ሮሜ 1:18-22
ሮሜ 1:18-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እውነትን ዐውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት በዐመፀናውና በኀጢአተናው ሰው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው እግዚአብሔርን ማወቅ በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ እርሱም የዘለዓለም ኀይሉና ጌትነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብና በመመርመር ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበትን ምክንያት እንዳያገኙ። እግዚአብሔርን ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላከበሩትም፤ አላመሰገኑትምም፤ ነገር ግን ካዱት፤ በአሳባቸውም ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ አላዋቆች ሆኑ።
ሮሜ 1:18-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በክፋታቸው እውነትን ዐፍነው በሚይዙ፣ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው ለእነርሱ ግልጽ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእነርሱ ግልጽ አድርጎታል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፣ ይኸውም ዘላለማዊ ኀይሉና መለኮትነቱ፣ ከፍጥረቱ በግልጽ ይታያል፤ ስለዚህ ሰዎች ማመካኛ የላቸውም። እግዚአብሔርን ቢያውቁም እንኳ፣ እንደ አምላክነቱ አላከበሩትም፤ ምስጋናም አላቀረቡለትም፤ ነገር ግን ሐሳባቸው ፍሬ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውል ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ፤
ሮሜ 1:18-22 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እውነትን በዓመፃ በሚከለክሉ ሰዎች በኃጢአተኝነታቸውና በዓመፃቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቍጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ እግዚአብሔር ስለ ገለጠላቸው፥ ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና። የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ደንቆሮ ሆኑ፥
ሮሜ 1:18-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ሰዎች በክፋታቸው እውነት እንዳይታወቅ ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ባለመፍራታቸውና በክፋታቸው ምክንያት በሁሉም ላይ የእግዚአብሔር ቊጣ ከሰማይ ይገለጣል። የሚቀጣቸውም ስለ እግዚአብሔር ማወቅ የሚገባቸውን እግዚአብሔር ራሱ ገልጦላቸው ያውቁ ስለ ነበር ነው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ለሰዎች የማይታየው የእግዚአብሔር ባሕርይ፥ ይኸውም ዘለዓለማዊው ኀይሉና አምላክነቱ እርሱ በፈጠራቸው ነገሮች አማካይነት ግልጥ ሆኖ ስለ ታየ ሰዎች ለሚያጠፉት ጥፋት ምክንያት የላቸውም። እነርሱ እግዚአብሔርን ዐውቀውት ሳለ ለእርሱ እንደ አምላክነቱ የሚገባውን ክብርና ምስጋና አልሰጡትም፤ በሐሳባቸውም ከንቱ ሆኑ፤ የማያስተውል ልቡናቸውም ጨለመ፤ “ጥበበኞች ነን” ሲሉ ሞኞች ሆኑ።
ሮሜ 1:18-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በክፋታቸው እውነትን አፍነው በሚይዙ ሰዎች፥ በዐመፃቸውና በክፋታቸው ሁሉ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ከሰማይ ይገለጣልና፤ ስለ እግዚአብሔር መታወቅ የሚገባው በእነርሱ መካከል ግልፅ ነው፤ ምክንያቱም ለእነርሱ እግዚአብሔር ግልፅ አድርጎላቸዋል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የማይታዩት ነገሮች፥ ይኸውም ዘላለማዊው ኃይሉና መለኮታዊነቱ ታውቆ፥ ግልፅም ሆኖ ስለሚታይ ሰበብ የላቸውም። ምክንያቱም እግዚአብሔርን እያወቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን አላከበሩትም ወይም አላመሰገኑትም፤ ነገር ግን ምክንያታቸው ዋጋ ቢስ ሆነ፤ የማያስተውለው ልባቸውም ጨለመ። ጥበበኞች ነን ሲሉ ሞኞች ሆኑ፤