ሮሜ 16:17-27
ሮሜ 16:17-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፥ መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን እንድታውቁባቸው እማልዳችኋለሁ፤ ከእነርሱም ተለዩ፤ እነርሱ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ያይደለ ለሆዳቸው ይገዛሉና፤ በነገር ማታለልና በማለዛዘብም የብዙዎች የዋሃንን ልብ ያስታሉ፤ መታዘዛችሁም በሁሉ ዘንድ ተሰምቶአል፤ እኔም በእናንተ ደስ ይለናል፤ ለመልካም ነገር ጠቢባን፥ ለክፉ ነገርም የዋሃን እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። የሰላም አምላክም ፈጥኖ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ይቀጥቅጠው፤ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን፤ አሜን። ከእኔ ጋር በሥራ የሚተባበረው ጢሞቴዎስም፥ ከዘመዶች ወገን የሚሆኑ ሉቅዮስም፥ ኢያሶንም፥ ሱሲ ጴጥሮስም ሰላም ይሉአችኋል። ይህችን መልእክት የጻፍኋት እኔ ጤርጥዮስ በጌታችን ስም ሰላም እላችኋለሁ። እኔንና አብያተ ክርስቲያናትን ሁሉ በእንግድነት የተቀበለ ጋይዮስም ሰላም ብሎአችኋል፤ የከተማው መጋቢ አርስጦስና ወንድማችን ቁአስጥሮስም ሰላም ብለዋችኋል። ከዓለም አስቀድሞ ምሥጢሩ ተሰውሮ ስለ ነበረ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በማስተምራት ትምህርት ላይ ሊያጸናችሁ የሚችለው እርሱ እግዚአብሔር ነው። ይህም በነቢያት ቃልና የዘለዓለም ገዥ በሚሆን በእግዚአብሔር ትእዛዝ በዚህ ወራት ተገለጠ፤ አሕዛብ ሁሉ ይህን ሰምተውና ዐውቀው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ያምኑ ዘንድ። ብቻውን ጠቢብ ለሆነው ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ አሜን። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። በቆሮንቶስ ተጽፋ ለክንክራኦስ ማኅበረ ክርስቲያን በምትላላከው በፌቤን እጅ ወደ ሮሜ ሰዎች የተላከችው መልእክት ተፈጸመች። ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን ለዘለዓለሙ አሜን።
ሮሜ 16:17-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ወንድሞች ሆይ፤ መለያየትን ከሚፈጥሩትና የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም በጕዟችሁ መሰናክል ከሚያደርጉት እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ። እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የሚያገለግሉት ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ሳይሆን የራሳቸውን ሆድ ነው። በለሰለሰ አንደበታቸውና በሽንገላ የዋሆችን ያታልላሉ። የእናንተን ታዛዥነት ሁሉም ሰምተዋል፤ በዚህም እኔ እጅግ ተደስቻለሁ። ሆኖም በጎ ስለ ሆነው ነገር ጥበበኞች፣ ክፉ ስለ ሆነውም የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። የሰላም አምላክ፣ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋራ ይሁን። ዐብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ፣ እንዲሁም ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስ፣ ኢያሶንና ሱሲጴጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍሁት እኔ ጤርጥዮስ፣ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። በመልካም መስተንግዶው እኔና በዚህ የምትገኘዋ መላዋ ቤተ ክርስቲያን ደስ የምንሰኝበት ጋይዮስ፣ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማዪቱ ግምጃ ቤት ሹም የሆነው ኤርስጦስ፣ ወንድማችንም ቍአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። [የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋራ ይሁን። አሜን።] በዘላለማዊ አምላክ ትእዛዝ ሕዝቦች ሁሉ አምነው እንዲታዘዙ፣ በነቢያት መጻሕፍት አሁን በተገለጠው፣ ላለፉት ረዥም ዘመናት ተሰውሮ በነበረው ምስጢር መገለጥ መሠረት፣ በአስተማርሁት ወንጌልና በኢየሱስ ክርስቶስ መሰበክ ሊያጸናችሁ ለሚችለው፣ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነ አምላክ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለዘላለም ክብር ይሁን! አሜን።
ሮሜ 16:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ፤ እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ። መታዘዛችሁ ለሁሉ ተወርቶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለበጎ ነገር ጥበበኞች ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ። የሰላምም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ በታች ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አብሮኝ የሚሠራ ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉቂዮስና ኢያሶን ሱሲጴጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። የእኔና የቤተ ክርስቲያን ሁሉ አስተናጋጅ ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው መጋቢ ኤርስጦስ ወንድማችንም ቁአስጥሮስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ እንደ ወንጌል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስም እንደ ተሰበከ፥ ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው አሁን ግን የታየው በነቢያትም መጻሕፍት የዘላለም እግዚአብሔር እንደ አዘዘ ለእምነት መታዘዝ ይሆን ዘንድ ለአሕዛብ ሁሉ የታወቀው ምሥጢር እንደ ተገለጠ መጠን ሊያበረታችሁ ለሚችለው፥ ብቻውን ጥበብ ላለው ለእግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ዘላለም ድረስ ክብር ይሁን፤ አሜን።
ሮሜ 16:17-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ወንድሞች ሆይ! ለተቀበላችሁት ትምህርት ተቃዋሚዎች በመሆን በመካከላችሁ መከፋፈልንና ችግርን ከሚያመጡ ሰዎች ተጠንቀቁ፤ ከእነርሱም ራቁ! እንደእነዚህ ዐይነቶቹ ሰዎች ራሳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉም። በለዘቡና በሚያቈላምጡ ቃላት የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። ለወንጌል ቃል ታዛዦች መሆናችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ ስለ ታወቀ ደስ ያለኝ ቢሆንም፥ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር ግን የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። ይህን ብታደርጉ የሰላም አምላክ ፈጥኖ ሰይጣንን በእግራችሁ ሥር ይቀጠቅጥላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። የሥራ ተባባሪዬ ጢሞቴዎስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ እንዲሁም አይሁድ ዘመዶቼ የሆኑት ሉቂዮስና ኢያሶን ሶሲጳጥሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍኩ እኔም ጠርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። እኔንና በዚህ ያለውን መላ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋይዮስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል፤ የከተማይቱ በጅሮንድ የሆነው ኤራስጦስ፥ ወንድማችንም ቋርጦስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። [ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን! አሜን።] እኔ በማበሥረው የምሥራች ቃል ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በሚተላለፈው መልእክትና ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተደብቆ በቈየው፥ አሁን ግን በተገለጠው የእውነት ምሥጢር አማካይነት እርሱ በእምነታችሁ እንድትቆሙ ሊያደርጋችሁ ይችላል። አሁን ግን ይህ እውነት ተገልጦአል፤ በዘለዓለማዊው አምላክ ትእዛዝ ሁሉም አምነው እንዲታዘዙ በነቢያት መጻሕፍት አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ እንዲያውቁት ተደርጓል። እርሱ ብቻ ጥበብ ላለው ለአንድ አምላክ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ምስጋና ይሁን! አሜን።
ሮሜ 16:17-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ወንድሞች ሆይ! ከሚለያዩትና እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት በመቃወም መሰናክል ከሚያደርጉ ሰዎች እንድትጠነቀቁ አሳስባችኋለሁ፤ ከእነርሱም ራቁ፤ እንደ እነዚህ ያሉት ሰዎች የገዛ ሆዳቸውን እንጂ ጌታችንን ክርስቶስን አያገለግሉምና፤ በሚያሳምን ንግግርና በሽንገላ የየዋሆችን ልብ ያታልላሉ። መታዘዛችሁ በሁሉም ሰው ዘንድ ደርሶአልና፤ እንግዲህ በእናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ለመልካም ነገር ጥበበኞች ለክፉ ነገር የዋሆች እንድትሆኑ እፈልጋለሁ። የሰላም አምላክ ሰይጣንን ከእግራችሁ ሥር ፈጥኖ ይቀጠቅጠዋል። የጌታችን የኢየሱስ ጸጋ ከእናንተ ጋር ይሁን። አብሮኝ የሚሠራው ጢሞቴዎስ ዘመዶቼም ሉኪዮስ፥ ኢያሶንና ሶሲፓትሮስም ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ቴርትዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ። እኔንና መላዋ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስተናግደው ጋዩስ ሰላምታ ያቀርብላችኋል። የከተማው ገንዘብ ያዥ ኤራስቶስ፥ ወንድማችንም ኳርቶስ ሰላምታ ያቀርቡላችኋል። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። እንግዲህ በወንጌሌ፥ በኢየሱስ ክርስቶስም ስብከት፥ ለዘመናት ተሰውሮ በነበረው የምሥጢር ግልፀት ሊያጸናችሁ ለሚችለው ለእርሱ፥ አሁን ግን ተገለጠ፤ በዘላለማዊው አምላክ ትእዛዝ፥ አሕዛብ ሁሉ ለእምነት እንዲታዘዙ፥ በነቢያት መጻሕፍት እንዲያውቁት ተደርጓል፤ እርሱ ብቻ ጥበበኛ ለሆነው አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ለዘለዓለም ክብር ይሁን፤ አሜን።