የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 10:4-13

ሮሜ 10:4-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የኦ​ሪት ጽድቅ ፍጻ​ሜስ ለሚ​ያ​ም​ኑ​በት ሁሉ በክ​ር​ስ​ቶስ ማመን ነው። ሙሴም “የኦ​ሪ​ትን ጽድቅ መሥ​ራ​ትን የፈ​ጸመ ሁሉ በእ​ርሱ ይጸ​ድ​ቅ​በ​ታል” አለ። የእ​ም​ነት ጽድቅ ግን እን​ዲህ ይላል፥ “በል​ብህ ወደ ሰማይ ማን ይወ​ጣል?” አት​በል፤ ከሰ​ማይ የወ​ረ​ደው ክር​ስ​ቶስ ነው። “ወደ ጥል​ቁም ማን ይወ​ር​ዳል?” አት​በል፤ ከሙ​ታን ተለ​ይቶ የተ​ነ​ሣው ክር​ስ​ቶስ ነው። መጽ​ሐፍ እን​ዲሁ፥ “ቃል ለል​ብ​ህም ለአ​ፍ​ህም ቀር​ቦ​ል​ሃል ይል የለ​ምን?” ይህም የም​ን​ሰ​ብ​ከው የእ​ም​ነት ቃል ነው። ኢየ​ሱስ ጌታ እንደ ሆነ በአ​ፍህ ብት​መ​ሰ​ክር እግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርም ከሙ​ታን ለይቶ እንደ አስ​ነ​ሣው በል​ብህ ብታ​ምን ትድ​ና​ለህ። በልቡ የሚ​ያ​ምን ይጸ​ድ​ቃ​ልና፤ በአ​ፉም የሚ​መ​ሰ​ክር ይድ​ና​ልና። መጽ​ሐፍ፥ “የሚ​ያ​ም​ን​በት ሁሉ አያ​ፍ​ርም” ብሎ​አል። አይ​ሁ​ዳ​ዊ​ንና አረ​ማ​ዊን አል​ለ​የም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፥ እግ​ዚ​አ​ብ​ሔር ባለ​ጸጋ ስለ​ሆነ ለለ​መ​ነው ሁሉ ይበ​ቃ​ልና። “የእ​ግ​ዚ​አ​ብ​ሔ​ርን ስም የሚ​ጠራ ሁሉ ይድ​ናል።”

ሮሜ 10:4-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ለሚያምን ሁሉ ጽድቅ ይሆን ዘንድ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ በኩል የሆነውን ጽድቅ ሲገልጽ፣ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፤ “ ‘በልብህ ማን ወደ ሰማይ ይወጣል?’ አትበል”፤ ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ “ወይም ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል”፤ ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማውጣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? “ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ውስጥ ነው፤” የምንሰብከውም የእምነት ቃል ይህ ነው፤ “ኢየሱስ ጌታ ነው” ብለህ በአፍህ ብትመሰክር፣ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን፣ ትድናለህ። የምትጸድቀው በልብህ አምነህ ነው፤ የምትድነውም በአፍህ መስክረህ ነውና። መጽሐፍ እንደሚለው፣ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት የለም፤ አንዱ ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና፤ የሚለምኑትንም አብዝቶ ይባርካል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”

ሮሜ 10:4-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ሰው ሁሉ በእምነት እንዲጸድቅ ሕግ በክርስቶስ አክትሞአል። ሕግን በመከተል ስለሚገኘው ጽድቅ ሙሴ የጻፈው “ሕግን የሚፈጽም ሁሉ በሕይወት ይኖራል” የሚል ነው። እግዚአብሔር ሰዎችን በእምነት ስለ ማጽደቁ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፤ “በልብህ ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም በልብህ “ወደ ሲኦል ማን ይወርዳል?” አትበል፤ ይህም ክርስቶስን ከሞት ለማስነሣት ነው። ደግሞም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “የእግዚአብሔር ቃል አጠገብህ ነው፤ እንዲያውም በአፍህና በልብህ ነው፤” ይህም ቃል እኛ የምናበሥረው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በአፍህ ብትመሰክርና እግዚአብሔር ከሞት እንዳስነሣውም በልብህ ብታምን ትድናለህ። ሰው በልቡ ሲያምን ይጸድቃል፤ በአፉም ሲመሰክር ይድናል፤ በቅዱስ መጽሐፍ እንደ ተጻፈው፦ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም።” እንግዲህ አንዱ ጌታ የሁሉም ጌታ ስለ ሆነ በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ምንም ልዩነት የለም፤ እርሱም ለሚለምኑት ሁሉ በረከቱን አብዝቶ ይሰጣል፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናል” ተብሎአልና።

ሮሜ 10:4-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የሚያምን ሁሉ እንዲጸድቅ ክርስቶስ የሕግ ፍጻሜ ነውና። ሙሴ በሕግ ስለ ሆነው ጽድቅ ሲጽፍ “እነዚህን የሚፈጽም ሰው በእነርሱ ይኖራል” ይላል። ከእምነት የሆነው ጽድቅ ግን እንዲህ ይላል፥ “በልብህ ‘ወደ ሰማይ ማን ይወጣል?’ አትበል፤” ይህ ክርስቶስን ለማውረድ ነው፤ ወይም “በልብህ ‘ወደ ጥልቁስ ማን ይወርዳል?’ አትበል፤” ይህም ክርስቶስን ከሙታን ለማስነሣት ነው። ነገር ግን ምን ይላል? ቃሉ በአጠገብህ ነው፤ በአፍህና በልብህም ነው፤ የምንሰብከው የእምነት ቃል ይህ ነው። ምክንያቱም ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር፥ እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምን ትድናለህ፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃል፥ በአፉም መስክሮ ይድናልና። መጽሐፍ “በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም” ይላልና። በአይሁዳዊና በግሪካዊ መካከል ልዩነት የለምና፤ ያው ጌታ የሁሉ ጌታ ነውና ለሚጠሩትም ሁሉ ባለ ጠጋ ነው፤ “የጌታን ስም የሚጠራ ሁሉ ይድናልና።”