ሮሜ 3:20-31
ሮሜ 3:20-31 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከኦሪት የተነሣ ኀጢአት ስለ ታወቀች ሰው ሁሉ የኦሪትን ሥርዐት በመፈጸም በእግዚአብሔር ፊት አይጸድቅም። አሁን ግን በኦሪትና በነቢያት የተመሰከረላት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ኦሪት ተገለጠች። የሚያምኑበት ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን በእግዚአብሔር ዘንድ ይጸድቃሉ። በዚህም ልዩነት የለም፤ ሁሉም ፈጽመው በድለዋልና፤ እግዚአብሔርን ማክበርንም ትተዋልና። ጽድቅ ግን በኢየሱስ ክርስቶስም ቤዛነት ያለ ዋጋ በእርሱ ቸርነት ሆነ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ፥ በደሙም የሆነ ማስተስረያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም ከጥንት ጀምሮ በበደሉት ላይ ጽድቁን ይገልጥ ዘንድ ነው። እግዚአብሔር ታጋሽ በመሆኑ፥ እሺ በማለቱም እርሱ ጻድቅ እንደ ሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም የሚያምኑትን እንደሚያጸድቃቸው ዛሬ ያውቁ ዘንድ ነው። ትምክሕት ወዴት አለ? እርሱ ቀርቶአል፤ በየትናውስ ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው የኦሪትን ሥራ ሳይሠራ በእምነት እንዲጸድቅ እናውቃለንና። በውኑ እግዚአብሔር ለአይሁድ ለብቻቸው ነውን? ለአሕዛብስ አይደለምን? አዎን፥ ለአሕዛብም ነው፤ የተገዘረውን በእምነት የሚያጸድቅ፥ ያልተገዘረውንም በእምነት የሚያጸድቀው እርሱ አንዱ እግዚአብሔር ነውና። እንግዲህ በእምነት ኦሪትን እንሽራለን? አንሽርም፤ ኦሪትን እናጸናለን እንጂ።
ሮሜ 3:20-31 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስለዚህ ሕግን በመጠበቅ ማንም በእርሱ ፊት ጻድቅ ነው ሊባል አይችልም፤ ይልቁንም በሕግ አማካይነት ኀጢአትን እንገነዘባለን። አሁን ግን ሕግና ነቢያት የመሰከሩለት፣ ከሕግ ውጭ የሆነ፣ የእግዚአብሔር ጽድቅ ተገልጧል። ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ኢየሱስ ክርስቶስን በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው። ልዩነት የለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ጸድቀዋል፤ በደሙም በሆነው እምነት፣ እግዚአብሔር የማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል፤ ይህንም ያደረገው ቀድሞ የተፈጸመውን ኀጢአት ሳይቀጣ በትዕግሥት በማለፍ ጽድቁን ለማሳየት ነው፤ በአሁኑ ዘመን ይህን ያደረገው፣ ጽድቁን ይኸውም እርሱ ራሱ ጻድቅ ሆኖ፣ በኢየሱስ የሚያምነውን የሚያጸድቅ መሆኑን ለማሳየት ነው። ታዲያ ትምክሕት ወዴት ነው? እርሱማ ቀርቷል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፤ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ማንም ሰው ሕግን በመፈጸም ሳይሆን፣ በእምነት እንደሚጸድቅ እናረጋግጣለን። እግዚአብሔር የአይሁድ አምላክ ብቻ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን፤ የአሕዛብም አምላክ ነው፤ የተገረዘውን በእምነት፣ ያልተገረዘውንም በዚያው እምነት የሚያጸድቅ አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነውና። ታዲያ እንዲህ ከሆነ ከእምነት የተነሣ ሕግን ዋጋ የሌለው እናደርግ ይሆን? ፈጽሞ አይደረግም፤ ሕጉን እናጸናለን እንጂ።
ሮሜ 3:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ይህም የሕግን ሥራ በመሥራት ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት ስለማይጸድቅ ነው፤ ኃጢአት በሕግ ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፥ እርሱም፥ ለሚያምኑ ሁሉ የሆነ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ጽድቅ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ አቆመው፤ ይህም በፊት የተደረገውን ኃጢአት በእግዚአብሔር ችሎታ ስለ መተው ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው፥ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን ያሳይ ዘንድ ነው። ትምክህት እንግዲህ ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ ነው? በሥራ ሕግ ነውን? አይደለም፥ በእምነት ሕግ ነው እንጂ። ሰው ያለ ሕግ ሥራ በእምነት እንዲጸድቅ እንቆጥራለንና። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ ደግሞ አምላክ አይደለምን? አዎን፥ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አምላክ አንድ ስለ ሆነ የአሕዛብ ደግሞ አምላክ ነው። እንግዲህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? አይደለም፤ ሕግን እናጸናለን እንጂ።
ሮሜ 3:20-31 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ስለዚህ ማንም ሰው በእግዚአብሔር ፊት፥ ሕግን በመፈጸም አይጸድቅም፤ ሕግ የሚያሳየው ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ መሆኑን ነው። አሁን ግን እግዚአብሔር ሰዎችን የሚያጸድቅበት መንገድ ያለ ሕግ መሆኑ ተገልጦአል፤ ይህም በሙሴ ሕግና በነቢያት ተመስክሮአል። ስለዚህ እግዚአብሔር ምንም ልዩነት ሳያደርግ በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሁሉ ጽድቅን ይሰጣል። ሰዎች ሁሉ ኃጢአት ሠርተዋል፤ እግዚአብሔር የሰጣቸውንም ክብር አጥተዋል። ስለዚህ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመው በአዳኝነት ሥራ በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይጸድቃሉ። እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስን መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበው በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ በደሙ የኃጢአታቸውን ስርየት እንዲያገኙ ነው፤ እግዚአብሔር ይህን ማድረጉ በትዕግሥቱ የቀድሞውን ኃጢአት እንዳልነበረ በማድረግ የራሱን ትክክለኛ ፍርድ ለመግለጥ ነው። በአሁኑም ዘመን እግዚአብሔር ራሱ ጻድቅ መሆኑን የሚያሳየው በኢየሱስ የሚያምኑትን ሁሉ በማጽደቅ ነው። እንግዲህ የምንመካበት ነገር ምን አለ? በምንም አንመካም! የማንመካበትስ ምክንያት ምንድን ነው? ሕግን ስለምንፈጽም ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በእምነት ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን የሚያጸድቀው፥ ሰው የሕግን ሥራ በመፈጸሙ ሳይሆን በእምነት መሆኑን እንገነዘባለን። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? በእርግጥ የአሕዛብም አምላክ ነው። እግዚአብሔር አንድ ነው፤ አይሁድንም ሆነ አሕዛብን በእምነት የሚያጸድቅ እርሱ ነው። ታዲያ፥ በእምነት ምክንያት ሕግን እንሽራለን ማለት ነውን? አይደለም፤ ይልቅስ ሕግን አጥብቀን እንይዛለን።
ሮሜ 3:20-31 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ምክንያቱም በሕግ ሥራ ሥጋ የለበሰ ሁሉ በእርሱ ፊት አይጸድቅም፤ በሕግ አማካኝነት ኃጢአት ይታወቃልና። አሁን ግን በሕግና በነቢያት የተመሰከረለት የእግዚአብሔር ጽድቅ ያለ ሕግ ተገልጦአል፤ ይህ የእግዚአብሔር ጽድቅ ለሚያምኑ ሁሉ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ባለን እምነት የሚገኝ ነው፤ ልዩነት የለምና፤ ሁሉም ኃጢአትን ሠርተዋልና፤ የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲሁ በጸጋው ይጸድቃሉ። እርሱንም እግዚአብሔር በእምነት የሚገኝ በደሙም የሆነ ማስተስሪያ አድርጎ ያቀረበው ነው፤ ይህም በእግዚአብሔር ትዕግስት በፊት የተደረገውን ኃጢአት በመተው ጽድቁን እንዲያሳይ ነው፤ ራሱም ጻድቅ እንዲሆን በኢየሱስም የሚያምነውን እንዲያጸድቅ አሁን በዚህ ዘመን ጽድቁን እንዲያሳይ ነው። ስለዚህ ትምክህት ወዴት ነው? እርሱ ቀርቶአል። በየትኛው ሕግ? በሥራ ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን በእምነት ሕግ ነው። ሰው ሕግ ከሚያዘው ሥራ ውጭ በእምነት እንደሚጸድቅ እናምናለንና። ወይስ እግዚአብሔር የአይሁድ ብቻ አምላክ ነውን? የአሕዛብስ አምላክ አይደለምን? አዎን የአሕዛብም አምላክ ነው፤ የተገረዘን ስለ እምነት ያልተገረዘንም በእምነት የሚያጸድቅ አንድ አምላክ አለና። ስለዚህ ሕግን በእምነት እንሽራለንን? በጭራሽ! ነገር ግን ሕግን እናጸናለን።