መዝሙር 71:20-24
መዝሙር 71:20-24 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብዙ መከራና ጭንቅ ብታሳየኝም፣ ሕይወቴን እንደ ገና ታድሳለህ፤ ከምድር ጥልቅም፣ እንደ ገና ታወጣኛለህ። ክብሬን ትጨምራለህ፤ ተመልሰህም ታጽናናኛለህ። አምላኬ ሆይ፤ ስለ ታማኝነትህ፣ በበገና አመሰግንሃለሁ፤ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ፤ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። ዝማሬ በማቀርብልህ ጊዜ ከንፈሮቼ በደስታ ይሞላሉ፤ አንተ የተቤዠሃትም ነፍሴ እልል ትላለች። አንደበቴ ስለ ጽድቅህ፣ ቀኑን ሙሉ ያወራል፤ የእኔን መጐዳት የሚፈልጉ፣ ዐፍረዋልና፤ ተዋርደዋልም።
መዝሙር 71:20-24 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በብዙ ችግርና መከራ እንድሠቃይ አድርገኸኛል፤ ሆኖም እንደገና ከመሬቱ ጥልቅ ጒድጓድ አውጥተህ አዲስ ሕይወትን ትሰጠኛለህ። ክብሬን ታሳድጋለህ፤ እንደገናም ታጽናናኛለህ። አምላኬ፥ የእስራኤል ቅዱስ ሆይ! ስለ ታማኝነትህ በበገና አመሰግንሃለሁ፤ በመሰንቆም የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ። ያዳንከኝ እኔ የምስጋና መዝሙር ስዘምርልህ። ከንፈሮቼ የደስታ ጩኸት ይጮኻሉ። ሊጐዱኝ የሚፈልጉ ስላፈሩና ግራ ስለ ተጋቡ አንደበቴ ቀኑን ሙሉ ስለ እውነተኛ ርዳታህ ይናገራል።
መዝሙር 71:20-24 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ብዙ ጭንቀትንና መከራን አሳይተኸኛልና፥ ተመለስህ ሕያውም አደረግኸኝ፥ ከምድር ጥልቅም እንደገና አወጣኸኝ። ክብሬን ታበዛለህ፥ ተመልሰህም ደስ ታሰኘኛለህ፥ እኔም በበገና ስለ እውነትህ አመሰግንሃለሁ፥ የእስራኤል ቅዱስ አምላክ ሆይ፥ በመሰንቆ እዘምርልሃለሁ። ዝማሬን ባቀርብሁልህ ጊዜ ከንፈሮቼ ደስ ይላቸዋል፥ አንተ ያዳንሃትም ነፍሴ እንዲሁ። ጉዳቴን የሚሹ ባፈሩና በተነወሩ ጊዜ አንደበቴ ደግሞ ሁልጊዜ ጽድቅህን ይናገራል።