መዝሙር 81:1-10
መዝሙር 81:1-10 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብርታታችን ለሆነው አምላክ በደስታ ዘምሩ፤ ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ። ዝማሬውን ጀምሩ፤ ከበሮውን ምቱ፤ በበገናና በመሰንቆ ጥዑም ዜማ አሰሙ። በሙሉ ጨረቃ፣ በክብረ በዓላችን ዕለት፣ በወሩ መግቢያ፣ ጨረቃ ስትወለድ መለከት ንፉ፤ ይህ ለእስራኤል የተሰጠ ሥርዐት፣ የያዕቆብም አምላክ ድንጋጌ ነውና። ሙሉ ለሙሉ ግብፅን ለቅቆ በወጣ ጊዜ፣ ይህን ለዮሴፍ ደነገገለት፤ በማላውቀውም ቋንቋ እንዲህ ሲል ሰማሁ፤ “ትከሻውን ከሸክም ገላገልሁት፤ እጁንም ቅርጫት ከመያዝ አሳረፍሁ። በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ፤ እኔም ታደግሁህ፤ በነጐድጓድ መሰወሪያ ውስጥ መለስሁልህ፤ በመሪባ ውሃ ዘንድ ፈተንሁህ። ሴላ “ሕዝቤ ሆይ፤ ሳስጠነቅቅህ ስማኝ፤ እስራኤል ሆይ፤ ምነው ብታደምጠኝ! በአንተ ዘንድ ባዕድ አምላክ አይኑር፤ ለሌላም አምላክ አትስገድ። ከግብፅ ምድር ያወጣሁህ፣ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ነኝ፤ አፍህን በሰፊው ክፈተው፤ እኔም እሞላዋለሁ።
መዝሙር 81:1-10 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ለመከታችን ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ! ለያዕቆብ አምላክ እልል በሉ! መዝሙር ለመዘመር ተነሡ፤ ከበሮም ምቱ፤ በበገናና በመሰንቆ ደስ የሚያሰኝ ዜማ አሰሙ። ለበዓሉ ክብር መለከት ንፉ፤ አዲስ ጨረቃ ስትወጣና ሙሉ ጨረቃ ስትሆን ይህንኑ አድርጉ። ይህ ለእስራኤል የተደነገገ፥ የያዕቆብ አምላክ የሰጠው ሥርዓት ነው። እርሱ ይህን ትእዛዝ ለዮሴፍ ልጆች የሰጣቸው ከግብጽ ምድር በወጡ ጊዜ ነው። ያልታወቀ ድምፅ እንዲህ ሲል እሰማለሁ፤ “እኔ ከትከሻችሁ ሸክምን አወረድኩላችሁ፤ የጡቡን ሸክም ከላያችሁ እንድትጥሉት አደረግሁ፤ በመከራ ላይ በነበራችሁበት ጊዜ ጠራችሁኝ፤ እኔም አዳንኳችሁ፤ ከመሰወሪያ ስፍራዬ፥ ከሞገድ ውስጥ ሰማኋችሁ፤ በክርክር ምንጮች አጠገብ ፈተንኳችሁ። ሕዝቤ ሆይ! የማስጠንቀቂያ ንግግሬን ስማ! እስራኤል ሆይ! ብታዳምጡኝ ምንኛ መልካም ነበር! ባዕድ አምላክ አይኑርህ፤ እርሱንም አታምልክ። ከግብጽ ምድር ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ፤ ጠይቅ እንጂ የሚያስፈልግህን ሁሉ እሰጥሃለሁ።
መዝሙር 81:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ለኃይላችን ለእግዚአብሔር በደስታ ዘምሩ፥ ለያዕቆብም አምላክ እልል በሉ። ዝማሬውን አንሡ ከበሮንም ስጡ፥ ደስ የሚያሰኘውን በገና ከመሰንቆ ጋር፥ በመባቻ ቀን በከፍተኛው በዓላችን ቀን መለከትን ንፉ፥ ለእስራኤል ሥርዓቱ ነውና፥ የያዕቆብም አምላክ ፍርድ። ከግብጽ በወጣ ጊዜ ለዮሴፍ ምስክር አድርጎ አቆመው። ያላወቅሁትን ቋንቋ ሰማሁ። ጫንቃውን ከሸክም፥ እጆቹንም በቅርጫት ከመገዛት አራቅሁ። በመከራህ ጊዜ ጠራኸኝ አዳንሁህም፥ ከተሰወረ የሞገድ ስፍራ መለስሁልህ፥ በክርክር ውኃ ዘንድም ፈተንሁህ። ሕዝቤ ሆይ፥ ስማኝ እነግርሃለሁም፥ እስራኤል ሆይ፥ ምነው በሰማኸኝ! አንተስ ብትሰማኝ ሌላ አምላክ አይሆንልህም፥ ለሌላ አምላክም አትሰግድም።