የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 8:4-39

ሮሜ 8:4-39 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

እናን ያጸ​ድ​ቀን ዘንድ፥ የኦ​ሪ​ት​ንም ሕግ ሠርቶ እንደ ፈጸመ ሰው ያደ​ር​ገን ዘንድ፤ ይህም በመ​ን​ፈ​ሳዊ ሕግ ጸን​ተው ለሚ​ኖሩ ነው እንጂ በሥጋ ሕግ ለሚ​ሠሩ አይ​ደ​ለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚ​ኖሩ የሥ​ጋን ነገር ያስ​ባ​ሉና፤ እንደ መን​ፈስ ፈቃድ የሚ​ኖሩ ግን የመ​ን​ፈ​ስን ነገር ያስ​ባሉ። የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመ​ጣ​ብ​ናል፤ የመ​ን​ፈስ ዐሳብ ግን ሰላ​ም​ንና ሕይ​ወ​ትን ይሰ​ጠ​ናል። የሥጋ ዐሳብ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጠላቱ ነውና፤ ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ሕግ ስለ​ማ​ይ​ገዛ፥ መፈ​ጸም አይ​ቻ​ለ​ውም። ለሥ​ጋዊ ፈቃ​ዳ​ቸው የሚ​ሠሩ ሁሉ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ደስ ማሰ​ኘት አይ​ች​ሉም። እና​ንተ ግን ለመ​ን​ፈ​ሳዊ ሕግ እንጂ ለሥ​ጋ​ችሁ ፈቃድ የም​ት​ሠሩ አይ​ደ​ላ​ች​ሁም፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ በእ​ና​ንተ አድሮ ይኖ​ራ​ልና፤ የክ​ር​ስ​ቶስ መን​ፈስ ያላ​ደ​ረ​በት ግን እርሱ የእ​ርሱ ወገን አይ​ደ​ለም። ክር​ስ​ቶስ ካደ​ረ​ባ​ችሁ ግን ሰው​ነ​ታ​ች​ሁን ከኀ​ጢ​አት ሥራ ለዩ፤ መን​ፈ​ሳ​ች​ሁ​ንም ለጽ​ድቅ ሥራ ሕያው አድ​ርጉ። ጌታ​ችን ኢየ​ሱ​ስን ከሙ​ታን ለይቶ ያስ​ነ​ሣው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ ካደ​ረ​ባ​ችሁ ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶ​ስን ከሙ​ታን ለይቶ ያስ​ነ​ሣው እርሱ አድ​ሮ​ባ​ችሁ ባለ መን​ፈሱ ለሟች ሰው​ነ​ታ​ችሁ ሕይ​ወ​ትን ይሰ​ጣ​ታል። ወን​ድ​ሞ​ቻ​ችን፥ አሁ​ንም በሥ​ጋ​ችን ሳለን በሥጋ ፈቃድ እን​ኖር ዘንድ አይ​ገ​ባም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብት​ኖሩ ትሞ​ታ​ላ​ችሁ፤ ነገር ግን በመ​ን​ፈ​ሳዊ ሥራ የሥ​ጋ​ች​ሁን ፈቃድ ብት​ገ​ድሉ ለዘ​ለ​ዓ​ለም በሕ​ይ​ወት ትኖ​ራ​ላ​ችሁ። በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መን​ፈስ የሚ​ሠሩ ሁሉ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች ናቸው። ዳግ​መ​ናም አባ አባት ብለን የም​ን​ጮ​ህ​በ​ትን የል​ጅ​ነት መን​ፈስ ተቀ​በ​ላ​ችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍ​ር​ሀት የባ​ር​ነት መን​ፈ​ስን አል​ተ​ቀ​በ​ላ​ች​ሁ​ምና። እና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች እን​ደ​ሆን ለል​ቡ​ና​ችን ምስ​ክሩ እርሱ መን​ፈስ ቅዱስ ነው። እና የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች ከሆን ወራ​ሾቹ ነን፤ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ወራ​ሾች ከሆ​ንም የክ​ር​ስ​ቶስ ወራ​ሾቹ ነን፤ በመ​ከራ ከመ​ሰ​ል​ነ​ውም በክ​ብር እን​መ​ስ​ለ​ዋ​ለን። ነገር ግን የዚህ ዓለም መከራ ለእና ሊገ​ለጥ ከአ​ለው ክብር ጋር እን​ደ​ማ​ይ​ተ​ካ​ከል ዐስቡ። የዓ​ለም ተስ​ፋው የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ልጅ መም​ጣት ይጠ​ባ​በቅ ነበ​ርና። ዓለም ባለ​ማ​ወቅ ለከ​ንቱ ነገር ተገ​ዝ​ቶ​አ​ልና በተ​ስፋ ስለ አስ​ገ​ዛው ነው እንጂ በፈ​ቃዱ አይ​ደ​ለም። ነገር ግን አስቶ በባ​ር​ነት ከሚ​ገ​ዛው ከዚህ ወጥቶ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ልጆች ወደ አገ​ኙ​አት የነ​ጻ​ነት ክብር ይገባ ዘንድ ተስፋ አለው። እስ​ካ​ሁን ዓለም ሁሉ ያዘ​ነና የተ​ከዘ እንደ ሆነ እና​ው​ቃ​ለን። ነገር ግን የሚ​ተ​ክዝ ዓለም ብቻ አይ​ደ​ለም፤ የመ​ን​ፈስ ቅዱ​ስን ፈለማ የተ​ቀ​በ​ል​ነው እናም ደግሞ እና​ዝ​ና​ለን እንጂ፤ የነ​ፍ​ሳ​ች​ንን ድኅ​ነት እና​ገኝ ዘንድ የል​ጅ​ነ​ትን ክብር ተስፋ እና​ደ​ር​ጋ​ለ​ንና፤ በእ​ም​ነ​ትም ድነ​ና​ልና። የሚ​ታ​የ​ውን ተስፋ ማድ​ረግ ተስፋ አይ​ደ​ለም፤ የሚ​ያ​የ​ው​ንማ እን​ዴት ተስፋ ያደ​ር​ጋል? እን​ዴ​ትስ ይጠ​ብ​ቃል? የማ​ይ​ታ​የ​ውን ተስፋ ብና​ደ​ርግ ግን እር​ሱን ተስፋ አድ​ር​ገን በእ​ርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕ​ግ​ሥ​ታ​ችን ይታ​ወ​ቃል። መን​ፈስ ቅዱ​ስም ከድ​ካ​ማ​ችን ይረ​ዳ​ናል፤ እን​ግ​ዲ​ያስ ተስ​ፋ​ች​ንን ካላ​ወ​ቅን ጸሎ​ታ​ችን ምን​ድ​ነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መን​ፈስ ቅዱስ ስለ መከ​ራ​ች​ንና ስለ ችግ​ራ​ችን ይፈ​ር​ድ​ል​ናል። እር​ሱም ልባ​ች​ንን ይመ​ረ​ም​ራል፤ ልብ የሚ​ያ​ስ​በ​ው​ንም እርሱ ያው​ቃል፤ ስለ ቅዱ​ሳ​ንም በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ዘንድ ይፈ​ር​ዳል። እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የሚ​ወ​ዱ​ትን ምር​ጦ​ቹን በበጎ ምግ​ባር ሁሉ እን​ደ​ሚ​ረ​ዳ​ቸው እና​ው​ቃ​ለን። ልጁ በብ​ዙ​ዎች ወን​ድ​ሞች መካ​ከል በኵር ይሆን ዘንድ አስ​ቀ​ድሞ ያወ​ቃ​ቸ​ው​ንና የመ​ረ​ጣ​ቸ​ውን እነ​ር​ሱን ልጁን ይመ​ስሉ ዘንድ አዘ​ጋ​ጅ​ቶ​አ​ቸ​ዋል። ያዘ​ጋ​ጃ​ቸ​ውን እነ​ር​ሱን ጠራ፤ የጠ​ራ​ቸ​ው​ንም እነ​ር​ሱን አጸ​ደቀ፤ የአ​ጸ​ደ​ቃ​ቸ​ው​ንም እነ​ር​ሱን አከ​በረ። እን​ግ​ዲህ ስለ​ዚህ ምን እን​ላ​ለን? እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ከእና ጋር ከሆነ ማን ይች​ለ​ናል? ለልጁ ስንኳ አል​ራ​ራም፤ ስለ ሁላ​ችን ቤዛ አድ​ርጎ አሳ​ልፎ ሰጠው እንጂ፥ እን​ግ​ዲህ እርሱ ሁሉን እን​ዴት አይ​ሰ​ጠ​ንም? እን​ግ​ዲህ እርሱ ራሱ ካጸ​ደቀ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የመ​ረ​ጣ​ቸ​ውን ሰዎች የሚ​ቃ​ወ​ማ​ቸው ማነው? የሚ​ፈ​ር​ድስ ማነው? የሞ​ተው፥ ይል​ቁ​ንም ከሙ​ታን ተለ​ይቶ የተ​ነ​ሣው፥ በእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ቀኝ የተ​ቀ​መ​ጠው፥ ደግሞ ስለ እና የሚ​ፈ​ር​ደው ኢየ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ነው። ከክ​ር​ስ​ቶስ ፍቅር ማን ይለ​የ​ናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራ​ቆት ነውን? ጭን​ቀት ነውን? ሾተል ነውን? መጽ​ሐፍ እን​ዳለ፥ “ስለ አንተ ዘወ​ትር ይገ​ድ​ሉ​ናል፤ እን​ደ​ሚ​ታ​ረዱ በጎ​ችም ሆነ​ናል።” ነገር ግን በወ​ደ​ደን በእ​ርሱ ሁሉን ድል እን​ነ​ሣ​ለን። ነገር ግን ሞትም ቢሆን፥ ሕይ​ወ​ትም ቢሆን፥ መላ​እ​ክ​ትም ቢሆኑ፥ አለ​ቆ​ችም ቢሆኑ፥ ያለ​ውም ቢሆን፥ የሚ​መ​ጣ​ውም ቢሆን በጌ​ታ​ችን በኢ​የ​ሱስ ክር​ስ​ቶስ ካለ ከእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ፍቅር ሊለ​የን እን​ደ​ማ​ይ​ችል አም​ና​ለሁ። ኀይ​ልም ቢሆን፥ ከፍ​ታም ቢሆን፥ ዝቅ​ታም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥ​ረ​ትም ቢሆን ከክ​ር​ስ​ቶስ ፍቅር ሊለ​የን የሚ​ችል የለም።

ሮሜ 8:4-39 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ይኸውም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ በምንመላለስ በእኛ፣ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ ልባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ልባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ለኀጢአት የተገዛ አእምሮ ከእግዚአብሔር ጋር ጠበኛ ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛም፤ መገዛትም አይችልም። በሥጋ የሚመሩትም እግዚአብሔርን ማስደሰት አይችሉም። እናንተ ግን፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ፣ በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ናችሁ። ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፣ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ፣ ሰውነታችሁ ከኀጢአት የተነሣ የሞተ ቢሆንም፣ መንፈሳችሁ ከጽድቅ የተነሣ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፣ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው፣ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ ሟች ለሆነው ሰውነታችሁ ሕይወትን ይሰጣል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ፤ ግዴታ አለብን፤ ይሁን እንጂ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና፤ ክፉ የሆነውን የሥጋ ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን፣ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደ ገና የፍርሀት ባሪያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ ሳይሆን፣ “አባ፣ አባት” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋልና፤ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆን ወራሾች ደግሞ ነን፤ የክብሩ ተካፋዮች እንሆን ዘንድ በርግጥ የመከራው ተካፋዮች ብንሆን፣ የእግዚአብሔር ወራሾች፣ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው፣ ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጓል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ገና ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፣ በትዕግሥት እንጠብቀዋለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው። ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህን ተረድቻለሁ፤ ሞትም ይሁን ሕይወት፣ መላእክትም ይሁኑ አጋንንት፣ ያለውም ይሁን የሚመጣው፣ ወይም ማንኛውም ኀይል፣ ከፍታም ይሁን ጥልቀት ወይም የትኛውም ፍጥረት፣ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።

ሮሜ 8:3-39 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኵኦነነ። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ቢሆን ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፥ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው የእርሱ መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ ክርስቶስ ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው እርሱ በእናንተ በሚኖረው በመንፈሱ፥ ለሚሞተው ሰውነታችሁ ደግሞ ሕይወትን ይሰጠዋል። እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ማለት የእግዚአብሔር ወራሾች ነን፥ አብረንም ደግሞ እንድንከብር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን። ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኵኦንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ሞት ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ግዛትም ቢሆን፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።

ሮሜ 8:4-39 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ይህንንም ያደረገው በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ፈቃድ በምንመላለስ በእኛ ትክክለኛው የሕግ ትእዛዝ እንዲፈጸም ነው። በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ። ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል። ሥጋዊ ነገርን የሚያስብ ሰው ለእግዚአብሔር ሕግ ስለማይታዘዝና መታዘዝም ስለማይችል የእግዚአብሔር ጠላት ነው። ለሥጋዊ ነገር የሚገዙ እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ የሚኖር ከሆነ በመንፈስ ፈቃድ እንጂ በሥጋ ፈቃድ አትኖሩም፤ የክርስቶስ መንፈስ የሌለውም ሰው የክርስቶስ ወገን አይደለም። ክርስቶስ በእናንተ ውስጥ ከሆነ ምንም እንኳ ሥጋችሁ በኃጢአት ምክንያት የሚሞት ቢሆን እግዚአብሔር ስላጸደቃችሁ መንፈሳችሁ ሕያው ነው። ኢየሱስን ከሞት ያስነሣው የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጣችሁ ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው አምላክ በውስጣችሁ በሚኖረው መንፈሱ አማካይነት ለሟች ሥጋችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞቼ ሆይ! በሕይወታችን ግዴታ አለብን፤ ነገር ግን ይህ ግዴታ በሥጋ ፈቃድ ለመኖር አይደለም። በሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞታላችሁ፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ሥጋዊ ሥራችሁን ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ስለዚህ “አባ! አባታችን ሆይ!” ብላችሁ የምትጠሩበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ በፍርሃት ለመኖር እንደገና የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁም። የእግዚአብሔር መንፈስ ከእኛ መንፈስ ጋር ሆኖ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለእኛ ይመሰክራል። እንግዲህ የእግዚአብሔር ልጆች ከሆንን የእርሱ ወራሾች ነን፤ ከክርስቶስም ጋር እንወርሳለን፤ አሁን የክርስቶስ መከራ ተካፋዮች ብንሆን በኋላ የክብሩ ተካፋዮች እንሆናለን። የአሁኑ ጊዜ መከራ ወደፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ቢመዛዘን በምንም ሊተካከል እንደማይችል አድርጌ እቈጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ከንቱ እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ ይኸውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በተስፋ እንዲጠባበቅ ባደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር የነፃነትና የክብር ተካፋይ እንደሚሆን ነው። ፍጥረት ሁሉ በአንድ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ መኖሩን እናውቃለን። ነገር ግን በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበልን እኛም የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጆች መሆንን በተስፋ እየተጠባበቅን በውስጣዊ ሰውነታችን በመቃተት ላይ እንገኛለን፤ እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ነገር ተስፋ ካደረግን ግን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ በድካማችን ይረዳናል፤ በቃል ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ያማልደናል። የሰውን ልብ የሚመረምር አምላክ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ምእመናን የሚያማልደው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ፈቃዱም ለተጠሩት ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው። እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል? እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለ እኛ አሳልፎ ከሰጠው እንዴት ከልጁ ጋር ሁሉን ነገር በነጻ አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቃቸው እርሱ ነው። ማነው የሚፈርድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርድባቸዋልን? እርሱ ስለ እኛ የሞተ፥ ከሞት ተነሥቶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ፥ ስለ እኛም የሚማልድ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማነው? ችግር ወይስ መከራ? ስደት፥ ወይስ ራብ? ወይስ ራቊትነት፥ ወይስ አደጋ? ወይስ ሰይፍ? ይህም፥ “ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ በወደደን በክርስቶስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ድል በመንሣት ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ስለዚህ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ባለሥልጣኖችም ቢሆኑ፥ አሁን ያለውም ቢሆን፥ በኋላ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኀይሎችም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ዝቅታም ቢሆን፥ ማንኛውም ፍጥረት ቢሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ካገኘነው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ እርግጠኛ ነኝ።

ሮሜ 8:4-39 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ፥ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው። ስለ ሥጋ ማሰብ የእግዚአብሔር ጠላት መሆን ነው፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም አይችልም፥ በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ማሰኘት አይችሉም። እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። ነገር ግን ማንም የክርስቶስ መንፈስ ከሌለው፥ እርሱ የክርስቶስ አይደለም። ክርስቶስ በውስጣችሁ ካለ ሰውነታችሁ በኃጢአት ምክንያት የሞተ ነው፤ መንፈሳችሁ ግን በጽድቅ ምክንያት ሕያው ነው። ነገር ግን ኢየሱስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ በእናንተ የሚኖር ከሆነ፥ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው መንፈስ፥ በውስጣችሁ በሚኖረው በመንፈሱ አማካይነት፥ ለሟች አካላቶቻችሁ ሕይወትን ይሰጠዋል። ስለዚህ ወንድሞች ሆይ! ባለዕዳ ነን፤ እንደ ሥጋ እንድንኖር ለሥጋ አይደለም፥ እንደ ሥጋ ብትኖሩ ትሞታላችሁና የሰውነትን ሥራ በመንፈስ ብትገድሉ ግን በሕይወት ትኖራላችሁ። በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ፥ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። እንደገና የፍርሃት ባርያ የሚያደርጋችሁን መንፈስ አልተቀበላችሁምና፥ ነገር ግን “አባ! አባት!” ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብላችኋል። የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን መንፈሱ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክርልናል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፤ ከእርሱ ጋር የክብሩ ተካፋዮች እንድንሆን ከእርሱ ጋር መከራ ብንቀበል የእግዚአብሔር ወራሾችና ከክርስቶስም ጋር አብረን ወራሾች ነን። የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ወደ ፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው እቆጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው። እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ስለ እኛም በእርግጥ የሚያማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? መከራ ወይስ ሥቃይ፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሃብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ አደጋ፥ ወይስ ሰይፍ? ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን። ይህንን ተረድቼአለሁ፤ ሞትም ቢሆን፥ ሕይወትም ቢሆን፥ መላእክትም ቢሆኑ፥ ገዢዎችም ቢሆኑ፥ ያለውም ቢሆን፥ የሚመጣውም ቢሆን፥ ኃይላትም ቢሆኑ፥ ከፍታም ቢሆን፥ ጥልቀትም ቢሆን፥ ሌላ ፍጥረትም ቢሆን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ ካለው ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን አይችልም።