ሮሜ 8:18-30
ሮሜ 8:18-30 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ነገር ግን የዚህ ዓለም መከራ ለእና ሊገለጥ ከአለው ክብር ጋር እንደማይተካከል ዐስቡ። የዓለም ተስፋው የእግዚአብሔርን ልጅ መምጣት ይጠባበቅ ነበርና። ዓለም ባለማወቅ ለከንቱ ነገር ተገዝቶአልና በተስፋ ስለ አስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም። ነገር ግን አስቶ በባርነት ከሚገዛው ከዚህ ወጥቶ የእግዚአብሔር ልጆች ወደ አገኙአት የነጻነት ክብር ይገባ ዘንድ ተስፋ አለው። እስካሁን ዓለም ሁሉ ያዘነና የተከዘ እንደ ሆነ እናውቃለን። ነገር ግን የሚተክዝ ዓለም ብቻ አይደለም፤ የመንፈስ ቅዱስን ፈለማ የተቀበልነው እናም ደግሞ እናዝናለን እንጂ፤ የነፍሳችንን ድኅነት እናገኝ ዘንድ የልጅነትን ክብር ተስፋ እናደርጋለንና፤ በእምነትም ድነናልና። የሚታየውን ተስፋ ማድረግ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ እንዴት ተስፋ ያደርጋል? እንዴትስ ይጠብቃል? የማይታየውን ተስፋ ብናደርግ ግን እርሱን ተስፋ አድርገን በእርሱ እንደ ጸናን መጠን ትዕግሥታችን ይታወቃል። መንፈስ ቅዱስም ከድካማችን ይረዳናል፤ እንግዲያስ ተስፋችንን ካላወቅን ጸሎታችን ምንድነው? ነገር ግን እርሱ ራሱ መንፈስ ቅዱስ ስለ መከራችንና ስለ ችግራችን ይፈርድልናል። እርሱም ልባችንን ይመረምራል፤ ልብ የሚያስበውንም እርሱ ያውቃል፤ ስለ ቅዱሳንም በእግዚአብሔር ዘንድ ይፈርዳል። እግዚአብሔር የሚወዱትን ምርጦቹን በበጎ ምግባር ሁሉ እንደሚረዳቸው እናውቃለን። ልጁ በብዙዎች ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ አስቀድሞ ያወቃቸውንና የመረጣቸውን እነርሱን ልጁን ይመስሉ ዘንድ አዘጋጅቶአቸዋል። ያዘጋጃቸውን እነርሱን ጠራ፤ የጠራቸውንም እነርሱን አጸደቀ፤ የአጸደቃቸውንም እነርሱን አከበረ።
ሮሜ 8:18-30 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
የአሁኑ ዘመን ሥቃያችን ወደ ፊት ሊገለጥ ካለው፣ ለእኛ ከተጠበቀልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም እንዳይደለ እቈጥራለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተዳርጓል፤ ይኸውም በራሱ ምርጫ ሳይሆን፣ ለተስፋ እንዲገዛ ካደረገው ከፈቃዱ የተነሣ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው ወደ ከበረው ነጻነት እንዲደርስ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ በምጥ ጊዜ እንዳለው ሥቃይ በመቃተት ላይ እንደሚገኝ እናውቃለን። እርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የመጀመሪያውን የመንፈስ ፍሬ ያገኘን እኛ ራሳችን የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነታችንን በናፍቆት እየተጠባበቅን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ተስፋው የሚታይ ከሆነ ግን ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ገና ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፣ በትዕግሥት እንጠብቀዋለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ያግዘናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅም፤ መንፈስ ግን በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ይማልድልናል። ልባችንንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስን ሐሳብ ያውቃል፤ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔር፣ ለሚወድዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወሰናቸው፤ ይኸውም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኵር እንዲሆን ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውን አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን አከበራቸው።
ሮሜ 8:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ። የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና። ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤ ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው። ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና። እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፥ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። ልጁ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ይሆን ዘንድ፥ አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና፤ አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።
ሮሜ 8:18-30 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
የአሁኑ ጊዜ መከራ ወደፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ቢመዛዘን በምንም ሊተካከል እንደማይችል አድርጌ እቈጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃል። ፍጥረት ሁሉ ከንቱ እንዲሆን ተፈርዶበታል፤ ይኸውም በራሱ ፍላጎት ሳይሆን በተስፋ እንዲጠባበቅ ባደረገው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ከጥፋት ባርነት ነጻ ወጥቶ ከእግዚአብሔር ልጆች ጋር የነፃነትና የክብር ተካፋይ እንደሚሆን ነው። ፍጥረት ሁሉ በአንድ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ በምጥ ጭንቀት ተይዞ በመቃተት ላይ መኖሩን እናውቃለን። ነገር ግን በመቃተት ላይ ያለው ፍጥረት ብቻ አይደለም፤ የመጀመሪያውን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ የተቀበልን እኛም የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን የእግዚአብሔር ልጆች መሆንን በተስፋ እየተጠባበቅን በውስጣዊ ሰውነታችን በመቃተት ላይ እንገኛለን፤ እኛ የዳንነው በዚሁ ተስፋ ነው። ነገር ግን ተስፋ የምናደርገው ነገር የሚታይ ከሆነ ተስፋ መሆኑ ይቀራል፤ የሚታየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? የማናየውን ነገር ተስፋ ካደረግን ግን በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም እንዴት መጸለይ እንደሚገባን ስለማናውቅ መንፈስ ቅዱስ በድካማችን ይረዳናል፤ በቃል ሊገለጥ በማይቻል መቃተት ያማልደናል። የሰውን ልብ የሚመረምር አምላክ የመንፈስ ቅዱስ ሐሳብ ምን እንደ ሆነ ያውቃል፤ መንፈስ ቅዱስ ስለ ምእመናን የሚያማልደው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ነው። እግዚአብሔርን ለሚወዱና እንደ ፈቃዱም ለተጠሩት ሰዎች እግዚአብሔር ሁሉን ነገር ለበጎ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን። ይህም የሆነበት ምክንያት አስቀድሞ ያወቃቸው ልጁን እንዲመስሉና ልጁም ከብዙ ወንድሞች መካከል በኵር እንዲሆን እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለ ወሰነ ነው። አስቀድሞ የወሰናቸውን ጠራቸው፤ የጠራቸውንም አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም አከበራቸው።
ሮሜ 8:18-30 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ወደ ፊት ለእኛ ከሚገለጥልን ክብር ጋር ሲነጻጸር ምንም ዋጋ እንደሌለው እቆጥረዋለሁ። ፍጥረት ሁሉ የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ በታላቅ ናፍቆት ይጠባበቃልና። ፍጥረት ሁሉ ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ ይኸውም በራሱ ፈቃድ ሳይሆን በተስፋ እንዲገዛ ባደረገው በእርሱ ፈቃድ ነው። ይህም ፍጥረት ራሱ ከመበስበስ ባርነት ነጻ ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደ ሆነው የከበረውን ነፃነት እንዲያገኝ ነው። እስከ አሁን ድረስ ፍጥረት ሁሉ አብሮ በመቃተትና በምጥ ሥቃይ እንደሚኖር እናውቃለንና። ፍጥረት ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን እኛ ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት በናፍቆት እየተጠባበቅን እኛ ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን። በዚህ ተስፋ ድነናል፤ ነገር ግን ተስፋው የሚታይ ከሆነ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል? ነገር ግን ያላየነውን ተስፋ ብናደርግ፥ በትዕግሥት እንጠባበቃለን። እንዲሁም ደግሞ መንፈስ በድካማችን ይረዳናል፤ እንዴት መጸለይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በቃላት ሊገለጥ በማይችል መቃተት ለእኛ ያማልድልናል፤ ልቦችንም የሚመረምረው እርሱ የመንፈስ ሐሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፥ ምክንያቱም መንፈስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ያማልዳልና። እግዚአብሔርንም ለሚወዱት እንደ ዓላማውም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን። አስቀድሞ ያወቃቸውን የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖአልና፥ ይህም ከብዙ ወንድሞች መካከል እርሱ በኩር እንዲሆን ነው፤ አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህንም ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውን እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውን እነዚህንም ደግሞ አከበራቸው።