ሮሜ 5:18-21
ሮሜ 5:18-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ በአንዱ ሰው በደል ዓለም ሁሉ እንደ ተፈረደበት፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው ጽድቅ ሰው ሁሉ ይጸድቃል። በአንድ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንድ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። ኦሪትስ ኀጢአትን ታበዛት ዘንድ መጣች፤ ኀጢአትም ከበዛች ዘንድ የእግዚአብሔር ጸጋ በዛች። ኀጢአትም ሞትን እንደ አነገሠችው እንዲሁ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ጸጋ ጽድቅን ለዘለዓለም ሕይወት ታነግሠዋለች።
ሮሜ 5:18-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከእንግዲህ በአንድ ሰው መተላለፍ የተነሣ ኵነኔ በሁሉ ሰው ላይ እንደ መጣ፣ እንዲሁም በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኀጢአተኞች እንደ ሆኑ፣ በአንዱ ሰው መታዘዝ ደግሞ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። ሕግ በመምጣቱ መተላለፍ በዛ፤ ነገር ግን ኀጢአት በበዛበት ጸጋ አብልጦ የተትረፈረፈ ሆነ፤ ይህም የሆነው ኀጢአት በሞት እንደ ነገሠ ሁሉ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ደግሞ የዘላለም ሕይወት ይገኝ ዘንድ ጸጋ በጽድቅ እንዲነግሥ ነው።
ሮሜ 5:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኵነኔ ወደ ሰው ሁሉ እንደ መጣ፥ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ሕይወትን ለማጽደቅ ወደ ሰው ሁሉ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በደልም እንዲበዛ ሕግ ጭምር ገባ፤ ዳሩ ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተነሣ በጽድቅ ምክንያት ለዘላለም ሕይወት ይነግሥ ዘንድ፥ ጸጋ ከመጠን ይልቅ በለጠ።
ሮሜ 5:18-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ የአንዱ የአዳም ኃጢአት የቅጣትን ፍርድ በሰው ሁሉ ላይ እንዳመጣ እንዲሁም የአንዱ የክርስቶስ የጽድቅ ሥራ ብዙዎችን ከቅጣት ነጻ አድርጎ ሕይወትን ይሰጣል። በአዳም አለመታዘዝ ምክንያት ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ እንዲሁም በክርስቶስ መታዘዝ ምክንያት ብዙዎች ይጸድቃሉ። ኃጢአት ይበዛ ዘንድ ሕግ መጣ፤ ነገር ግን ኃጢአት በበዛ መጠን የእግዚአብሔር ጸጋ በይበልጥ በዛ። ይህም የሆነው በሞት ምክንያት ኃጢአት እንደ ነገሠ ሁሉ እንዲሁም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አማካይነት ዘለዓለማዊ ሕይወት እንዲገኝ የእግዚአብሔር ጸጋ ጽድቅን በመስጠት ይነግሣል።
ሮሜ 5:18-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ በአንድ ሰው በደል ምክንያት ኩነኔ ለሰው ሁሉ እንደመጣ፥ እንዲሁም በአንድ ሰው የጽድቅ ሥራ ምክንያት ሕይወትን ለማጽደቅ መጣ። በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ ሰው መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ። በደል እንዲበዛ ሕግ ገባ፤ ነገር ግን ኃጢአት በበዛበት፥ ጸጋ ይበልጥ በዛ፤ ይህም የሆነው፥ ኃጢአት በሞት እንደ ነገሠ፥ እንዲሁ ደግሞ ጸጋ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘለዓለም ሕይወት፥ በጽድቅ በኩል እንዲነግሥ ነው።