ሮሜ 11:11-16
ሮሜ 11:11-16 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እንግዲህ እላለሁ፤ ሊወድቁ ተሰናከሉን? አይደለም፤ ነገር ግን እስራኤል ይቀኑ ዘንድ እነርሱ በመሰናከላቸው ለአሕዛብ ድኅነት ሆነ። የእነርሱ መሰናከል ለዓለም ባለጸግነት፥ በደላቸውም ለአሕዛብ ባለጸግነት ከሆነ ፍጹምነታቸውማ እንዴት በሆነ ነበር? ለእናንተ ለአሕዛብ እናገራለሁ፤ እኔ ለአሕዛብ ሐዋርያቸው እንደ መሆኔ መጠን መልእክቴን አከብራታለሁ። ይህም በዚህ ዘመዶችን አስቀናቸው እንደ ሆነ፥ ከእነርሱ ወገን የሆኑትንም አድን እንደ ሆነ ነው። የእነርሱ መውጣት ለዓለም ዕርቅ ከሆነ ይልቁንም መመለሳቸው ምን ይሆን? ከሙታን በመነሣት የሚገኝ ሕይወት ነው። እርሾው ቅዱስ ከሆነ ቡሆውም እንዲሁ ቅዱስ ነው፤ ሥርዋ ቅዱስ ከሆነም ቅርንጫፎችዋ እንዲሁ ቅዱሳን ይሆናሉ።
ሮሜ 11:11-16 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ተመልሰው እስከማይድኑ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እንደ ገና እጠይቃለሁ፤ ከቶ አይሆንም! ይልቁንም እስራኤልን ለማስቀናት ሲባል በእነርሱ መተላለፍ ምክንያት ድነት ለአሕዛብ መጥቷል። ነገር ግን የእነርሱ መተላለፍ ለዓለም በረከት ከሆነ፣ ውድቀታቸውም ለአሕዛብ በረከት ከሆነ፣ ሙላታቸው ምን ያህል ታላቅ በረከት ያመጣ ይሆን? አሕዛብ ሆይ፤ ለእናንተ እናገራለሁ፤ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን አገልግሎቴን በትጋት እፈጽማለሁ፤ ይኸውም የገዛ ወገኖቼን እንዲቀኑ አነሣሥቼ ከእነርሱ ጥቂቱን ለማዳን ተስፋ በማድረግ ነው። የእነርሱ መተው ለዓለም ዕርቅን ካስገኘ፣ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በኵር ሆኖ የቀረበው የቡሖው ክፍል ቅዱስ ከሆነ፣ ቡሖው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩ ቅዱስ ከሆነ፣ ቅርንጫፎቹም ቅዱሳን ናቸው።
ሮሜ 11:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እንግዲህ፦ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ዳሩ ግን በደላቸው ለዓለም ባለ ጠግነት መሸነፋቸውም ለአሕዛብ ባለ ጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? ለእናንተም ለአሕዛብ እናገራለሁ። እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ በሆንሁ መጠን ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ አገልግሎቴን አከብራለሁ። የእነርሱ መጣል ለዓለም መታረቅ ከሆነ ከሙታን ከሚመጣ ሕይወት በቀር መመለሳቸው ምን ይሆን? በኵራቱም ቅዱስ ከሆነ ብሆው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው።
ሮሜ 11:11-16 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እስቲ፥ እንደገና ልጠይቅ፤ አይሁድ የወደቁት ዳግመኛ እንደማይነሡ ሆነው ነውን? አይደለም! በአይሁድ በደል ምክንያት አሕዛብ መዳንን አገኙ፤ ይህም የሆነው አይሁድ በአሕዛብ እንዲቀኑ ለማድረግ ነው። የአይሁድ በደል ለዓለም ብዙ በረከት አስገኝቶአል፤ የእነርሱም ውድቀት ለአሕዛብ በረከት ሆኖአል፤ አይሁድ ቢድኑማ ኖሮ በረከቱ ምን ያኽል ብዙ በሆነ ነበር! አሁን እንግዲህ የምናገረው ለእናንተ ለአሕዛብ ነው፤ የአሕዛብም ሐዋርያ እንደ መሆኔ መጠን በአገልግሎቴ ክብር ይሰማኛል፤ ይህንንም ማድረጌ የሥጋ ዘመዶቼ የሆኑትን አይሁድ ለማስቀናት ነው፤ በዚህም ሁኔታ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዶቹን ለማዳን እችል ይሆናል በማለት ነው። እግዚአብሔር እነርሱን በጣላቸው ጊዜ ሌላው የዓለም ሕዝብ ከእግዚአብሔር ጋር ከታረቀ እግዚአብሔር እነርሱን በሚቀበላቸው ጊዜ ምን የሚሆን ይመስላችኋል? ይህማ ከሞት እንደ መነሣት ያኽል ነው! ከአንድ ዐይነት ሊጥ የመጀመሪያው ክፍል የተቀደሰ ከሆነ ሊጡ በሙሉ የተቀደሰ ይሆናል፤ እንዲሁም የአንድ ዛፍ ሥሩ የተቀደሰ ከሆነ ቅርንጫፎቹም የተቀደሱ ይሆናሉ።
ሮሜ 11:11-16 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ተመልሰው መዳን እስከማይችሉ ድረስ ተሰናከሉን? ብዬ እጠይቃለሁ፤ በጭራሽ! ነገር ግን እነርሱን ለማስቀናት፥ በእነርሱ በደል፥ መዳን ለአሕዛብ ሆነ። ነገር ግን በደላቸው ለዓለም ባለጠግነት ውድቀታቸውም ለአሕዛብ ባለጠግነት ከሆነ፥ ይልቁንስ መሙላታቸው እንዴት ይሆን? አሁን አሕዛብ ለሆናችሁ ለእናንተ እናገራለሁ፤ እኔ የአሕዛብ ሐዋርያ እንደመሆኔ አገልግሎቴን አከብራለሁ፤ ይህም ሥጋዬ የሆኑትን አስቀንቼ ምናልባት ከእነርሱ አንዳንዱን አድን እንደሆነ ነው። የእነርሱ መጣል ለዓለም እርቅን ካስገኘ፥ ተቀባይነት ማግኘታቸውማ ከሞት መነሣት ነው ከማለት በቀር ምን መሆን ይችላል? በኩራቱም ቅዱስ ከሆነ ብኮው ደግሞ ቅዱስ ነው፤ ሥሩም ቅዱስ ከሆነ ቅርንጫፎቹ ደግሞ ቅዱሳን ናቸው።