ራእይ 6:1-8
ራእይ 6:1-8 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም አምባላይ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ ድልም እየነሣ ወጣ፤ ድል ለመንሣት። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፤ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ጥቁር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ” ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ “መጥተህ እይ” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ሐመር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
ራእይ 6:1-8 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲፈታ አየሁ፤ ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን አንዱ፣ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ነጭ ፈረስ ቆሞ ነበር፤ ተቀምጦበት የነበረውም ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም እንደ ድል አድራጊ ድል ለመንሣት ወጣ። በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሁለተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። ሌላ ፍም የሚመስል ቀይ ፈረስም ወጣ፤ ተቀምጦበት የነበረው ሰላምን ከምድር ላይ እንዲወስድና ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅም ሰይፍ ተሰጠው። በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ ሦስተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ጥቍር ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም በእጁ ሚዛን ይዞ ነበር። ከዚያም ከአራቱ ሕያዋን ፍጡራን መካከል፣ “አንድ እርቦ ስንዴ ለአንድ ቀን ደመወዝ፤ ሦስት እርቦ ገብስም ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይቱንና የወይን ጠጁን አትጕዳ” የሚል ድምፅ ሰማሁ። በጉ አራተኛውን ማኅተም በፈታ ጊዜ፣ አራተኛው ሕያው ፍጡር፣ “ና!” ሲል ሰማሁ። እኔም ተመለከትሁ፤ እነሆ፤ ግራጫ ፈረስ ቆሞ አየሁ፤ ተቀምጦበት የነበረውም ስሙ ሞት ነበር፤ ሲኦልም ከኋላ ይከተለው ነበር። እነርሱም በሰይፍ፣ በራብ፣ በመቅሠፍትና በምድር አራዊት እንዲገድሉ በምድር አንድ አራተኛ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
ራእይ 6:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
በጉም ከሰባቱ ማኅተም አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፥ ከአራቱም እንስሶች አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ አምባላይ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፥ አክሊልም ተሰጠው፥ ድልም እየነሣ ወጣ ድል ለመንሣት። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። ሌላም ዳማ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር ይወስድ ዘንድ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ ሥልጣን ተሰጠው፥ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ጕራቻ ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም እንስሶች መካከል ድምፅ፦ አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንንም አትጕዳ ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ፦ መጥተህ እይ ሲል ሰማሁ። አየሁም፥ እነሆም፥ ሐመር ፈረስ ወጣ፥ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።
ራእይ 6:1-8 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህም በኋላ በጉ ከሰባቱ ማኅተሞች የመጀመሪያውን ሲከፍት አየሁ። ከአራቱ እንስሶች አንዱ እንደ ነጐድጓድ በሚያስገመግም ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ። እነሆ ነጭ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ቀስት ይዞ ነበር፤ አክሊልም ተሰጠው፤ እርሱም ድል ነሺ ሆኖ ከድል ወደ ድል ለመሄድ ወጣ። በጉ ሁለተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ፥ ሁለተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ። ሌላ ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ በፈረሱ ላይ ለተቀመጠው ሰላምን ከምድር እንዲያስወግድና ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲተላለቁ ለማድረግ ሥልጣን ተሰጠው፤ ትልቅ ሰይፍም ተሰጠው። በጉ ሦስተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ እነሆ ጥቊር ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ሚዛን በእጁ ይዞ ነበር፤ ከአራቱ እንስሶች መካከል የመጣ የሚመስል ድምፅ ሰማሁ፤ ይህ ድምፅ “ግማሽ ኪሎ ያኽል ስንዴ የአንድ ቀን ደመወዝ፥ ለአንድ ኪሎ ተኩል ያኽል ገብስ ለአንድ ቀን ደመወዝ ይሁን፤ ዘይትንና ወይንን ግን አትጒዳ!” ሲል ሰማሁ። በጉ አራተኛውን ማኅተም በከፈተ ጊዜ የአራተኛውን እንስሳ ድምፅ “ና!” ሲል ሰማሁ፤ እነሆ ግራጫ ፈረስ አየሁ፤ በፈረሱ ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ይባል ነበር፤ ሲኦልም ይከተለው ነበር፤ ሞትና ሲኦልም የምድርን አንድ አራተኛ እጅ በጦርነት፥ በራብ፥ በቸነፈርና በምድር አራዊት እንዲገድሉ ሥልጣን ተሰጣቸው።
ራእይ 6:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በጉም ከሰባቱ ማኅተሞች አንዱን በፈታ ጊዜ አየሁ፤ ከአራቱም ሕያዋን ፍጡራን አንዱ ነጐድጓድ በሚመስል ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ነጭ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ቀስት ነበረው፤ አክሊልም ተሰጠው፤ ድል እየነሣ፥ ድልም ለመንሣት ወጣ። ሁለተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሁለተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። ሌላም ደማቅ ቀይ ፈረስ ወጣ፤ ሰዎችም እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱ፥ ሰላምን ከምድር ያስወግድ ዘንድ በእርሱ ላይ ለተቀመጠው ሥልጣን ተሰጠው፤ ታላቅም ሰይፍ ተሰጠው። ሦስተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ ሦስተኛው እንስሳ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም ጥቁር ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው በእጁ ሚዛን ያዘ። በአራቱም ሕያዋን ፍጡራን መካከል እንደ ድምፅ ሰማሁ፦ “አንድ እርቦ ስንዴ በዲናር ሦስት እርቦ ገብስም በዲናር፥ ዘይትንና ወይንን ግን አትጉዳ” ሲል ሰማሁ። አራተኛውንም ማኅተም በፈታ ጊዜ የአራተኛው እንስሳ ድምፅ “ና” ሲል ሰማሁ። አየሁም፤ እነሆም የገረጣ ፈረስ ወጣ፤ በእርሱም ላይ የተቀመጠው ስሙ ሞት ነበረ። ሲኦልም ተከተለው፤ በሰይፍና በራብም በሞትም በምድርም አራዊት ይገድሉ ዘንድ ከምድር በአራተኛዋ እጅ ላይ ሥልጣን ተሰጣቸው።