናል። እንግዲህ ሰውነትሽን ታጠቢና ሽቶ ተቀቢ፥ የክት ልብስሽንም ልበሺ፥ ከዚህ በኋላ እርሱ ገብሱን ወደሚወቃበት አውድማ ሂጂ፤ ነገር ግን እስከሚበላና እስከሚጠጣ ድረስ በፊቱ አትታዪ። በሚተኛም ጊዜ፥ የሚተኛበትን ስፍራ ተመልከቺ፥ ገብተሽም ከግርጌው በኩል ልብሱን ገልጠሽ በእግሩ አጠገብ ተኚ፤ ምን ማድረግ እንደሚገባሽ እርሱ ራሱ ይነግርሻል።” ሩትም፦ “ያልሽውን ሁሉ አደርጋለሁ” አለቻት። ስለዚህ ወደ አውድማው ወረደች፥ አማትዋም ያዘዘቻትን ሁሉ አደረገች። ቦዔዝም ከበላና ከጠጣ ሰውነቱንም ደስ ካሰኘ በኋላ፥ በእህሉ ክምር አጠገብ ሊተኛ ሄደ፥ ሩትም በቀስታ መጣች፥ እግሩንም ገልጣ ተኛች። መንፈቀ ሌሊትም በሆነ ጊዜ ሰውዮው ደነገጠ፥ ዘወርም አለ፥ እነሆም፥ አንዲት ሴት በግርጌው ተኝታ ነበር። እርሱም፦ “ማን ነሽ?” አለ። እርሷም፦ “እኔ ባርያህ ሩት ነኝ፥ ዋርሳዬ ነህና ልብስህን በባርያህ ላይ ጣል አለችው።” ቦዔዝም አላት፦ “ልጄ ሆይ፥ በጌታ የተባረክሽ ሁኚ፥ ባለ ጠጋ ይሁን ወይም ድሀ፥ ወጣቶችን መርጠሽ መሄድ አልፈለግሽምና ከፊተኛው ይልቅ አሁን ባደረግሽው ታማኝነትን አድርገሻል። አሁንም፥ ልጄ ሆይ! አትፍሪ፤ በከተማው ያሉ ሰዎች ሁሉ አንቺ ምግባረ መልካም ሴት እንደ ሆንሽ ያውቃሉና ያልሽውን ነገር ሁሉ አደርግልሻለሁ።