ሮሜ 8:5-13
ሮሜ 8:5-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመጣብናል፤ የመንፈስ ዐሳብ ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል። የሥጋ ዐሳብ ለእግዚአብሔር ጠላቱ ነውና፤ ለእግዚአብሔርም ሕግ ስለማይገዛ፥ መፈጸም አይቻለውም። ለሥጋዊ ፈቃዳቸው የሚሠሩ ሁሉ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን ለመንፈሳዊ ሕግ እንጂ ለሥጋችሁ ፈቃድ የምትሠሩ አይደላችሁም፤ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ አድሮ ይኖራልና፤ የክርስቶስ መንፈስ ያላደረበት ግን እርሱ የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ ካደረባችሁ ግን ሰውነታችሁን ከኀጢአት ሥራ ለዩ፤ መንፈሳችሁንም ለጽድቅ ሥራ ሕያው አድርጉ። ጌታችን ኢየሱስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ ካደረባችሁ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ለይቶ ያስነሣው እርሱ አድሮባችሁ ባለ መንፈሱ ለሟች ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣታል። ወንድሞቻችን፥ አሁንም በሥጋችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይገባም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈሳዊ ሥራ የሥጋችሁን ፈቃድ ብትገድሉ ለዘለዓለም በሕይወት ትኖራላችሁ።
ሮሜ 8:5-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንደ ሥጋ የሚኖሩ ሐሳባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ሐሳባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋራ ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም። በሥጋ የሚመሩትም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችሉም። እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ።
ሮሜ 8:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።
ሮሜ 8:5-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ። ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል። ሥጋዊ ነገርን የሚያስብ ሰው ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይታዘዝና መታዘዝም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት ነው። ለሥጋዊ ነገር የሚገዙ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ በመንፈስ ፈቃድ እንጂ በሥጋ ፈቃድ አትኖሩም፤ የክርስቶስ መንፈስ የሌለውም ሰው የክርስቶስ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ከሆነ ምንም እንኳ ሥጋችሁ በኃጢአት ምክንያት የሚሞት ቢሆን እግዚአብሔር ስላጸደቃችሁ መንፈሳችሁ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው አምላክ በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ አማካይነት ለሟች ሥጋችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! በሕይወታችን ግዴታ አለብን፤ ነገር ግን ይህ ግዴታ በሥጋ ፈቃድ ለመኖር አይደለም። በሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሥጋዊ ሥራችሁን ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።
ሮሜ 8:5-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም አይችልም፥ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። ነገር ግን ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፥ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ፥ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ አማካይነት፥ ለሟች አካላቶቻችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ባለዕዳ ነን፤ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም፥ እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና የሰውነትን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ።