ራእይ 19:1-6
ራእይ 19:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ከዚህ በኋላ በሰማይ “ሃሌ ሉያ! በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፥ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኀይልም የአምላካችን ነው፤” ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ። ደግመውም “ሃሌ ሉያ! ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል፤” አሉ። ሃያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር “አሜን! ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱለት። ድምፅም “ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ! አምላካችንን አመስግኑ፤” ሲል ከዙፋኑ ወጣ። እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውሃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።
ራእይ 19:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚህ በኋላ የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ በሰማይ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ማዳን፣ ክብርና ኀይል የአምላካችን ነው፤ ፍርዱ እውነትና ጽድቅ ነውና፤ በዝሙቷ ምድርን ያረከሰችውን፣ ታላቂቱን አመንዝራ ፈርዶባታል፤ ስለ አገልጋዮቹም ደም ተበቅሏታል።” ደግሞም እንዲህ አሉ፤ “ሃሌ ሉያ! ጢስ ከእርሷ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል።” ሃያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጡራን በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ ወድቀው ሰገዱ፤ እንዲህም አሉ፤ “አሜን፣ ሃሌ ሉያ!” ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ፤ “እናንተ አገልጋዮቹ ሁሉ፣ እርሱን የምትፈሩ፣ ታናናሾችና ታላላቆችም፣ አምላካችንን አመስግኑ!” ደግሞም እንደ ብዙ ሕዝብ ድምፅ፣ እንደ ኀይለኛ ወራጅ ውሃ ድምፅ፣ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ የሚመስል እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን ቻይ ጌታ አምላካችን ነግሧልና።
ራእይ 19:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
ከዚህ በኋላ በሰማይ፦ ሃሌ ሉያ፤ በዝሙትዋ ምድርን ያጠፋችይቱን ታላቂቱን ጋለሞታ ስለ ፈረደባት፥ የባሪያዎቹንም ደም ከእጅዋ ስለ ተበቀለ፥ ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው ብሎ ሲናገር እንደ ብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅ ያለ ድምፅን ሰማሁ። ደግመውም፦ ሃሌ ሉያ አሉ፤ ጢስዋም ለዘላለም እስከ ዘላለም ይወጣል። ሀያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር፦ አሜን፥ ሃሌ ሉያ እያሉ ሰገዱለት። ድምፅም፦ ባሪያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ፥ አምላካችንን አመስግኑ ሲል ከዙፋኑ ወጣ። እንደ ብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ እንደ ብዙ ውኃዎችም ድምፅ፥ እንደ ብርቱም ነጐድጓድ ድምፅ ያለ ድምፅ ሰማሁ እንዲህ ሲል፦ ሃሌ ሉያ፤ ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።
ራእይ 19:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ከዚህ በኋላ እንዲህ የሚል የብዙ ሰዎችን ድምፅ የሚመስል ታላቅ ድምፅ በሰማይ ሰማሁ “ሃሌ ሉያ! ማዳንና ክብር ኀይልም የአምላካችን ነው! ፍርዱ እውነትና ትክክል ነው፤ ምድርን በአመንዝራነትዋ ያረከሰችውን ታላቂቱን አመንዝራ በፍርድ ቀጥቶአታል፤ እርስዋን በመቅጣትም የአገልጋዮቹን ደም ተበቅሎአል።” እንደገናም፥ “ሃሌ ሉያ! ከእርስዋ የሚነሣው ጢስ ለዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ወደ ላይ ይወጣል!” እያሉ ጮኹ። ኻያ አራቱ ሽማግሌዎችና አራቱ እንስሶች በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው አምላክ በግንባራቸው ተደፍተው “አሜን፥ ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱ። ከዚህ በኋላ “እርሱን የምትፈሩ አገልጋዮቹ ሁሉ፥ ታናናሾችም ታላላቆችም አምላካችንን አመስግኑ!” የሚል ድምፅ ከዙፋኑ ወጣ። የብዙ ሰዎችን ድምፅ የወራጅ ውሃን ድምፅ፥ የብርቱ ነጐድጓድንም ድምፅ፥ የሚመስል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚችል ጌታ አምላካችን ይነግሣል!
ራእይ 19:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ከዚህ በኋላ በሰማይ የብዙ ሕዝብ ታላቅ ድምፅን የመሰለ ድምፅ ሰማሁ፦ “ሃሌ ሉያ! ማዳንና ክብር ኃይልም የአምላካችን ነው፤” ፍርዶቹ እውነትና ጽድቅ ናቸውና፤ በዝሙትዋ ምድርን ያበላሸችውን ታላቂቱን አመንዝራ ፈርዶባት፥ የባርያዎቹንም ደም ከእጅዋ ተበቀሎአልና። ደግመውም እንዲህ አሉ፦ “ሃሌ ሉያ! ጢስዋም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ይወጣል፤” አሉ። ሃያ አራቱም ሽማግሌዎችና አራቱ ሕያዋን ፍጡራን በፊታቸው ተደፍተው በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለእግዚአብሔር “አሜን! ሃሌ ሉያ!” እያሉ ሰገዱለት። ድምፅም ከዙፋኑ እንዲህ ሲል ወጣ፦ “ባርያዎቹ ሁሉ እርሱንም የምትፈሩት ታናናሾችና ታላላቆች ሆይ! አምላካችንን አመስግኑ፤” የብዙ ሕዝብም ድምፅ፥ የብዙ ውሃዎችም ድምፅ፥ የብርቱም ነጐድጓድም ድምፅ የሚመስል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ሃሌ ሉያ! ሁሉን የሚገዛ ጌታ አምላካችን ነግሦአልና።