ሮሜ 8:31-37
ሮሜ 8:31-37 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ ስለዚህ ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእና ጋር ከሆነ ማን ይችለናል? ለልጁ ስንኳ አልራራም፤ ስለ ሁላችን ቤዛ አድርጎ አሳልፎ ሰጠው እንጂ፥ እንግዲህ እርሱ ሁሉን እንዴት አይሰጠንም? እንግዲህ እርሱ ራሱ ካጸደቀ እግዚአብሔር የመረጣቸውን ሰዎች የሚቃወማቸው ማነው? የሚፈርድስ ማነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን ተለይቶ የተነሣው፥ በእግዚአብሔርም ቀኝ የተቀመጠው፥ ደግሞ ስለ እና የሚፈርደው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነውን? ኀዘን ነውን? ስደት ነውን? ራብ ነውን? መራቆት ነውን? ጭንቀት ነውን? ሾተል ነውን? መጽሐፍ እንዳለ፥ “ስለ አንተ ዘወትር ይገድሉናል፤ እንደሚታረዱ በጎችም ሆነናል።” ነገር ግን በወደደን በእርሱ ሁሉን ድል እንነሣለን።
ሮሜ 8:31-37 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ታዲያ ለዚህ ምን እንመልሳለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ፣ ማን ሊቃወመን ይችላል? ለገዛ ልጁ ያልሳሳለት፣ ነገር ግን ለሁላችንም አሳልፎ የሰጠው እርሱ፣ ሁሉንስ ነገር ከእርሱ ጋር እንደ ምን በልግስና አይሰጠን? እግዚአብሔር የመረጣቸውን የሚከስስ ማን ነው? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፤ ታዲያ የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፣ እንዲሁም ከሞት የተነሣው፣ በእግዚአብሔር ቀኝ የተቀመጠው ክርስቶስ ኢየሱስ፣ ስለ እኛ ይማልዳል። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? ችግር ነው ወይስ ሥቃይ፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ዕራቍትነት፣ ወይስ አደጋ፣ ወይስ ሰይፍ? ይህም፣ “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ ከሞት ጋር እንጋፈጣለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። ምንም አይለየንም፤ በዚህ ሁሉ በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
ሮሜ 8:31-37 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው፥ የሚኵኦንንስ ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ደግሞ ስለ እኛ የሚማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፥ ወይስ ጭንቀት፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ራብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ ፍርሃት፥ ወይስ ሰይፍ ነውን? ስለ አንተ ቀኑን ሁሉ እንገደላለን፥ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በዚህ ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
ሮሜ 8:31-37 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል? እግዚአብሔር ለአንድ ልጁ ሳይራራ ስለ እኛ አሳልፎ ከሰጠው እንዴት ከልጁ ጋር ሁሉን ነገር በነጻ አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቃቸው እርሱ ነው። ማነው የሚፈርድ? ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈርድባቸዋልን? እርሱ ስለ እኛ የሞተ፥ ከሞት ተነሥቶ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ የተቀመጠ፥ ስለ እኛም የሚማልድ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር ሊለየን የሚችል ማነው? ችግር ወይስ መከራ? ስደት፥ ወይስ ራብ? ወይስ ራቊትነት፥ ወይስ አደጋ? ወይስ ሰይፍ? ይህም፥ “ስለ አንተ በየቀኑ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎችም ተቈጠርን” ተብሎ እንደ ተጻፈው ነው። እንግዲህ በወደደን በክርስቶስ እነዚህን ነገሮች ሁሉ ድል በመንሣት ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።
ሮሜ 8:31-37 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ስለ እነዚህ ነገሮች ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል? ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው እርሱ፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም? እግዚአብሔር የመረጣቸውን ማን ይከሳቸዋል? የሚያጸድቅ እግዚአብሔር ነው። የሚኰንን ማን ነው? የሞተው፥ ይልቁንም ከሙታን የተነሣው፥ በእግዚአብሔር ቀኝ ያለው፥ ስለ እኛም በእርግጥ የሚያማልደው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየን ማን ነው? መከራ ወይስ ሥቃይ፥ ወይስ ስደት፥ ወይስ ረሃብ፥ ወይስ ራቁትነት፥ ወይስ አደጋ፥ ወይስ ሰይፍ? ይህም “ስለ አንተ ቀኑን ሙሉ እንገደላለን፤ እንደሚታረዱ በጎች ተቆጠርን፤” ተብሎ እንደ ተጻፈ ነው። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ግን በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን።