ሮሜ 7:18-25
ሮሜ 7:18-25 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በእኔ ማለት በሥጋዬ መልካም ነገር እንደማይኖር አውቃለሁ፤ መልካም ሥራ ለመሥራት መሻቱስ በእኔ ዘንድ አለ፤ በጎ ምግባር መሥራት ግን የለኝም። ያን የምወደውንም በጎ ነገር የማደርግ አይደለም፤ ነገር ግን ያን የምጠላውን ክፉውን አደርጋለሁ። የማልወደውንስ የምሠራ ከሆነ የምሠራው እኔ አይደለሁም፤ በእኔ ላይ ያደረች ኀጢአት ናት እንጂ። መልካም ሥራ እንድሠራ የፈቀደልኝን ያን ሕግ እርሱ ክፉ ነገር አምጥቶብኝ አገኘሁት። በልቡናዬ ውስጥ ያለ የእግዚአብሔር ሕግ መልካም ነው። ነገር ግን በሰውነቴ ውስጥ ያለውን ሌላ የኀጢአት ሕግ እመለከታለሁ፤ በልቡናዬም ውስጥ ካለው ከእግዚአብሔር ሕግ ጋር ተሰልፈው ተዋጉ፤ በሰውነቴ ውስጥ ያለው ያ የኀጢአት ሕግም በረታና ወደ እርሱ ማረከኝ። እኔ ምንና ወራዳ ሰው ነኝ፤ ከዚህ ሟች ሰውነቴ ማን ባዳነኝ? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እኔ በልቤ ለእግዚአብሔር ሕግ እገዛለሁ፤ በሥጋዬ ግን ለኀጢአት ሕግ እገዛለሁ።
ሮሜ 7:18-25 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም። የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው። ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው። ስለዚህ ይህ ሕግ እየሠራ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ፤ ይኸውም በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋር አለ። በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ። እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣ በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።
ሮሜ 7:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በእኔ ማለት በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁና፤ ፈቃድ አለኝና፥ መልካሙን ግን ማድረግ የለኝም። የማልወደውን ክፉን ነገር አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን በጎውን ነገር አላደርገውም። የማልወደውን የማደርግ ከሆንሁ ግን ያን የማደርገው አሁን እኔ አይደለሁም፥ በእኔ የሚኖር ኃጢአት ነው እንጂ። እንግዲያስ መልካሙን አደርግ ዘንድ ስወድ በእኔ ክፉ እንዲያድርብኝ ሕግን አገኛለሁ። በውስጡ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን በብልቶቼ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በብልቶቼ ባለ በኃጢአት ሕግ የሚማርከኝን ሌላ ሕግ አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ እገዛለሁ።
ሮሜ 7:18-25 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በእኔ ወይም በእኔ ሥጋዊ ባሕርይ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፤ መልካም ነገርን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም እንኳ ያን መልካም ነገር ለማድረግ ችሎታ የለኝም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገርን አላደርግም፤ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ። ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር የማደርግ ከሆንኩ ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም ማለት ነው። ስለዚህ ሕግ በሥራ ላይ ውሎ አያለሁ፤ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፉ ነገርን ለማድረግ እገደዳለሁ። ውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል። ይሁን እንጂ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር እየተቃረነ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ለሚሠራው የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ የተፈጥሮ ዝንባሌ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ሟች ሰውነትስ ማን ያድነኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሚያድነኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እንግዲህ እኔ በአእምሮዬ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዢ ስሆን በሥጋ ባሕርዬ ለኃጢአት ሕግ ተገዢ ሆኜአለሁ።
ሮሜ 7:18-25 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በእኔ ማለትም በሥጋዬ ምንም መልካም ነገር እንደማይኖር አውቃለሁና፤ መልካምን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም ነገር ግን ልፈፅመው አልችልም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፥ ነገር ግን ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁና። የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ፥ ያን የማደርገው እኔ ሳልሆን በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። ስለዚህ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፋት ወደ እኔ ይቀርባል፤ ይኸውም ሕግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ክፍሎች ባለ በኃጢአት ሕግ ምርኮኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባርያ ስሆን፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባርያ ነኝ።