ሮሜ 12:10-18
ሮሜ 12:10-18 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ። ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ። በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ። ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር ዕዘኑ። እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።
ሮሜ 12:10-18 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ መምህሮቻችሁንም አክብሩ። ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ። በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልንም አዘውትሩ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ። እርስ በርሳችሁም በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እና ዐዋቆች ነን አትበሉ። ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ። ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።
ሮሜ 12:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።
ሮሜ 12:10-18 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ፤ ሳትታክቱ የጋለ መንፈስን ተከትላችሁ ጌታን አገልግሉ። በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ጊዜ ታገሡ፤ ሁልጊዜ ጸልዩ። አማኞች ወንድሞችን በችግራቸው እርዱ፤ በእንግድነት የሚመጡትንም ተቀበሉ። የሚያሳድዱአችሁንም መርቁ፤ መርቁአቸው እንጂ አትርገሙአቸው። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ራሳችሁን ከፍ ከማድረግ ይልቅ ትዕቢትን አስወግዳችሁ ከድኾች ጋር በአንድነት ኑሩ፤ በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አድርጉ እንጂ፥ ሰዎች ክፉ ነገር ሲያደርጉባችሁ፥ እናንተም መልሳችሁ ክፉ ነገር አታድርጉባቸው። የሚቻላችሁ ቢሆን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርጉ።
ሮሜ 12:10-18 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እርስ በእርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ጌታን አገልግሉ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ ነገር ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፤ ነገር ግን የተናቁትን ቅረቡ። በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። ለማንም በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አስቡ። ቢቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።