ራእይ 12:1-9

ራእይ 12:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የዐሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የተቀዳጀች አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፤ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ ይኸውም ታላቅ ቀይ ዘንዶነው፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፤ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች። በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

ራእይ 12:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሓይን የለበሰች፣ ጨረቃን ከእግሮቿ በታች የረገጠችና በራሷም ላይ ዐሥራ ሁለት ከዋክብት ያሉት አክሊል የደፋች አንዲት ሴት ታየች። እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድ ስትል ምጥ ይዟት ተጨንቃ ጮኸች። ከዚያም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት፣ በራሶቹም ላይ ሰባት አክሊል የደፋ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ። ጅራቱ የከዋክብትን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ እርሷም በወለደች ጊዜ ልጇን ለመዋጥ ፈልጎ ዘንዶው ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች። በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋራ ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ። ታላቁ ዘንዶ፣ የጥንቱ እባብ ተጣለ፤ እርሱም ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው፣ ዓለምን ሁሉ የሚያስተው ነው፤ እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከርሱ ጋራ ተጣሉ።

ራእይ 12:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናጽፋ ጨረቃ ከእግሮችዋ በታች ያላት በራስዋም ላይ የአሥራ ሁለት ከዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች። እርስዋም ፀንሳ ነበር፥ ምጥም ተይዛ ልትወልድ ተጭንቃ ጮኸች። ሌላም ምልክት በሰማይ ታየ፤ እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶ፤ ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፥ ጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ዘንዶውም ሴቲቱ በወለደች ጊዜ ሕፃንዋን እንዲበላ ልትወልድ ባላት ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም፥ ሁሉ በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ልጅ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ሺህ ከሁለት መቶ ስድሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ ወደ በረሀ ሸሸች። በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፥ አልቻላቸውምም፥ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።

ራእይ 12:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

ከዚህ በኋላ ታላቅና አስደናቂ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግርዋ በታች ያደረገች፥ ዐሥራ ሁለት ኮከቦችን እንደ አክሊል በራስዋ ላይ የደፋች፥ አንዲት ሴት ታየች። እርስዋም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዞአት ተጨንቃ ትጮኽ ነበር፤ እንዲሁም ሌላ ምልክት በሰማይ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶች የነበሩት ትልቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ደፍቶ ነበር፤ በጅራቱ የኮከቦችን አንድ ሦስተኛ ከሰማይ ስቦ ወደ ምድር ጣላቸው፤ ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ልጅዋን ለመዋጥ አስቦ ዘንዶው ልትወልድ ወደተቃረበችው ሴት ከፊት ለፊትዋ ቆመ፤ ሴቲቱም ሕዝቦችን ሁሉ በብረት በትር የሚገዛ ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጅዋ ግን ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተወሰደ፤ ሴቲቱም ወደ በረሓ ሸሽታ ሄደች፤ እዚያ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሥልሳ ቀን በእንክብካቤ ተይዛ የምትጠበቅበትን ስፍራ እግዚአብሔር አዘጋጅቶላት ነበር። በሰማይ ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና የእርሱ መላእክት ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፥ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጉ። ከእርሱ መላእክት ጋር ተዋጉ፤ ነገር ግን ዘንዶውና የእርሱ መላእክት ተሸነፉ፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ታላቁም ዘንዶ ወደታች ተጣለ፤ እርሱ መላውን ዓለም የሚያስተው ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የቀድሞው እባብ ነው። እርሱ ወደ ምድር ተጣለ፤ የእርሱም መላእክት ከእርሱ ጋር አብረው ተጣሉ።

ራእይ 12:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ፤ ፀሐይን የለበሰች፥ ጨረቃን ከእግሮችዋ በታች ያደረገች፥ ባለ ዐሥራ ሁለት ኮከቦች አክሊልም በራስዋ ላይ የደፋች አንዲት ሴት ነበረች። እርሷም ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ልትወልድም ምጥ ይዟት ተጨንቃ ትጮኻለች። ሌላም ምልክት በሰማይ ተከሠተ፤ እነሆ ታላቅ ቀይ ዘንዶ ታየ፤ ሰባት ራሶችና ዐሥር ቀንዶችም ነበሩት፤ በራሶቹም ላይ ሰባት ዘውዶች ነበሩ፤ በጅራቱም የሰማይን ከዋክብት ሲሶ እየሳበ ወደ ምድር ጣላቸው። ከዚያም ዘንዶው ሴቲቱ በምትወልድበት ጊዜ ሕፃንዋን ለመዋጥ ልትወልድ በተቃረበችው ሴት ፊት ቆመ። አሕዛብንም ሁሉ በብረት በትር የሚገዛቸውን ወንድ ልጅ ወለደች፤ ልጇም ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ። ሴቲቱም ለአንድ ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀን በዚያ እንዲመግቡአት በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደነበረው ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች። በሰማይም ጦርነት ተነሣ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ፤ አልቻላቸውምም፤ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ታላቁም ዘንዶ ወደ ታች ተጣለ፤ ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፥ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ፤ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።