የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ራእይ 9:1-21

ራእይ 9:1-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

አምስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፤ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ፤ ፀሐይና አየርም በጕድጓዱ ጢስ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፤ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው። የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው። አምስትም ወር ሊያሰቃዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚያሠቃዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚያሠቃይ ነው። በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ አያገኙትምም፤ ሊሞቱም ይመኛሉ፤ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል። የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፤ በራሳቸውም ላይ ወርቅ የሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፤ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤ የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፤ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ። እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፤ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፤ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው። በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው፤ እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አባዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል። ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል። ስድስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፤ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው፤” አለው። የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፥ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ይጐዳሉ። በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሓ አልገቡም።

ራእይ 9:1-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀውንም ኮከብ አየሁ፤ ኮከቡም የጥልቁ ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። ጥልቁን ጕድጓድ በከፈተውም ጊዜ፣ ከውስጡ ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ያለ ጢስ ወጣ። ከጕድጓዱም በወጣው ጢስ ፀሓይና ሰማይ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጦች ወጥተው በምድር ላይ ወረዱ፤ እንደ ምድር ጊንጦች ሥልጣን ያለ ሥልጣን ተሰጣቸው። እነርሱም የምድርን ሣር ወይም ማናቸውንም የለመለመ ተክል ወይም ዛፍ እንዳይጐዱ፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር ማኅተም በግምባራቸው ላይ የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ እንዲጐዱ ተነገራቸው። እነርሱንም አምስት ወር ብቻ እንዲያሠቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሏቸው ሥልጣን አልተሰጣቸውም፤ የሚሠቃዩትም ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ሥቃይ ነው። በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል። አንበጦቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶች ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ደፍተዋል፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤ ጠጕራቸው የሴት ጠጕር፣ ጥርሳቸውም የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር። የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት የሚገሠግሡ የብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች ድምፅ ይመስል ነበር። እንደ ጊንጥም ያለ፣ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ ደግሞም ሰዎችን አምስት ወር የሚያሠቃዩበት ኀይል በጅራታቸው ላይ ነበር። በላያቸው ንጉሥ ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጕድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ “አብዶን”፣ በግሪክ ደግሞ “አጶልዮን” ይባላል። የመጀመሪያው ወዮ ዐልፏል፤ እነሆ፤ ከዚህ በኋላ ገና ሌላ ሁለት ወዮዎች ይመጣሉ። ስድስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲመጣ ሰማሁ፤ ድምፁም መለከት የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፣ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው” አለው። ከሰው ዘር አንድ ሦስተኛውን እንዲገድሉ፣ ለዚህች ሰዓትና ዕለት እንዲሁም ለዚህች ወርና ዓመት ተዘጋጅተው የነበሩት አራቱ መላእክት ተፈቱ። የፈረሰኛው ሰራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበር፤ ቍጥራቸውንም ሰማሁ። በራእዬ ያየኋቸው ፈረሶችና በላያቸውም የተቀመጡት ይህን ይመስሉ ነበር፤ ጥሩራቸው እንደ እሳት ቀይ፣ እንደ ያክንት ሰማያዊና እንደ ዲን ብጫ ነበር፤ የፈረሶቹ ራስ የአንበሶችን ራስ ይመስል ነበር። ከአፋቸውም እሳትና ጢስ፣ ዲንም ይወጣ ነበር። ከአፋቸው በወጡት፣ በሦስቱ መቅሠፍቶች፣ ማለት በእሳቱ፣ በጢሱና በዲኑ አንድ ሦስተኛው የሰው ዘር ተገደለ። የፈረሶቹ ኀይል በአፋቸውና በጅራታቸው ላይ ነበር፤ ጅራታቸውም እባብ ይመስል ነበር፤ ራስ ስላላቸው ጕዳት የሚያደርሱት በእርሱ ነበር። በእነዚህ መቅሠፍቶች ሳይገደሉ የቀሩት ሰዎች አሁንም ከእጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትን እንዲሁም ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከናስ፣ ከድንጋይና ከዕንጨት የተሠሩትን ጣዖቶች ማምለክ አልተዉም፤ ደግሞም ከነፍስ ግድያቸው፣ ከጥንቈላ ሥራቸው፣ ከዝሙት ርኩሰታቸው ወይም ከስርቆት ተግባራቸው ንስሓ አልገቡም።

ራእይ 9:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

አምስተኛውም መልአክ ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፥ የጥልቁም ጕድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። የጥልቁንም ጕድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ እቶን እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጕድጓዱ ወጣ ፀሐይና አየርም በጕድጕዱ ጢስ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፥ የምድርም ጊንጦች ሥልጣን እንዳላቸው ሥልጣን ተሰጣቸው። የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተባለላቸው። አምስትም ወር ሊሣቅዩአቸው ተሰጣቸው እንጂ ሊገድሉአቸው አይደለም፤ እነርሱም የሚሣቅዩት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ነድፎ እንደሚሣቅይ ነው። በዚያም ወራት ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ አያገኙትምም፥ ሊሞቱም ይመኛሉ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል። የአንበጣዎቹም መልክ ለጦርነት እንደ ተዘጋጁ ፈረሶች ነው፥ በራሳቸውም ላይ ወርቅ እንደሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፥ ፊታቸውም እንደ ሰው ፊት ነበረ፤ የሴቶችን ጠጕር የሚመስል ጠጕር ነበራቸው፥ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፥ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፥ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሰረገላዎች ድምፅ ነበረ። እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው በጅራታቸውም መውጊያ አለ፥ ሰዎችንም አምስት ወር እንዲጐዱ ሥልጣን አላቸው። በእነርሱም ላይ ንጉሥ አላቸው እርሱም የጥልቅ መልአክ ነው፥ ስሙም በዕብራይስጥ አብዶን በግሪክም አጶልዮን ይባላል። ፊተኛው ወዮ አልፎአል፤ እነሆ፥ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት ወዮ ይመጣል። ስድስተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለ በወርቅ ከተሠራ መሠዊያ ቀንዶች አንድ ድምፅ ሰማሁ፥ መለከትም ያለውን ስድስተኛውን መልአክ፦ በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው አለው። የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። የፈረሰኞችም ጭፍራ ቁጥር እልፍ ጊዜ እልፍ፥ እልፍ ጊዜ እልፍ ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፥ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፤ ጅራታቸው እባብን ይመስላልና፥ ራስም አላቸው በእርሱም ይጐዳሉ። በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ለአጋንንትና ያዩ ወይም ይሰሙ ወይም ይሄዱ ዘንድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶች እንዳይሰግዱ ስለ እጃቸው ሥራ ንስሐ አልገቡም፤ ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሐ አልገቡም።

ራእይ 9:1-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

አምስተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እነሆ፥ ከሰማይ ወደ ምድር የወደቀ አንድ ኮከብ አየሁ፤ የጥልቁ ጒድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። እርሱ የጥልቁን ጒድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጥልቁ ጒድጓድ ወጣ፤ ከጒድጓዱ በወጣው ጢስ ምክንያት ፀሐይና አየር ጨለሙ፤ ከጢሱም ውስጥ አንበጣዎች በምድር ላይ ወጡ፤ የምድር ጊንጦችን ኀይል የመሰለ ኀይል ተሰጣቸው፤ የምድርን ሣር ሆነ ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተነገራቸው፤ መጒዳት ያለባቸው ግን በግንባራቸው ላይ የእግዚአብሔር ማኅተም የሌለባቸውን ሰዎች ብቻ ነበር። እነርሱንም ቢሆን አምስት ወር ለማሠቃየት እንጂ ለመግደል ፈቃድ አልተሰጣቸውም፤ አንበጣዎቹ የደረሰባቸው ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚሰማው ዐይነት ያለ ነው። በእነዚያ ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ ነገር ግን አያገኙትም፤ ለመሞትም ይመኛሉ፤ ነገር ግን ሞት ከእነርሱ ይሸሻል። አንበጣዎቹ ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶችን ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸው ላይ የወርቅ አክሊል የመሰለ ነገር ነበር፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበር፤ የሴት ጠጒር የመሰለ ጠጒር ነበራቸው፤ ጥርሳቸው የአንበሳ ጥርስ ይመስል ነበር፤ የብረት ጥሩር የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፎቻቸው ድምፅ ወደ ጦርነት የሚጋልቡ ብዙ ፈረሶችና ሠረገላዎች የሚያሰሙትን ድምፅ ይመስል ነበር። እንደ ጊንጥ ጅራትና መንደፊያ ነበራቸው፤ በጅራታቸው ውስጥ ሰዎችን ለአምስት ወር የሚጐዱበት ኀይል ነበራቸው። ንጉሥም ነበራቸው፤ እርሱ የጥልቁ ጒድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አባዶን፥ በግሪክ አጶልዮን ይባላል፤ የመጀመሪያው ወዮ አልፎአል፥ እነሆ ከዚህ በኋላ ሌላ ሁለት ወዮ ገና ይመጣል። ስድስተኛው መልአክ እምቢልታውን ነፋ፤ እነሆ፥ በእግዚአብሔር ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው ከመሠዊያው ቀንዶች ድምፅ ሲወጣ ሰማሁ። ድምፁም እምቢልታ የያዘውን ስድስተኛውን መልአክ፥ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው!” አለው። ለዚህ ሰዓትና ለዚህ ቀን፥ ለዚህ ወርና ለዚህ ዓመት የተዘጋጁት አራቱ መላእክት የሰውን ዘር አንድ ሦስተኛ እንዲገድሉ ተፈቱ። የፈረሰኞቹ ሠራዊት ብዛት ሁለት መቶ ሚሊዮን መሆኑን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በፈረሶቹ ላይ የተቀመጡትን ሰዎች በራእይ ያየኋቸው እንደሚከተለው ነበር፦ በደረታቸው ላይ የነበረው ጥሩር እንደ እሳት ፍም ቀይ፥ እንደ ያክንት ጥቊር ሰማያዊ፥ እንደ ዲን ቢጫ ይመስል ነበር፤ የፈረሶቹም ራስ የአንበሳ ራስ ይመስል ነበር፤ ከአፋቸው እሳትና ጢስ ዲንም ይወጣ ነበር፤ ከአፋቸው ባወጡት እሳት፥ ጢስና ዲን በእነዚህ በሦስቱ መቅሠፍቶች የሰው ዘር አንድ ሦስተኛ ተገደለ። የፈረሶቹ ኀይል በአፋቸውና በጅራታቸው ነበር፤ ጅራታቸው እባብ ይመስላል፤ የእባብ ራስም አለው፤ ሰውንም የሚጐዱት በእርሱ ነበር። በእነዚህ መቅሠፍቶች ከሞት የተረፉት የሰው ዘር ከእጃቸው ሥራ ተመልሰው ንስሓ አልገቡም፤ አጋንንትንና ከወርቅ፥ ከብር፥ ከናስ፥ ከድንጋይና ከእንጨት የተሠሩ ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ የማይችሉትን ጣዖቶች ማምለክንም አልተዉም። እንዲሁም ከነፍሰ ገዳይነታቸው፥ ከሟርታቸው፥ ከሴሰኛነታቸው፥ ከሌብነታቸውም ንስሓ አልገቡም።

ራእይ 9:1-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

አምስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ከሰማይም ወደ ምድር ወድቆ የነበረ ኮከብ አየሁ፤ የጥልቁም ጉድጓድ መክፈቻ ተሰጠው። የጥልቁንም ጉድጓድ ከፈተው፤ ጢስም ከታላቅ ምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ሆኖ ከጉድጓዱ ወጣ፤ ፀሐይና አየርም በጉድጓዱ ጢስ ጨለሙ። ከጢሱም አንበጣዎች ወደ ምድር ወጡ፤ የምድርም ጊንጦች እንዳላቸው ሥልጣን ዓይነት ሥልጣን ተሰጣቸው። የእግዚአብሔርም ማኅተም በግምባራቸው ከሌለባቸው ሰዎች በቀር በምድር ያለውን ሣር ቢሆንም ወይም ማናቸውንም የለመለመ ነገር ወይም ማናቸውንም ዛፍ እንዳይጐዱ ተነገራቸው። ለአምስትም ወር እንዲያሰቃዩአቸው እንጂ እንዲገድሉአቸው አልተፈቀደላቸውም፤ እነርሱም የሚያደርሱት ሥቃይ ጊንጥ ሰውን ሲነድፍ እንደሚያደርሰው ስቃይ ዓይነት ነው። በዚያም ቀኖች ሰዎች ሞትን ይፈልጋሉ፤ አያገኙትምም፤ ሊሞቱም ይመኛሉ፤ ሞትም ከእነርሱ ይሸሻል። አንበጣዎቹም ለጦርነት የተዘጋጁ ፈረሶችን ይመስሉ ነበር፤ በራሳቸውም ላይ የወርቅ የሚመስሉ አክሊሎች ነበሩአቸው፤ ፊታቸውም የሰው ፊት ይመስል ነበረ፤ የሴቶችን ጠጉር የሚመስል ጠጉር ነበራቸው፤ ጥርሳቸውም እንደ አንበሳ ጥርስ ነበረ፤ የብረት ጥሩር የሚመስልም ጥሩር ነበራቸው፤ የክንፋቸውም ድምፅ ወደ ጦርነት እንደሚጋልቡ እንደ ብዙ ፈረሶች ሠረገላዎች ድምፅ ነበረ። እንደ ጊንጥም ጅራት ያለ ጅራት አላቸው፤ በጅራታቸውም መውጊያ አለ፤ ሰዎችንም ለአምስት ወር ያህል የመጉዳት ሥልጣን አላቸው። ንጉሥም ነበራቸው፤ እርሱም የጥልቁ ጉድጓድ መልአክ ነው፤ ስሙም በዕብራይስጥ አባዶን በግሪክም አጶልዮን ነው። የፊተኛው “ወዮ” አልፎአል፤ እነሆ ከዚህ በኋላ ገና ሁለት “ወዮ” ይመጣል። ስድስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ካለው በወርቅ ከተሠራው መሠዊያ ቀንዶች ድምፅ ሲወጣ ሰማሁ፤ እርሱም መለከት ለያዘው ስድስተኛው መልአክ “በታላቁ ወንዝ በኤፍራጥስ የታሰሩትን አራቱን መላእክት ፍታቸው፤” አለው። የሰዎችንም ሲሶ እንዲገድሉ ለሰዓቱና ለቀኑ ለወሩም ለዓመቱም ተዘጋጅተው የነበሩ አራቱ መላእክት ተፈቱ። የፈረሰኞችም ጭፍራ ቍጥር ሁለት መቶ ሚሊዮን ነበረ፤ ቁጥራቸውን ሰማሁ። ፈረሶቹንና በእነርሱም ላይ የተቀመጡትን እንዲሁ በራእይ አየሁ፤ እሳትና ያክንት ዲንም የሚመስል ጥሩር ነበራቸው፤ የፈረሶቹም ራስ እንደ አንበሳ ራስ ነበረ፤ ከአፋቸውም እሳትና ጢስ ዲንም ወጣ። ከአፋቸውም በወጡት በእሳቱና በጢሱ በዲኑም በእነዚህ ሦስት መቅሰፍቶች የሰዎቹ ሲሶ ተገደለ። የፈረሶቹ ሥልጣን በአፋቸውና በጅራታቸው ነውና፥ ጅራታቸው እባብን ይመስላል፤ ራስም አላቸው፤ በእርሱም ጉዳትን ያደርሳሉ። በእነዚህም መቅሠፍቶች ያልተገደሉት የቀሩቱ ሰዎች ስለ እጃቸው ሥራ ንስሓ አልገቡም፤ ለአጋንንትና ማየት ወይም መስማት ወይም መሄድ ለማይችሉ ከወርቅና ከብር ከናስም ከድንጋይም ከእንጨትም ለተሠሩ ለጣዖቶችም መስገድን አልተዉም። ስለ መግደላቸውም ቢሆን ወይም ስለ አስማታቸው ወይም ስለ ዝሙታቸው ወይም ስለ ስርቆታቸው ንስሓ አልገቡም።