ሮሜ 12:1-21
ሮሜ 12:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ፤ ሰውነታችሁን ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሕያው መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም እንደ ባለ አእምሮ የምታቀርቡት አምልኳችሁ ነው። መልካም፣ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በአእምሯችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ በሰጣችሁ እምነት መጠን ራሳችሁን በአግባቡ መዝኑ እንጂ፣ ከሆናችሁት በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ እያንዳንዳችሁን እመክራለሁ። እያንዳንዳችን በአንዱ አካላችን ብዙ ብልቶች እንዳሉን፣ እነዚህም ብልቶች አንድ ዐይነት ተግባር እንደሌላቸው ሁሉ፣ እንዲሁም እኛ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን። እያንዳንዳችንም የሌላው ብልት ነን። እንደ ተሰጠን ጸጋ የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ለአንዱ የተሰጠው ስጦታ ትንቢት መናገር ከሆነ፣ እንደ እምነቱ መጠን ይናገር። ማገልገል ቢሆን ያገልግል፤ ማስተማርም ከሆነ ያስተምር፤ መምከር ከሆነ ይምከር፤ ለሌላቸው መለገስ ከሆነም አብዝቶ ይለግስ፤ ማስተዳደር ከሆነም በትጋት ያስተዳድር፤ ምሕረት ማድረግ ከሆነም በደስታ ይማር። ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ክፉ የሆነውን ሁሉ ተጸየፉ፤ በጎ ከሆነው ነገር ጋር ተቈራኙ። እርስ በርሳችሁ በወንድማማች መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ አንዱ ሌላውን ከራሱ በማስበለጥ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ። ጌታን ለማገልገል በመንፈስ የጋላችሁ ሁኑ እንጂ ከዚህ ትጋት ወደ ኋላ አትበሉ። በተስፋ ደስተኞች ሁኑ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ። ችግረኛ ለሆኑ ቅዱሳን ካላችሁ አካፍሉ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዷችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያዝኑም ጋር ዕዘኑ። እርስ በርሳችሁ በመስማማት ኑሩ። ዝቅተኛ ኑሮ ውስጥ ካሉ ጋር አብራችሁ ለመሆን ፍቀዱ እንጂ አትኵራሩ፤ በራሳችሁም አትመኩ። ለማንም ክፉን በክፉ አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ትጉ። ቢቻላችሁስ በበኩላችሁ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወዳጆቼ ሆይ፤ ለእግዚአብሔር ቍጣ ፈንታ ስጡ እንጂ አትበቀሉ፤ “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፏልና። ይልቁንስ፣ “ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው። ይህን በማድረግህም የእሳት ፍም በራሱ ላይ ትከምራለህ።” ክፉን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
ሮሜ 12:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፥ እርሱም ለአእምሮ የሚመች አገልግሎታችሁ ነው። የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ የእምነትን መጠን እንዳካፈለው፥ እንደ ባለ አእምሮ እንዲያስብ እንጂ ማሰብ ከሚገባው አልፎ በትዕቢት እንዳያስብ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ በተሰጠኝ ጸጋ እናገራለሁ። በአንድ አካል ብዙ ብልቶች እንዳሉን፥ የብልቶቹም ሁሉ ሥራ አንድ እንዳይደለ፥ እንዲሁ ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው ብልቶች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ ልዩ ልዩ ስጦታ አለን፤ ትንቢት ቢሆን እንደ እምነታችን መጠን ትንቢት እንናገር፤ አገልግሎት ቢሆን በአገልግሎታችን እንትጋ፤ የሚያስተምርም ቢሆን በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም ቢሆን በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥ በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛ በትጋት ይግዛ፤ የሚምር በደስታ ይማር። ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን። ክፉውን ነገር ተጸየፉት፤ ከበጎ ነገር ጋር ተባበሩ፤ በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ለመቀበል ትጉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፥ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፥ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፥ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ። ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ። ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ተወዳጆች ሆይ፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ግን ቢራብ አብላው፤ ቢጠማ አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።
ሮሜ 12:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ወንድሞቻችን፥ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ፥ ደስ የሚያሰኝም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ። ይህም በዕውቀት የሚሆን አገልግሎታችሁ ነው። ይህን ዓለም አትምሰሉ፤ ልባችሁንም አድሱ፤ እግዚአብሔር የሚወደውን መልካሙንና እውነቱን፥ ፍጹሙንም መርምሩ። በተሰጠኝ በእግዚአብሔር ጸጋ ሁላችሁም እንዳትታበዩ እነግራችኋለሁ፤ ራሳችሁን ከዝሙት የምታነጹበትን ዐስቡ እንጂ ትዕቢትን አታስቡ፤ ሁሉም እንደ እምነቱ መጠን እግዚአብሔር እንደ አደለው ይኑር። በአንዱ ሰውነታችን ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉ፥ ሥራቸውም ልዩ ልዩ እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ሁላችን ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤ እርስ በርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው አካሎች ነን፤ ስጦታውም ልዩ ልዩ ነው፤ እግዚአብሔርም በሰጠን ጸጋ መጠን ልዩ ልዩ ስጦታ አለን። ትንቢት የሚናገር እንደ እምነቱ መጠን ይናገር። የሚያገለግልም በማገልገሉ ይትጋ፤ የሚያስተምርም በማስተማሩ ይትጋ፤ የሚመክርም በመምከሩ ይትጋ፤ የሚሰጥም በልግስና ይስጥ፤ የሚገዛም በትጋት ይግዛ፤ የሚመጸውትም በደስታ ይመጽውት። ፍቅራችሁ ያለ ግብዝነት ይሁን፤ ከክፉ ራቁ፤ በጎውንም ያዙ፤ ለጽድቅ አድሉ፤ እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ ተዋደዱ፤ የምትራሩም ሁኑ፤ እርስ በርሳችሁ ተከባበሩ፤ መምህሮቻችሁንም አክብሩ። ለሥራ ከመትጋት አትስነፉ፤ በመንፈስ ሕያዋን ሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ ለጸሎት ትጉ። በችግራቸው ቅዱሳንን ለመርዳት ተባበሩ፤ እንግዳ መቀበልንም አዘውትሩ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ። እርስ በርሳችሁም በአንድ ዐሳብ ተስማሙ፤ ትዕቢትን ግን አታስቡ፤ ራሱን የሚያዋርደውንም ሰው ምሰሉ፤ እና ዐዋቆች ነን አትበሉ። ክፉ ላደረገባችሁም ክፉ አትመልሱለት፤ በሰው ሁሉ ፊት በጎውን ተነጋገሩ። ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። ወንድሞቻችን፥ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ቍጣን አሳልፏት፥ “እኔ እበቀላለሁ፤ እኔ ብድራትን እከፍላለሁ ይላል እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአልና። ጠላትህ ቢራብ አብላው፤ ቢጠማም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ የእሳት ፍሕም በራሱ ላይ ትከምራለህ። ክፉውን በመልካም ሥራ ድል ንሣው እንጂ ክፉውን በክፉ ድል አትንሣው።
ሮሜ 12:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እንግዲህ ወንድሞቼ ሆይ! እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ፥ ሕያውና የተቀደሰ መሥዋዕት አድርጋችሁ ሁለንተናችሁን እንድታቀርቡ በመሐሪው በእግዚአብሔር ስም እለምናችኋለሁ፤ ይህም ማቅረብ የሚገባችሁ ቅንነት ያለው እውነተኛ የእግዚአብሔር አገልግሎት ነው። መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ አእምሮአችሁን በማደስ ሕይወታችሁ ይለወጥ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉት። ደግሞም እያንዳንዳችሁ እግዚአብሔር በሰጣችሁ እምነት መጠን በትሕትና አስቡ እንጂ ከሚገባችሁ በላይ ስለ ራሳችሁ በትዕቢት አታስቡ ብዬ በተሰጠኝ ጸጋ እነግራችኋለሁ። በአንዱ አካላችን ብዙ ክፍሎች አሉ፤ እያንዳንዱም የአካል ክፍል የተለየ ሥራ አለው። እንዲሁም እኛ ብዙዎች ሆነን ሳለ በክርስቶስ አንድ አካል ነን፤ የአንድ አካል ክፍሎች እንደ መሆናችንም እርስ በርሳችን ተጣምረናል። ስለዚህ እግዚአብሔር በጸጋው የሰጠንን ልዩ ልዩ ስጦታ በሥራ ላይ እናውል፤ ስጦታችን የእግዚአብሔርን ቃል ማወጅ ከሆነ በእምነታችን መጠን የእግዚአብሔርን ቃል እናውጅ። ስጦታችን ሌሎችን ማገልገል ከሆነ በትጋት እናገልግል፤ ስጦታችን ማስተማር ከሆነ በሚገባ እናስተምር፤ ስጦታችን መምከር ከሆነ እንምከር፤ ስጦታችን መለገሥ ከሆነ ከልብ እንለግሥ፤ ስጦታችን ማስተዳደር ከሆነ በትጋት እናስተዳድር፤ ስጦታችን ርኅራኄ ማድረግ ከሆነ ይህንኑ በደስታ እናድርግ። ግብዝነት የሌለበት እውነተኛ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ክፉውን ነገር ጥሉ፤ መልካሙን ነገር ተከተሉ። እርስ በርሳችሁ በወንድማማችነት ፍቅር ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ለመከባበርም ተሽቀዳደሙ፤ ሳትታክቱ የጋለ መንፈስን ተከትላችሁ ጌታን አገልግሉ። በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ጊዜ ታገሡ፤ ሁልጊዜ ጸልዩ። አማኞች ወንድሞችን በችግራቸው እርዱ፤ በእንግድነት የሚመጡትንም ተቀበሉ። የሚያሳድዱአችሁንም መርቁ፤ መርቁአቸው እንጂ አትርገሙአቸው። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱም ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማምታችሁ ኑሩ፤ ራሳችሁን ከፍ ከማድረግ ይልቅ ትዕቢትን አስወግዳችሁ ከድኾች ጋር በአንድነት ኑሩ፤ በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አድርጉ እንጂ፥ ሰዎች ክፉ ነገር ሲያደርጉባችሁ፥ እናንተም መልሳችሁ ክፉ ነገር አታድርጉባቸው። የሚቻላችሁ ቢሆን ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የሚያስፈልገውን ሁሉ አድርጉ። ወዳጆቼ ሆይ! ቊጣን ለእግዚአብሔር ተዉ እንጂ ራሳችሁ አትበቀሉ፤ “የምበቀልና የበቀልንም ብድራት የምከፍል እኔ ነኝ ይላል ጌታ እግዚአብሔር” ተብሎ ተጽፎአል። ስለዚህ ከመበቀል ይልቅ ጠላትህን ቢርበው አብላው፤ ቢጠማውም አጠጣው፤ ይህን ብታደርግ በዕፍረት እሳት ታቃጥለዋለህ። ስለዚህ ክፉውን ነገር በመልካም ነገር አሸንፍ እንጂ በክፉ ነገር አትሸነፍ።
ሮሜ 12:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
እንግዲህ ወንድሞች ሆይ! ሰውነታችሁን ሕያው መሥዋዕት፥ ቅዱስና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ አድርጋችሁ እንድታቀርቡ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ፤ ይህም መንፈሳዊ አገልግሎታችሁ ነው። መልካም፥ ደስ የሚያሰኝና ፍጹም የሆነውን የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ ለማወቅ በአእምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችሁ እንደሰጣችሁ እምነት መጠን፥ በረጋ አእምሮ አስቡ እንጂ ማሰብ ከሚገባችሁ በላይ ራሳችሁን ከፍ አድርጋችሁ እንዳታስቡ በተሰጠኝ ጸጋ በመካከላችሁ ላለው ለእያንዳንዱ እናገራለሁና። በአንድ አካል ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉን፥ የሰውነት ክፍሎቹም ሥራ አንድ እንዳልሆነ ሁሉ፥ እንዲሁም ብዙዎች ስንሆን በክርስቶስ አንድ አካል ነን፥ እርስ በእርሳችንም እያንዳንዳችን የሌላው የሰውነት ክፍሎች ነን። እንደ ተሰጠንም ጸጋ መጠን የተለያዩ ስጦታዎች አሉን፤ ትንቢት ከሆነ እንደ እምነት መጠን መናገር፤ አገልግሎት ከሆነ ማገልገል፤ ማስተማር ከሆነ ማስተማር፤ ምክር ከሆነ መምከር፤ መስጠት ከሆነ በልግስና መስጠት፤ ማስተዳደር ከሆነ በትጋት ማስተዳደር፤ ምሕረት ማድረግ ከሆነ በደስታ መማር። ፍቅር እውነተኛ ይሁን፤ ክፉውን ነገር ተጸየፉ፥ መልካም የሆነው ነገር አጥብቃችሁ ያዙ፤ እርስ በእርሳችሁ በወንድማማችነት መዋደድ አጥብቃችሁ ተዋደዱ፤ እርስ በርሳችሁ ይበልጥ ተከባበሩ፤ ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ጌታን አገልግሉ፤ በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ታገሡ፤ በጸሎት ጽኑ፤ ቅዱሳንን በሚያስፈልጋቸው እርዱ፤ እንግዶችን ተቀበሉ። የሚያሳድዱአችሁን መርቁ፤ መርቁ እንጂ አትርገሙ። ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ። እርስ በርሳችሁ በአንድ ነገር ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፤ ነገር ግን የተናቁትን ቅረቡ። በራሳችሁ ዐዋቂዎች ነን አትበሉ። ለማንም በክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን ነገር አስቡ። ቢቻላችሁ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ። “በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራቱን እመልሳለሁ፤ ይላል ጌታ” ተብሎ ተጽፎአልና፥ ተወዳጆች ሆይ! ራሳችሁ አትበቀሉ፤ ለቁጣው ቦታ ስጡ እንጂ። ነገር ግን ጠላትህ ቢርበው አብላው፤ ቢጠማው አጠጣው፤ ይህን በማድረግህ በራሱ ላይ የእሳት ፍም ትከምራለህና። ክፉውን በመልካም አሸንፍ እንጂ በክፉ አትሸነፍ።