ራእይ 8:1-13
ራእይ 8:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጉ ሰባተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ግማሽ ሰዓት ያህል በሰማይ ዝምታ ሆነ። ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባት መለከትም ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ የወርቅ ጥና ይዞ መጣና በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ እርሱም በዙፋኑ ፊት ባለው የወርቅ መሠዊያ ላይ ከቅዱሳን ጸሎት ሁሉ ጋር እንዲያቀርበው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳኑ ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ። መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፤ ነጐድጓድ፣ ድምፅ፣ መብረቅና የምድር መናወጥ ሆነ። ከዚያም ሰባቱን መለከት የያዙት ሰባቱ መላእክት ለመንፋት ተዘጋጁ። የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ወደ ምድር ተጣለ፤ የምድር አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የዛፎችም አንድ ሦስተኛ ተቃጠለ፤ የለመለመውም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገር በእሳት እየተቀጣጠለ ወደ ባሕር ተጣለ፤ የባሕሩ አንድ ሦስተኛ ወደ ደም ተለወጠ፤ በባሕሩም ውስጥ ከሚኖሩት ሕያዋን ፍጡራን አንድ ሦስተኛ ሞተ፤ የመርከቦችም አንድ ሦስተኛ ወደመ። ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦ የሚነድድ ታላቅ ኮከብ በወንዞች አንድ ሦስተኛና በውሃ ምንጮች ላይ ከሰማይ ወደቀ፤ የኮከቡም ስም “እሬቶ” ይባል ነበር። የውሃውም አንድ ሦስተኛ መራራ ሆነ፤ ውሃው መራራ ከመሆኑ የተነሣም ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የብርሃናቸው አንድ ሦስተኛ ይጨልም ዘንድ፣ የፀሓይ አንድ ሦስተኛ፣ የጨረቃም አንድ ሦስተኛ፣ የከዋክብትም አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ የቀንም አንድ ሦስተኛ፣ የሌሊቱም አንድ ሦስተኛ ብርሃን እንዳይሰጥ ተከለከለ። ከዚያም ተመለከትሁ፤ አንድ ንስር በሰማይ መካከል ይበርር ነበር፤ በታላቅ ድምፅም፣ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚነፉ፣ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።
ራእይ 8:1-13 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ግማሽ ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። ፊተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፤ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ፤ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ። ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞችና በውሃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፤ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት። አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” ሲል ሰማሁ።
ራእይ 8:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ እኵል ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፥ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሰዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሰዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ወጣ። መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሰዊያውን እሳት ሞላበት ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። ፊተኛውም መልአክ ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፥ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ የመርከቦችም ሲሶው ጠፋ። ሦስተኛውም መልአክ ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፥ በወንዞችና በውኃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል። የውኃውም ሲሶ መራራ ሆነ መራራም ስለተደረገ በውኃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛውም መልአክ ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፥ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንም ሲሶው እንዳያበራ፥ እንዲሁም የሌሊት። አየሁም፥ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ፦ ሊነፉ ያላቸው የሦስቱ መላእክት መለከት ስለሚቀረው ድምፅ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው፥ ወዮላቸው፥ ወዮላቸው ሲል ሰማሁ።
ራእይ 8:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በጉ ሰባተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ እኩል ሰዓት ያኽል በሰማይ ዝምታ ሆነ፤ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙትንም ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ለእነርሱ ሰባት እምቢልታዎች ተሰጡአቸው። የወርቅ ጥና የያዘ ሌላ መልአክ መጣና በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑ ፊት ባለው የወርቅ መሠዊያ ላይ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር የሚያቀርበው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑ ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ ወደ እግዚአብሔር ፊት ወጣ። ከዚህ በኋላ መልአኩ ጥናውን ይዞ ከመሠዊያው እሳት ሞላበትና ወደ ምድር ወረወረው፤ ነጐድጓድ፥ ድምፅ፥ መብረቅ፥ የምድር መናወጥም ሆነ። ሰባት መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት መለከቶቻቸውን ለመንፋት ተዘጋጁ። የመጀመሪያው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በረዶና ደም የተቀላቀለበት እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድር ሢሶ ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሢሶ ተቃጠለ፤ የለመለመ ሣርም ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ትልቅ ተራራ የሚመስል ነገር እየነደደ ወደ ባሕር ተጣለ፤ የባሕር ሢሶው ደም ሆነ፤ በባሕር ውስጥ ከሚኖሩት ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሢሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሢሶ ወደመ። ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦ የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ የወደቀውም በወንዞች ሢሶና በውሃ ምንጮች ላይ ነው። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃው አንድ ሦስተኛ መራራ ሆነ፤ መራራ በሆነውም ውሃ ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛው መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ አንድ ሦስተኛ፥ የጨረቃ አንድ ሦስተኛ፥ የኮከቦች አንድ ሦስተኛ ተመታ፤ ስለዚህ የእነርሱ አንድ ሦስተኛቸው ጨለመ፤ በዚህ ዐይነት የቀን አንድ ሦስተኛና የሌሊት አንድ ሦስተኛ ያለ ብርሃን ሆነ። ከዚህ በኋላ ስመለከት አንድ ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት የእምቢልታቸውን ድምፅ በሚያሰሙበት ጊዜ በምድር ላይ ለሚኖሩ ሰዎች ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!” እያለ ሲጮኽ ሰማሁ።
ራእይ 8:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ሰባተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ለግማሽ ሰዓት የሚያህል ዝምታ በሰማይ ሆነ። በእግዚአብሔርም ፊት የሚቆሙትን ሰባቱን መላእክት አየሁ፤ ሰባትም መለከት ተሰጣቸው። ሌላም መልአክ መጣና የወርቅ ጥና ይዞ በመሠዊያው አጠገብ ቆመ፤ በዙፋኑም ፊት ባለው በወርቅ መሠዊያ ላይ ለቅዱሳን ሁሉ ጸሎት እንዲጨምረው ብዙ ዕጣን ተሰጠው። የዕጣኑም ጢስ ከቅዱሳን ጸሎት ጋር ከመልአኩ እጅ በእግዚአብሔር ፊት ዐረገ። መልአኩም ጥናውን ይዞ የመሠዊያውን እሳት ሞላበት፤ ወደ ምድርም ጣለው፤ ነጐድጓድና ድምፅም መብረቅም መናወጥም ሆነ። ሰባቱንም መለከት የያዙ ሰባቱ መላእክት ሊነፉ ተዘጋጁ። የፊተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ ደምም የተቀላቀለበት በረዶና እሳት ሆነ፤ ወደ ምድርም ተጣለ፤ የምድርም ሲሶው ተቃጠለ፤ የዛፎችም ሲሶው ተቃጠለ፤ የለመለመም ሣር ሁሉ ተቃጠለ። ሁለተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ በእሳት የሚቃጠል ታላቅ ተራራን የሚመስል ነገር በባሕር ተጣለ፤ የባሕርም ሲሶው ደም ሆነ፤ በባሕርም ከሚኖሩ ሕይወት ካላቸው ፍጥረቶች ሲሶው ሞተ፤ የመርከቦችም ሲሶው ወደመ። ሦስተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ እንደ ችቦም የሚቃጠል ታላቅ ኮከብ ከሰማይ ወደቀ፤ በወንዞችና በውሃም ምንጮች ሲሶ ላይ ወደቀ። የኮከቡም ስም እሬቶ ይባላል፤ የውሃውም ሲሶ መራራ ሆነ፤ መራራም ስለተደረገ በውሃው ጠንቅ ብዙ ሰዎች ሞቱ። አራተኛውም መልአክ መለከቱን ነፋ፤ የፀሐይ ሲሶና የጨረቃ ሲሶ የከዋክብትም ሲሶ ተመታ፤ የእነዚህ ሲሶ ይጨልም ዘንድ፥ የቀንና የሌሊት ሲሶው እንዳያበራ ተከለከለ። አየሁም፤ አንድም ንስር በሰማይ መካከል እየበረረ በታላቅ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፦ “የቀሩት ሦስቱ መላእክት መለከትን በሚነፋበት ጊዜ ከሚቀረው ድምፅ የተነሣ በምድር ላይ ለሚኖሩት ወዮላቸው! ወዮላቸው! ወዮላቸው!”