የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 6:12-18

ሮሜ 6:12-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

በዚህ በሚ​ሞት ሰው​ነ​ታ​ችሁ ኀጢ​አ​ትን አታ​ን​ግ​ሡ​አት፤ ለም​ኞ​ቱም እሽ አት​በ​ሉት። ከሙ​ታን ተለ​ይቶ እንደ ተነሣ፥ ራሳ​ች​ሁን ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር መሥ​ዋ​ዕት አድ​ርጉ እንጂ ሰው​ነ​ታ​ች​ሁን ለኀ​ጢ​አት የዐ​መፅ የጦር መሣ​ሪያ አታ​ድ​ር​ጉት፤ ሰው​ነ​ታ​ች​ሁ​ንም ለእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር የጽ​ድቅ የጦር መሣ​ሪያ አድ​ርጉ። እን​ግ​ዲህ ኀጢ​አት አት​ገ​ዛ​ች​ሁም፤ የኦ​ሪ​ትን ሕግ ከመ​ሥ​ራት ወጥ​ታ​ችሁ ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋ ገብ​ታ​ች​ኋ​ልና። እን​ግ​ዲህ ምን እን​ላ​ለን? የኦ​ሪ​ትን ሕግ ከመ​ሥ​ራት ወጥ​ተን ወደ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ጸጋ ስለ ገባን ኀጢ​አት እን​ሥ​ራን? አይ​ደ​ለም። ለም​ት​ታ​ዘ​ዙ​ለት፥ እሺ ለም​ት​ሉ​ትም እና​ንተ አገ​ል​ጋ​ዮች እንደ ሆና​ችሁ አታ​ው​ቁ​ምን? ለተ​ባ​በ​ራ​ች​ሁ​ለ​ትስ ራሳ​ች​ሁን እንደ አስ​ገ​ዛ​ችሁ አታ​ው​ቁ​ምን? ኀጢ​አ​ት​ንም እሺ ብት​ሉ​አት፥ ተባ​ብ​ራ​ች​ሁም ብት​በ​ድሉ እና​ንት ለሞት ተገ​ዢ​ዎች ትሆ​ና​ላ​ችሁ፤ ጽድ​ቅ​ንም እሺ ብት​ሉ​አት ለበጎ ሥራም ብት​ተ​ባ​በሩ የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔር አገ​ል​ጋ​ዮች ናችሁ። የኀ​ጢ​አት ተገ​ዦች ስት​ሆኑ ምሳ​ሌ​ነቱ ለተ​ሰ​ጣ​ችሁ ለም​ት​ማ​ሩት ትም​ህ​ርት ታዝ​ዛ​ች​ኋ​ልና እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ይመ​ስ​ገን። አሁን ግን ከኀ​ጢ​አት ነጻ ሁና​ችሁ ለጽ​ድቅ ተገ​ዝ​ታ​ች​ኋል።

ሮሜ 6:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና። እንግዲህ ምን ይሁን? ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላይደለን ኃጢአትን እንሥራን? አይደለም። ለመታዘዝ ባሪያዎች እንድትሆኑ ራሳችሁን ለምታቀርቡለት፥ ለእርሱ ለምትታዘዙለት ባሪያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? ወይም ለሞት የኃጢአት ባሪያዎች ወይም ለጽድቅ የመታዘዝ ባሪያዎች ናችሁ። ነገር ግን አስቀድማችሁ የኃጢአት ባሪያዎች ከሆናችሁ፥ ለተሰጣችሁለት ለትምህርት ዓይነት ከልባችሁ ስለ ታዘዛችሁ፥ ከኃጢአትም አርነት ወጥታችሁ ለጽድቅ ስለ ተገዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን።

ሮሜ 6:12-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ስለዚህ ኃጢአት በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ሥልጣን እንዲኖረውና ለሥጋ ምኞትም ተገዢ እንዲያደርጋችሁ አትፍቀዱለት። እንዲሁም የሰውነታችሁን ክፍሎች የዐመፅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታስገዙ፤ ነገር ግን ከሞት ተነሥታችሁ ሕያዋን እንደ ሆናችሁ በማድረግ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች ሁሉ የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አስገዙ። አሁን እናንተ የምትኖሩት ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆነ ኃጢአት ሊገዛችሁ አይገባም። እንግዲህ ምን እንላለን? ከሕግ በታች መሆናችን ቀርቶ ከጸጋ በታች ስለ ሆንን ኃጢአት እንሥራ ማለት ነውን? ከቶ አይደለም! ለአንድ ሰው አገልጋዮች ሆናችሁ ለመታዘዝ ራሳችሁን ስታቀርቡ ለዚያ ለምትታዘዙለት ሰው አገልጋዮች መሆናችሁን ታውቃላችሁ፤ እንዲሁም ለኃጢአት ብትታዘዙ ሞትን ለሚያመጣባችሁ ኃጢአት አገልጋዮች ትሆናላችሁ፤ ለእግዚአብሔር ብትታዘዙ ግን ጽድቅን ታገኛላችሁ። እናንተ አስቀድሞ የኃጢአት ባሪያዎች ነበራችሁ፤ አሁን ግን ለተቀበላችሁት ትምህርት ከልብ በመታዘዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ከኃጢአት ባርነት ነጻ ወጥታችሁ የጽድቅ አገልጋዮች ሆናችኋል።

ሮሜ 6:12-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ስለዚህ፥ ለምኞቱ ታዛዥ ሊያደርጋችሁ በሚሞተው ሰውነታችሁ ላይ ኃጢአት አይንገሥ። የሰውነታችሁን ክፍሎች የክፋት መሣሪያ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፤ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ የሰውነታችሁንም ክፍሎች የጽድቅ መሣሪያ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ። ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች ስላልሆናችሁ ኃጢአት አይገዛችሁም። እንግዲህ ምን ይሁን? ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋ በታች ስለ ሆንን ኃጢአት መሥራት አለብንን? በጭራሽ! እራሳችሁን የመታዘዝ ባርያዎች አድርጋችሁ ለምታቀርቡለት፥ ለምትታዘዙት ለእርሱ ሞትን ለሚያመጣው ለኃጢአት ወይም ጽድቅን ለሚያመጣው ለመታዘዝ ባርያዎች እንደ ሆናችሁ አታውቁምን? አስቀድማችሁ የኃጢአት ባርያዎች የነበራችሁ፥ ነገር ግን ለተሰጣችሁለት የትምህርት ዓይነት ከልባችሁ በመታዘዛችሁ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። ከኃጢአትም ነፃ ወጥታችሁ ለጽድቅ ባርያዎች ሆናችኋል።