ሮሜ 8:1-6
ሮሜ 8:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ በኢየሱስ ክርስቶስ ላሉት በመንፈስ እንጂ በሥጋ ለማይመላለሱ ፍርድ የለባቸውም። በኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠን ሕይወት የሚገኝበት የመንፈስ ሕግ እርሱ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶናልና። ስለ ሥጋ ደካማነት የኦሪት ሕግ ከሞት ማዳን በተሳነው ጊዜ እግዚአብሔር በኀጢኣተና ሥጋ ምሳሌ ልጁን ላከ፤ ያችንም ኀጢአት በሥጋው ቀጣት። እናን ያጸድቀን ዘንድ፥ የኦሪትንም ሕግ ሠርቶ እንደ ፈጸመ ሰው ያደርገን ዘንድ፤ ይህም በመንፈሳዊ ሕግ ጸንተው ለሚኖሩ ነው እንጂ በሥጋ ሕግ ለሚሠሩ አይደለም። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። የሥጋ ዐሳብ ሞትን ያመጣብናል፤ የመንፈስ ዐሳብ ግን ሰላምንና ሕይወትን ይሰጠናል።
ሮሜ 8:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ያሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም፤ ምክንያቱም የሕይወት መንፈስ ሕግ በክርስቶስ ኢየሱስ ከኀጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቷችኋል። ሕግ ከሥጋ ባሕርይ የተነሣ ደክሞ ሊፈጽም ያልቻለውን፣ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኀጢአተኛ ሰው አምሳል፣ የኀጢአት መሥዋዕት እንዲሆን በመላክ ፈጸመው፤ በዚህም ኀጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ ይኸውም በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ በምንመላለስ በእኛ፣ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ ሙሉ በሙሉ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ ልባቸውን በሥጋ ፍላጎት ላይ ያሳርፋሉ፤ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን ልባቸውን በመንፈስ ፍላጎት ላይ ያደርጋሉ። የሥጋን ነገር ማሰብ ሞት ነው፤ የመንፈስን ነገር ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።
ሮሜ 8:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኵነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ አርነት አውጥቶኛልና። ከሥጋ የተነሣ ስለ ደከመ ለሕግ ያልተቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌ በኃጢአትም ምክንያት ልኮ አድርጎአልና፤ እንደ መንፈስ ፈቃድ እንጂ እንደ ሥጋ ፈቃድ በባንመላለስ በእኛ የሕግ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ ኃጢአትን በሥጋ ኵኦነነ። እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።
ሮሜ 8:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚኖሩ አሁን ኲነኔ የለባቸውም። በኢየሱስ ክርስቶስ የሚገኘውን ሕይወት የሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነጻ አውጥቶኛል። ከሰው ባሕርይ ደካማነት የተነሣ ሕግ ሊያደርገው ያልቻለውን እግዚአብሔር አድርጎታል፤ የገዛ ልጁንም በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌነት በኃጢአት ምክንያት ልኮ በሥጋው ኃጢአትን በፍርድ አስወገደ። ይህንንም ያደረገው በሥጋ ፈቃድ ሳይሆን በመንፈስ ፈቃድ በምንመላለስ በእኛ ትክክለኛው የሕግ ትእዛዝ እንዲፈጸም ነው። በሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ ሥጋዊ ነገርን፥ በመንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን መንፈሳዊ ነገርን ያስባሉ። ሥጋዊ ነገርን ማሰብ ሞትን ያመጣል፤ መንፈሳዊ ነገርን ማሰብ ግን ሕይወትንና ሰላምን ይሰጣል።
ሮሜ 8:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ስለዚህ በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም። በክርስቶስ ኢየሱስ ያለው የሕይወት መንፈስ ሕግ ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ አውጥቶኛልና። ሕግ ከሥጋ ድካም የተነሣ ማድረግ ያልቻለውን፥ እግዚአብሔር የገዛ ልጁን በኃጢአተኛ ሥጋ ምሳሌና ስለ ኃጢአት ልኮ ኃጢአትን በሥጋ ኰነነ፤ እንደ ሥጋ ሳይሆን እንደ መንፈስ በምንመላለስ በእኛ፥ ሕጉ የሚጠይቀው ጽድቅ እንዲፈጸም ነው። እንደ ሥጋ የሚኖሩ አእምሮአቸው የሥጋን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉና፥ እንደ መንፈስ የሚኖሩ ግን አእምሮአቸው የመንፈስን ነገር እንዲያስብ ያደርጋሉ። ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።