የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሩት 2:1-21

ሩት 2:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ለኑኃሚንም ባል የሚዛመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን፦ በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ አለቻት። እርስዋም፦ ልጄ ሆይ፥ ሂጂ አለቻት። ሄደችም፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፣ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን አላቸው። እነርሱም፦ እግዚአብሔር ይባርክህ ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን፦ ይህች ቆንጆ የማን ናት? አለው። የአጫጆቹም አዛዥ፦ ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፣ እርስዋም፦ ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ አለች፣ መጣችም፥ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፣ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም አለው። ቦዔዝም ሩትን፦ ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ። ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፣ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፣ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ አላት። በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት፦ እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን? አለችው። ቦዔዝም፦ ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፣ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን አላት። እርስዋም፦ ጌታዬ ሆይ፥ ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኽኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ አለችው። በምሳም ጊዜ ቦዔዝ፦ ወደዚህ ቅረቢ፣ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ አተረፈችም። ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን፦ በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አታሳፍሩአት፣ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፣ እርስዋም ትቃርም፥ አትውቀሱአትም ብሎ አዘዛቸው። በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፣ የቃረመችውንም ወቃችው፣ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ። ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፣ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። አማትዋም፦ ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን አለቻት። እርስዋም፦ ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት። ኑኃሚንም ምራትዋን፦ ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ፦ ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው አለቻት። ሞዓባዊቱ ሩትም፦ ደግሞ፦ መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ አለኝ አለቻት።

ሩት 2:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ኑኃሚን፣ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነ ቦዔዝ የሚባል ባለ ጸጋ የባል ዘመድ ነበራት። ሞዓባዊቷ ሩትም ኑኃሚንን፣ “በፊቱ ሞገስ አግኝቼ ቃርሚያ የሚያስቃርመኝ ሰው ባገኝ እስቲ ወደ እህል አዝመራው ልሂድ” አለቻት። ኑኃሚንም፣ “ልጄ ሆይ፤ ይሁን ሂጂ” አለቻት። ስለዚህ እርሷም ወጣች፤ ከዐጫጆች ኋላ ኋላ እየተከታተለችም ከአዝመራው ቦታ ትቃርም ጀመር፤ እንዳጋጣሚ ትቃርምበት የነበረው አዝመራ ከአቤሜሌክ ጐሣ የሆነው የቦዔዝ ነበር። በዚሁ ጊዜ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ ዐጫጆቹንም፣ “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” ብሎ ሰላምታ ሰጣቸው። እነርሱም፣ “እግዚአብሔር ይባርክህ!” ብለው መለሱለት። ከዚያም ቦዔዝ የዐጫጆቹን አለቃ፣ “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” ሲል ጠየቀው። የዐጫጆቹም አለቃ እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ከኑኃሚን ጋር ከሞዓብ ምድር ተመልሳ የመጣች ሞዓባዊት ናት። እርሷም፣ ‘ዐጫጆቹን እየተከተልሁ በነዶው መካከል እንድቃርም እባክህ ፍቀድልኝ’ አለችኝ። ለጥቂት ጊዜ በመጠለያው ከማረፏ በስተቀር፣ ወደ አዝመራው ቦታ ገብታ ከጧት አንሥቶ እስካሁን ያለ ማቋረጥ ስትቃርም ቈይታለች።” ስለዚህም ቦዔዝ ሩትን፣ “ልጄ ሆይ ስሚኝ፤ ከእንግዲህ ወደ ሌላ አዝመራ ሄደሽ አትቃርሚ፤ ከዚህም አትራቂ፤ ከሴቶች ልጆቼ ጋር እዚሁ ሁኚ። ወንዶቹ የሚያጭዱበትን ዕርሻ ልብ እያልሽ ልጃገረዶቹን ተከተዪ፤ ወንዶቹ እንዳያስቸግሩሽም አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃ ሲጠማሽ ደግሞ፣ እየሄድሽ ወንዶቹ ሞልተው ካስቀመጡት እንስራ ቀድተሽ ጠጪ።” በዚህ ጊዜ ወደ መሬት ዝቅ ብላ እጅ ነሣችው። እርሷም፣ “ባይተዋር የሆንሁትን እኔን ታስበኝ ዘንድ በፊትህ ሞገስ ለማግኘት የበቃሁት እንዴት ነው?” አለችው። ቦዔዝም መልሶ እንዲህ አላት፤ “ባልሽ ከሞተ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን ሁሉ፣ አባት እናትሽን እንዲሁም የተወለድሽበትን አገር ትተሽ ቀድሞ ከማታውቂው ሕዝብ ጋር ለመኖር እንዴት እንደ መጣሽ ነግረውኛል። ስላደረግሽው ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋሽን ይክፈልሽ፤ በክንፉ ጥላ ሥር ለመጠለል የመጣሽበት የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ብድራትሽን አትረፍርፎ ይመልስልሽ።” እርሷም መልሳ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ ምንም እንኳ፣ ከሴት ሠራተኞችህ እንደ አንዲቱ መቈጠር የማይገባኝ ብሆንም፣ እንድጽናና አድርገኸኛል፤ እንዲሁም እኔን አገልጋይህን በመልካም ንግግር ደስ አሰኝተኸኛል፤ ስለዚህ ሞገስህ እንዳይለየኝ እለምንሃለሁ” አለችው። በምሳ ሰዓት ቦዔዝ፣ “ወደዚህ ቀረብ በዪ፤ እንጀራም ወስደሽ በወይን ሆምጣጤው አጥቅሽ” አላት። እርሷም ከዐጫጆች አጠገብ እንደ ተቀመጠች፣ ቦዔዝ የተጠበሰ እሸት ሰጣት፤ የቻለችውንም ያህል በልታ ጥቂት ተረፋት። ለመቃረም ስትነሣም፣ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን እንዲህ ብሎ አዘዛቸው፤ “በነዶው መካከል እንኳ ብትቃርም ክፉ አትናገሯት፤ ይልቁንም ከየታሰረው ነዶ ላይ ጥቂት ጥቂቱን ዘለላ እየመዘዛችሁ በመጣል እንድታነሣው ተዉላት፤ አታስቀይሟት።” ስለዚህ ሩት እስኪመሽ ድረስ ከአዝመራው ላይ ቃረመች፤ ከዚያም የሰበሰበችውን ገብስ ወቃች፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያም ያህል ሆነ። ያንንም ይዛ ወደ ከተማ ሄደች፤ ዐማቷም የሰበሰበችው ምን ያህል እንደ ሆነም አየች፤ እንዲሁም ሩት የሚበቃትን ያህል ከበላች በኋላ አስተርፋ የነበረውን አውጥታ ለእርሷ ሰጠቻት። ዐማቷም፣ “ዛሬ የቃረምሽው ከየት ነው? የትስ ቦታ ስትሠሪ ዋልሽ? መልካም ነገር ያደረገልሽ ሰው የተባረከ ይሁን” አለቻት። ከዚያም ሩት ስትሠራ ስለ ዋለችበት ስፍራ ባለቤት ለዐማቷ ነገረቻት፤ እርሷም፣ “ዛሬ ስቃርም የዋልሁበት አዝመራ ባለቤት፣ ስሙ ቦዔዝ ይባላል” አለቻት። ኑኃሚንም ምራቷን፣ “በጎነቱን ለሕያዋንም ሆነ ለሙታን ማድረጉን ያልተወ እግዚአብሔር ይባርከው” አለቻት፤ ቀጥላም፣ “ሰውየው እኮ የሥጋ ዘመዳችን ነው፤ የመቤዠት ግዴታ ካለባቸው ዘመዶቻችን አንዱ እርሱ ነው” አለቻት። ከዚያም ሞዓባዊቷ ሩት፣ “ደግሞም፣ ‘እህሌን ሁሉ ዐጭደው እስኪጨርሱ ድረስ ከሠራተኞቼ አትለዪ!’ ብሎኛል” አለቻት።

ሩት 2:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ለኑኃሚንም ባል የሚዘመደው ከአቤሜሌክ ወገን የሆነ ኃያል ሰው ስሙ ቦዔዝ የተባለ ሰው ነበረ። ሞዓባዊቱም ሩት ኑኃሚንን “በፊቱ ሞገስ የማገኘውን ተከትዬ እህል እንድቃርም ወደ እርሻ ልሂድ፤” አለቻት። እርስዋም “ልጄ ሆይ! ሂጂ፤” አለቻት። ሄደችም፤ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፤ እንደ አጋጣሚውም የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። እነሆም፥ ቦዔዝ ከቤተ ልሔም መጣ፤ አጫጆችንም “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን፤” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር ይባርክህ፤” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን ሎሌውን “ይህች ወጣት ሴት የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከኑኃሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ቆንጆ ናት፤ እርስዋም ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም እባክህ ፍቀድልኝ’ አለች፤ መጣችም፤ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ድረስ ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም፤” አለው። ቦዔዝም ሩትን “ልጄ ሆይ! ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፤ ከዚህም አትላወሺ፤ ነገር ግን ገረዶቼን ተጠጊ። ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፤ ተከተያቸውም፤ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፤ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውሃ ጠጪ፤” አላት። በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት “እኔንስ ለመቀበል በምን ነገር በፊትህ ሞገስ አገኘሁ? እኔ እንግዳ አይደለሁምን?” አለችው። ቦዔዝም “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። እግዚአብሔር እንደ ሥራሽ ይስጥሽ፤ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ዘንድ ደመወዝሽ ፍጹም ይሁን፤” አላት። እርስዋም “ጌታዬ ሆይ! ከባሪያዎችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባሪያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዐይንህ ሞገስ ላግኝ፤” አለችው። በምሳም ጊዜ ቦዔዝ “ወደዚህ ቅረቢ፤ ምሳ በዪ፤ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሽ፤” አላት። በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች፤ የተጠበሰም እሸት ሰጣት፤ በልታም ጠገበች፤ አተረፈችም። ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ጐበዛዝቱን “በነዶው መካከል ትቃርም፤ እናንተም አታሳፍሩአት፤ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፤ እርስዋም ትቃርም፤ አትውቀሱአትም፤” ብሎ አዘዛቸው። በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፤ የቃረመችውንም ወቃችው፤ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ያህልም ገብስ ሆነ። ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፤ አማትዋም የቃረመችውን አየች፤ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። አማትዋም “ዛሬ ወዴት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን፤” አለቻት። እርስዋም “ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል፤” ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማትዋ ነገረቻት። ኑኃሚንም ምራትዋን “ቸርነቱን በሕያዋንና በሙታን ላይ አልተወምና በእግዚአብሔር የተባረከ ይሁን፤” አለቻት። ኑኃሚንም ደግሞ “ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፤ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው፤” አለቻት። ሞዓባዊቱ ሩትም “ደግሞ ‘መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ፤’ አለኝ፤” አለቻት።

ሩት 2:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ለናዖሚም ሀብታምና ታዋቂ የሆነ ቦዔዝ የሚባል የባልዋ የአቤሜሌክ የቅርብ ዘመድ ነበራት፤ አንድ ቀን ሞአባዊትዋ ሩት ናዖሚን “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው እርሻ ሄጄ ቃርሚያ ልቃርም” አለቻት። ናዖሚም “ልጄ ሆይ! ሂጂ!” አለቻት። ሩትም ወደ እርሻዎች ሄደች፤ ከአጫጆች ኋላ እየተከተለችም ከእጃቸው የወዳደቀውን ዛላ ትቃርም ጀመር፤ እንደ አጋጣሚ የምትቃርምበት ቦታ የአቤሜሌክ ዘመድ የሆነው የቦዔዝ እርሻ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ቦዔዝ ራሱ ከቤተልሔም ተነሥቶ ወደ እርሻው መጣ፤ አጫጆቹንም “እንደምን ዋላችሁ! እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን!” አላቸው። እነርሱም “እግዚአብሔር አንተንም ይባርክህ!” አሉት። ከዚህ በኋላ ቦዔዝ የአጫጆቹ ኀላፊ የሆነውን ሰው “ያቺ ወጣት ሴት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው። ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “እርስዋ ናዖሚን ተከትላ ከሞአብ አገር የመጣች ሞአባዊት ናት፤ አጫጆችን ተከትላ ከነዶ መካከል የወዳደቀውን ዛላ ለመቃረም እንድፈቅድላት ጠየቀችኝ፤ ከጧት ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ነበር፤ አሁን ግን ትንሽ ዕረፍት ለማድረግ ወደ ዳስ ተጠግታለች።” በዚህ ጊዜ ቦዔዝ ሩትን እንዲህ አላት፦ “ልጄ ሆይ! ስሚ እዚህ ያሉትን ሴቶች ሠራተኞችን ተከትለሽ ቃርሚ እንጂ ይህን እርሻ ትተሽ ለመቃረም ወደ ሌላ ቦታ አትሂጂ። እነርሱ የት እንደሚያጭዱ በመጠባበቅ እየተመለከትሽ ከእነርሱ ጋር ሁኚ፤ ወንዶች ሠራተኞቼን እንዳያስቸግሩሽ አስጠንቅቄአቸዋለሁ፤ ውሃም በሚጠማሽ ጊዜ እነርሱ ሞልተው ወዳስቀመጡአቸው እንስራዎች እየሄድሽ ቀድተሽ ጠጪ።” እርስዋም ግንባርዋ መሬት እስኪነካ ድረስ እጅ ነሥታ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ እንዴት በፊትህ ሞገስ ላገኝ ቻልኩ?” አለችው። ቦዔዝም እንዲህ ሲል መለሰላት፦ “ባልሽ ከሞተበት ጊዜ ጀምሮ ለዐማትሽ ያደረግሽላትን መልካም ነገር ሁሉ፥ እንዲሁም አባትሽንና እናትሽን፥ የትውልድ አገርሽንም ትተሽ ከዚህ በፊት በማታውቂው ሕዝብ መካከል ለመኖር ወደዚህ እንደ መጣሽ ሰምቼአለሁ። እግዚአብሔር ላደረግሽው በጎ ነገር ዋጋሽን ይክፈልሽ! የእርሱን ጥበቃ ተማምነሽ የመጣሽው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ዋጋሽን የተትረፈረፈ ያድርገው!” ሩትም “ጌታዬ ሆይ! ምንም እንኳ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ባልሆን እኔን አገልጋይህን በመልካም ቃላት አጽናንተኸኛል፤ ይህ በፊትህ ያገኘሁት ሞገስ እንዲቀጥል ፍቀድልኝ!” አለችው። በምሳ ሰዓት ቦዔዝ ሩትን “ነይ ወደ ገበታው ቅረቢ፤ በወጡም እያጠቀስሽ እንጀራ ብዪ” አላት። እርስዋም ከአጫጆቹ ጋር ተቀመጠች፤ ቦዔዝም የተጠበሰ እሸት ሰጣት፤ እስክትጠግብ ድረስ በላች፤ ምግብም ተርፏት ነበር። እንደገናም ልትቃርም ስትነሣ ቦዔዝ ጐልማሶቹን እንዲህ አላቸው፦ “በነዶዎች መካከል ያለውንም እንኳ ቢሆን ትቃርም፤ እናንተም አትከልክሉአት፤ እንዲያውም ከታሰረው ነዶ እየመዘዛችሁ ተዉላትና ትቃርም፤ አትቈጣጠሩአት።” ሩትም እስከ ምሽት ድረስ ከእርሻው እህል ስትቃርም ዋለች፤ ባሸችውም ጊዜ ዐሥር ኪሎ ያኽል ሆነ። እህሉንም ተሸክማ ወደ ከተማ ተመለሰች፤ ምን ያኽል እንደ ሰበሰበችም ለዐማትዋ አሳየቻት፤ ከምሳዋ ተርፎአት የነበረውንም ምግብ ሰጠቻት። ዐማትዋ “ዛሬ ከየት ቃረምሽ? ወደየትስ ሠራሽ? ይህን መልካም አቀባበል ያደረገልሽን ሰው እግዚአብሔር ይባርከው!” አለቻት። ሩትም “እኔ ስቃርም የዋልኩበት እርሻ ባለቤት ቦዔዝ የሚባል ሰው ነው” ብላ ለናዖሚ ነገረቻት። ናዖሚም “ለሕያዋንና ለሙታን የሰጠውን ተስፋ የሚፈጽም አምላክ ቦዔዝን ይባርከው!” አለች፤ ቀጥላም “ያ ሰው እኮ የቅርብ ዘመዳችን ነው! እንዲያውም ለእኛ ኑሮ የማሰብ ኀላፊነት ካለባቸው ሰዎች አንዱ እርሱ ነው” አለች። ደግሞም ሩት “መከሩን ሰብስበው እስከሚጨርሱ ድረስ ከአጫጆቹ ተጠግተሽ ቈዪ አለኝ” አለቻት።

ሩት 2:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ለናዖሚም በባልዋ የሚዛመዳት ሰው ከኤሊሜሌክ ወገን የሆነ ስሙ ቦዔዝ የተባለ ኃያል ሰው ነበረ። ሞአባዊቱም ሩት ናዖሚንን፦ “በፊቱ ሞገስ ወደማገኝበት ሰው ተከትዬ እህል ለመቃረም ወደ እርሻ ልሂድ” አለቻት። እርሷም፦ “ልጄ ሆይ፥ ሂጂ” አለቻት። ስለዚህም ሄደች፥ ከአጫጆችም በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች፥ እንደ አጋጣሚም የኤሊሜሌክ ወገን ወደነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደረሰች። ከጥቂት ጊዜ በኋላም፥ ቦዔዝ ከቤተልሔም መጣ፥ አጫጆችንም፦ “ጌታ ከእናንተ ጋር ይሁን” አላቸው። እነርሱም፦ “ጌታ ይባርክህ” ብለው መለሱለት። ቦዔዝም በአጫጆች ላይ አዛዥ የነበረውን አገልጋዩን፦ “ይህች ብላቴና የማን ናት?” አለው። የአጫጆቹም አዛዥ፦ “ይህችማ ከሞዓብ ምድር ከናዖሚን ጋር የመጣች ሞዓባዊቱ ብላቴና ናት፥” ብሎ መለሰ። “እርሷም፦ ‘ከአጫጆቹ በኋላ በነዶው መካከል እንድቃርምና እንድለቅም፥ እባክህ፥ ፍቀድልኝ’ ብላ፥ መጣች፤ ከማለዳም ጀምራ እስከ አሁን ስትቃርም ቆይታለች፤ በቤትም ጥቂት ጊዜ እንኳ አላረፈችም” አለው። ቦዔዝም ሩትን፦ “ልጄ ሆይ፥ ትሰሚያለሽን? ቃርሚያ ለመቃረም ወደ ሌላ እርሻ አትሂጂ፥ ከዚህም አትላወሺ፥ ነገር ግን አገልጋዮቼን ተከትለሽ ቃርሚ። ወደሚያጭዱበትም ስፍራ ተመልከቺ፥ ተከተያቸውም፥ እንዳያስቸግሩሽም ጐበዛዝቱን አዝዣለሁ፥ በተጠማሽም ጊዜ ወደ ማድጋው ሄደሽ ጐበዛዝቱ ከቀዱት ውኃ ጠጪ” አላት። በግምባርዋም ተደፍታ በምድር ላይ ሰገደችለት፦ “እኔ ባዕድ ሆኜ ሳለሁ፥ ስለ እኔ ታስብ ዘንድ፥ እንዴት በፊትህ ሞገስ አገኘሁ?” አለችው። ቦዔዝም፦ “ባልሽ ከሞተ በኋላ አባትሽንና እናትሽን የተወለድሽባትንም ምድር ትተሽ ቀድሞ ወደማታውቂው ሕዝብ እንደ መጣሽ፥ ለአማትሽ ያደረግሽውን ነገር ሁሉ ፈጽሞ ሰምቻለሁ። ለሠራሽው ሥራ ጌታ ይክፈልሽ፥ ከክንፉም በታች መጠጊያ እንድታገኚ በመጣሽበት በእስራኤል አምላክ በጌታ ዘንድ ዋጋሽ ፍጹም ይሁን” አላት። እርሷም፦ “ጌታዬ ሆይ፥ ከአገልጋዮችህ እንደ አንዲቱ ሳልሆን አጽናንተኸኛልና፥ የባርያህንም ልብ ደስ አሰኝተሃልና በዓይንህ ሞገስ ላግኝ” አለችው። በምሳ ሰዓትም ቦዔዝ፦ “ወደዚህ ቅረቢ፥ ምሳ ብዪ፥ እንጀራሽንም በሆምጣጤው አጥቅሺ አላት።” በአጫጆቹም አጠገብ ተቀመጠች የተጠበሰም እሸት ሰጣት፥ በልታም ጠገበች፥ ተረፋትም። ደግሞም ልትቃርም በተነሣች ጊዜ ቦዔዝ ብላቴኖቹን፦ “በነዶው መካከል ትቃርም፥ እናንተም አትከልክሏት፥ ደግሞ ከነዶው አስቀርታችሁ ተዉላት፥ እርሷም ትቃርም፤ አትከልክሉአትም” ብሎ አዘዛቸው። በእርሻውም ውስጥ እስከ ማታ ድረስ ቃረመች፥ የቃረመችውንም ወቃችው፥ ዐሥር ኪሎ ያህልም ገብስ ሆነ። ተሸክማውም ወደ ከተማ ገባች፥ አማትዋም የቃረመችውን አየች፥ ከጠገበችም በኋላ የተረፋትን አውጥታ ሰጠቻት። አማትዋም፦ “ዛሬ ከየት ቃረምሽ? ወዴትስ ሠራሽ? የተቀበለሽ የተባረከ ይሁን” አለቻት። እርሷም፦ “ዛሬ የሠራሁበት ሰው ስም ቦዔዝ ይባላል” ብላ በማን ዘንድ እንደ ሠራች ለአማቷ ነገረቻት። ናዖሚም ምራትዋን፦ “በሕያዋን እና በሙታን ላይ ቸርነቱ የማያልቅበት ጌታ የተባረከ ይሁን” አለቻት። ናዖሚም ደግሞ፦ “ይህ ሰው የቅርብ ዘመዳችን ነው፥ እርሱም ሊቤዡን ከሚችሉት አንዱ ነው” አለቻት። ሞዓባዊቱ ሩትም፦ “ደግሞ፥ መከሬን እስኪጨርሱ ድረስ ጐበዛዝቴን ተጠጊ፥ አለኝ” አለቻት።