ሮሜ 9:14-18
ሮሜ 9:14-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያደላልን? አያደላም። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፥ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ይቅር የምለውንም ይቅር እለዋለሁ።” አሁንም ለሮጠና ለቀደመ አይደለም፤ እግዚአብሔር ይቅር ላለው ነው እንጂ። እግዚአብሔርም ለፈርዖን በመጽሐፍ እንዲህ አለው፥ “ኀይሌን በአንተ ላይ እገልጥ ዘንድ፥ ስሜም በምድር ሁሉ ይሰማ ዘንድ ስለዚህ አስነሣሁህ።” እነሆ፥ የሚወድደውን ይምረዋል፤ የሚወድደውንም ልቡን ያጸናዋል።
ሮሜ 9:14-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር አድልዎ ያደርጋልን? በፍጹም አያደርግም! ለሙሴ፣ “የምምረውን እምረዋለሁ፤ ለምራራለትም እራራለታለሁ” ይላልና። እንግዲህ ይህ ከሰው ፍላጎት ወይም ጥረት ሳይሆን፣ ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። መጽሐፍ ፈርዖንን፣ “ኀይሌ በአንተ እንዲታይ፣ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና። ስለዚህ እግዚአብሔር ሊምረው ለሚወድደው ምሕረት ያደርግለታል፤ ልቡ እንዲደነድን የፈለገውንም ያደነድነዋል።
ሮሜ 9:14-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ምን እንላለን? በእግዚአብሔር ዘንድ ዓመፃ አለ ወይ? አይደለም። ለሙሴ፦ የምምረውን ሁሉ እምረዋለሁ ለምራራለትም ሁሉ እራራለታለሁ ይላልና። እንግዲህ ምሕረት ለወደደ ወይም ለሮጠ አይደለም፥ ከሚምር ከእግዚአብሔር ነው እንጂ። መጽሐፍ ፈርዖንን፦ ኃይሌን በአንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አስነሣሁህ ይላልና። እንግዲህ የሚወደውን ይምረዋል፥ የሚወደውንም እልከኛ ያደርገዋል።
ሮሜ 9:14-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለት እንችላለን? እግዚአብሔር ያዳላል ማለትስ ከቶ አንችልም! እግዚአብሔር ሙሴን “ልምረው የምፈልገውን እምረዋለሁ፥ ልራራለት የምፈልገውንም እራራለታለሁ” ብሎታል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ምርጫ የሚገኘው በሰው ፈቃድና በሰው ሥራ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት ነው። በዚህ ምክንያት በቅዱስ መጽሐፍ ስለ ግብጽ ንጉሥ “በአንተ ኀይሌን ለማሳየትና ስሜም በዓለም ሁሉ ላይ እንዲታወቅ ለማድረግ አንተን አንግሼሃለሁ” የሚል ቃል ተጽፎአል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ይምረዋል፤ የሚፈልገውንም እልኸኛ ያደርገዋል።
ሮሜ 9:14-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ያዳላልን? በጭራሽ! ሙሴን “የምምረውን እምረዋለሁ፥ ለምራራለትም እራራለታለሁ” ብሎታልና። ስለዚህ ይህ ለፈለገ ወይም ለሮጠ አይደለም፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው። መጽሐፍ ፈርዖንን “ኃይሌ በአንተ እንዲታይ፥ ስሜም በምድር ሁሉ እንዲነገር፥ ለዚህ አስነሣሁህ” ይላልና። እንግዲህ የፈለገውን ይምረዋል የፈለገውንም እልከኛ ያደርገዋል።