ሮሜ 4:7-13
ሮሜ 4:7-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
“መተላለፋቸው የቀረላቸው፥ ኀጢአታቸውም የተሰረየላቸው ብፁዓን ናቸው። እግዚአብሔርም በደሉን የማይቈጥርበት ሰው ብፁዕ ነው።” እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገዘር ተነገረን? ወይስ ስለ አለመገዘር? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት እንላለንና። ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ተገዝሮ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገዘር? ሳይገዘር ነው እንጂ ተገዝሮ ሳለ አይደለም። ሳይገዘር እግዚአብሔር አብርሃምን በእምነት እንደ አጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማኅተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው። ሳይገዘሩ ለሚያምኑ ሁሉ አባት ሊሆን፥ አብርሃም በእምነት እንደ ከበረ እነርሱም በእምነት እንደሚከብሩ ያውቁ ዘንድ ሰጠው። ለተገዘሩትም አባት ይሆን ዘንድ ነው፤ ነገር ግን ለተገዘሩት ብቻ አይደለም፤ እርሱ አባታችን አብርሃም ሳይገዘር እንደ አመነ ሳይገዘሩ የአባታችን የአብርሃምን የሃይማኖቱን ፍለጋ ለሚከተሉ ደግሞ ነው እንጂ። አብርሃም፥ ዘሩም ዓለምን ይወርስ ዘንድ ተስፋ ያገኘ የኦሪትን ሥራ በመሥራት አይደለም፤ በእግዚአብሔር ቃል፥ እርሱንም በማመን በእውነተና ሃይማኖቱ ይህን አገኘ እንጂ።
ሮሜ 4:7-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
“መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኀጢአታቸው የተሰረየላቸው፣ ብፁዓን ናቸው። ኀጢአቱን፣ ጌታ ከቶ የማይቈጥርበት ሰው ምስጉን ነው።” ይህ ብፅዕና ለተገረዙት ብቻ ነው ወይስ ላልተገረዙትም? የአብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት ብለናል። ታዲያ እንዴት ተቈጠረለት? ከተገረዘ በኋላ ነው ወይስ ከመገረዙ በፊት? የተቈጠረለት ከተገረዘ በኋላ ሳይሆን ከመገረዙ በፊት ነው። ሳይገረዝ በነበረው እምነት ላገኘው ጽድቅ፣ የመገረዝን ምልክት ይኸውም የጽድቅን ማኅተም ተቀበለ፤ ስለዚህ ለሚያምኑ ነገር ግን ላልተገረዙት ጽድቅ ይቈጠርላቸው ዘንድ የሁሉ አባት ነው። እርሱ ለተገረዙትም አባት ነው፤ መገረዝ ብቻ ሳይሆን፣ አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ሁሉ ነው። እርሱ የዓለም ወራሽ እንዲሆን አብርሃምና ዘሩ ተስፋን የተቀበሉት በሕግ በኩል አልነበረም፤ ነገር ግን በእምነት ከሆነው ጽድቅ ነው።
ሮሜ 4:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ዓመፃቸው የተሰረየላቸው ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው ብፁዓን ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው። እንግዲህ ይህ ብፅዕና ስለ መገረዝ ተነገረ? ወይስ ደግሞ ስለ አለመገረዝ? እምነቱ ለአብርሃም ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። እንዴት ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ተገርዞስ አይደለም፥ ሳይገረዝ ነበር እንጂ። ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የሆነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤ ይህም እነርሱ ደግሞ ጻድቃን ሆነው ይቆጠሩ ዘንድ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ አባት እንዲሆን ነው፥ ለተገረዙትም አባት እንዲሆን ነው፤ ይኸውም ለተገረዙት ብቻ አይደለም ነገር ግን አባታችን አብርሃም ሳይገረዝ የነበረውን የእምነቱን ፍለጋ ደግሞ ለሚከተሉ ነው። የዓለምም ወራሽ እንዲሆን ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም።
ሮሜ 4:7-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
“በደላቸው ይቅር የተባለላቸውና ኃጢአታቸው የተደመሰሰላቸው ሰዎች የተባረኩ ናቸው! ጌታ ኃጢአቱን የማይቈጥርበት ሰው የተባረከ ነው!” ታዲያ፥ ዳዊት የተናገረው ይህ በረከት ለተገረዙት ብቻ ነውን? ወይስ ላልተገረዙትም? ላልተገረዙትም ነው፤ “አብርሃም በእግዚአብሔር ስላመነ እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቈጠረለት” ብለናል። እንግዲህ አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ የተቈጠረለት መቼ ነው? ከመገረዙ በፊት ነውን ወይስ ከተገረዘ በኋላ? ከመገረዙ በፊት ነው እንጂ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። አብርሃም ገና ከመገረዙ በፊት እምነቱ ጽድቅ ሆኖ እንደ ተቈጠረለት ማረጋገጫ ምልክት እንዲሆነው ተገረዘ፤ ስለዚህ አብርሃም፥ ሳይገረዙ ለሚያምኑና እምነታቸው ጽድቅ ሆኖ ለሚቈጠርላቸው ሁሉ አባት ነው። እንዲሁም አብርሃም ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት አባት የሆነበትም ምክንያት በመገረዛቸው ብቻ ሳይሆን እርሱ ከመገረዙ በፊት የነበረውን እምነት በመከተላቸውም ጭምር ነው። ለአብርሃምና ለዘሩ ዓለምን እንደሚወርስ እግዚአብሔር ተስፋ የሰጠው በእምነት ስላገኘው ጽድቅ ነው እንጂ ሕግን በመፈጸሙ አይደለም።
ሮሜ 4:7-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
“መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፥ ኃጢአታቸውም የተከደነላቸው የተባረኩ ናቸው፤ ጌታ ኃጢአቱን የማይቆጥርበት ሰው የተባረከ ነው።” እንግዲህ ይህ መባረክ በመገረዝ መጣን? ወይስ ደግሞ ባለመገረዝ? አብርሃም እምነቱ ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት እንላለንና። እንዴት ታዲያ ተቆጠረለት? ተገርዞ ሳለ ነውን? ወይስ ሳይገረዝ? ሳይገረዝ ነበር እንጂ፤ ከተገረዘ በኋላ አይደለም። ሳይገረዝም በእምነቱ ባገኘው የጽድቅ ማኅተም፥ መገረዝን እንደ ምልክት ተቀበለ፤ ሳይገረዙ ለሚያምኑ ሁሉ፥ ለእነርሱም ጽድቅ ሆኖ እንዲቆጠርላቸው አባት ነውና፤ ለተገረዙትም አባት ነው፤ ለተገረዙት ብቻ ሳይሆን፥ ነገር ግን አባታችን አብርሃም ከመገረዙ በፊት የነበረውን የእምነቱን ፈለግ ለሚከተሉ ጭምር ነው። ዓለምን እንዲወርስ ለአብርሃምና ለዘሩ የተሰጠው የተስፋ ቃል በእምነት ጽድቅ ነው እንጂ በሕግ አይደለም።