ሮሜ 5:6-15
ሮሜ 5:6-15 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክርስቶስም እና ኀጢአተኞች ስንሆን ስለ ኀጢአታችን ይሞት ዘንድ ዘመኑ ሲደርስ መጣ። ስለ ክፉዎች በጭንቅ ጊዜ ስንኳ ቢሆን ሊሞት የሚደፍር አይገኝም፤ ስለ ደጋጉ ግን ሊሞት የሚጨክን የሚገኝ እንዳለ እንጃ። እግዚአብሔር ምን ያህል እንደ ወደደን እነሆ፥ እዩ፤ እና ኀጢአተኞች ስንሆን ክርስቶስ ስለ እና ሞተ። እንግዲህ በደሙ ዛሬ ከጸደቅን ከሚመጣው መከራ በእርሱ እንድናለን። እና የእግዚአብሔር ጠላቶቹ ስንሆን በልጁ ሞት ይቅር ካለን፥ ከታረቀን በኋላም በልጁ ሕይወት እንዴት የበለጠ ያድነን! በዚህ ብቻ አይደለም፤ በእርሱ ይቅርታውን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስም በእግዚአብሔር ዘንድ እንመካለን እንጂ። ስለዚህም በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኀጢአት ወደ ዓለም ገባች፤ ስለዚችም ኀጢአት ሞት ገባ፤ እንደዚሁም ሁሉ ኀጢአትን ስለ አደረጉ በሰው ሁሉ ላይ ሞት መጣ። ኦሪት እስከ መጣች ድረስ ኀጢአት ምን እንደ ሆነች ሳትታወቅ በዓለም ውስጥ ነበረች፤ ነገር ግን የኦሪት ሕግ ገና ስላልመጣ ኀጢአት ተብላ አትቈጠርም ነበር። ነገር ግን በአዳም ኀጢአት ምክንያት ከአዳም እስከ ሙሴ የበደሉትንም ያልበደሉትንም ሞት ገዛቸው፤ ሁሉ በአዳም አምሳል ተፈጥሮአልና፥ አዳምም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋው በበደላችን መጠን የሆነብን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎች ከሞቱ፥ እንግዲህ በእግዚአብሔር ጸጋ፥ በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት በሰጠን ሀብቱ ሕይወት በብዙዎች ላይ እንዴት እጅግ ይበዛ ይሆን?
ሮሜ 5:6-15 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ገና ደካሞች ሳለን፣ ልክ ጊዜው ሲደርስ፣ ክርስቶስ ስለ ኀጢአተኞች ሞቷልና። ለጻድቅ የሚሞት ሰው ማግኘት እጅጉን ያዳግታል፤ ለደግ ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኀጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያሳያል። አሁን በደሙ ከጸደቅን፣ ይልቁንማ በርሱ በኩል ከእግዚአብሔር ቍጣ እንዴት አንድንም! የእግዚአብሔር ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት ከርሱ ጋራ ከታረቅን፣ ዕርቅን ካገኘን በኋላ፣ በሕይወቱማ መዳናችን እንዴት የላቀ አይሆንም! ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን። ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቷል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኀጢአት በዓለም ላይ ነበር፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኀጢአት አይቈጠርም። ይሁን እንጂ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ባሉት፣ እንደ አዳም ሕግን በመጣስ ኀጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው አምሳሉ ነበረ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው መተላለፍ ብዙዎቹ ከሞቱ፣ የእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው፣ ይኸውም በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የመጣው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት አብልጦ ይትረፈረፍ!
ሮሜ 5:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ገና ደካሞች ሳለን ክርስቶስ ዘመኑ ሲደርስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቶአልና። ስለ ጻድቅ የሚሞት በጭንቅ ይገኛልና፤ ስለ ቸር ሰው ግን ሊሞት እንኳ የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞቶአልና እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። ይልቁንስ እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን በእርሱ ከቍጣው እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን አሁን መታረቁን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤ ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቍኦጠርም፤ ነገር ግን በአዳም መተላለፍ ምሳሌ ኃጢአትን ባልሠሩት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ፤ አዳም ይመጣ ዘንድ ላለው ለእርሱ አምሳሉ ነውና። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን እንደዚያው አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ሞተዋልና፥ ነገር ግን የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የሆነው ስጦታ ከዚያ ይልቅ ለብዙዎች በዛ።
ሮሜ 5:6-15 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ገና ደካሞች ሆነን ሳለ እግዚአብሔር በወሰነው ጊዜ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞተ። በጻድቅ ምትክ ሆኖ የሚሞት ሰው ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነው፤ ሆኖም በደግ ሰው ምትክ ለመሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን እኛ ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ሞቶአል፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር ምን ያኽል ታላቅ መሆኑን ያስረዳል። እንግዲህ የጸደቅነው በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ከሆነ ይበልጡንም ከእግዚአብሔር ቊጣ የምንድነው በእርሱ አማካይነት ነው። እኛ የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነን ሳለ በልጁ ሞት ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀናል፤ አሁን ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቅን በኋላ በልጁ ሕይወት አማካይነት ይበልጡን እንድናለን። ይህም ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነትም በእግዚአብሔር እንመካለን። በአንድ ሰው ምክንያት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአት ምክንያትም ሞት መጣ፤ እንዲሁም ሰው ሁሉ ኃጢአትን ስለ ሠራ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ የሙሴ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበር፤ ይሁን እንጂ ሕግ በሌለበት ኃጢአት ራሱ እንደ ኃጢአት አይቈጠርም ነበር። ሆኖም እንደ አዳም ሕግን በመተላለፍ ኃጢአት ባልሠሩት ላይ እንኳ ሳይቀር ሞት ከአዳም አንሥቶ እስከ ሙሴ ድረስ በሰው ሁሉ ላይ ሥልጣን አገኘ። ይህ አዳም ወደፊት ለሚመጣው ክርስቶስ ምሳሌ ነበረ። ነገር ግን የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታው እንደ ሰው ኃጢአት አይደለም፤ በአንድ ሰው ኃጢአት ምክንያት ብዙዎች እንደ ሞቱ እንዲሁም በእግዚአብሔር ጸጋና በአንዱ ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያት የተገኘው የጸጋ ስጦታ ለብዙዎች ተትረፍርፎ ተሰጥቶአል።
ሮሜ 5:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ገና ደካሞች ሳለን፥ በትክክለኛው ጊዜ ክርስቶስ ስለ ኃጢአተኞች ሞቷልና። ስለ ጻድቅ ሰው ሲል የሚሞት ሰው ማግኘት አስቸጋሪ ነው፤ ስለ መልካም ሰው ሲል ሊሞት የሚደፍር ምናልባት ይገኝ ይሆናል። ነገር ግን ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ ስለ እኛ ሞተ፤ ይህም እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር ያስረዳል። እንግዲህ አሁን በደሙ ከጸደቅን ይበልጡንም በእርሱ በኩል ከቁጣ እንድናለን። ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤ ይህም ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን አሁን ዕርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ እንመካለን። ስለዚህ ኃጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ፥ ሞትም በኃጢአት በኩል እንደመጣ፥ እንዲሁም ሁሉም ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ ሞት በሰው ሁሉ ላይ መጣ፤ ሕግ ከመሰጠቱ በፊት ኃጢአት በዓለም ነበረና፤ ነገር ግን ሕግ በሌለበት ኃጢአት አይቆጠርም። ነገር ግን ለሚመጣው ምሳሌ እንደነበረው እንደ አዳም ሕግን ባልተላለፉት ላይ እንኳ፥ ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ። ነገር ግን ስጦታው እንደ በደሉ መጠን አይደለም፤ በአንድ ሰው በደል ብዙዎቹ ከሞቱ፥ ይልቁንም የእግዚአብሔር ጸጋና በአንድ ሰው፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ያለው ስጦታ ለብዙዎች እንዴት ይበዛ።