መዝሙር 7:12-17
መዝሙር 7:12-17 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ሰው በንስሓ የማይመለስ ከሆነ ግን፣ ሰይፉን ይስላል፤ ቀስቱን ይገትራል። የሚገድሉ ጦር ዕቃዎቹን አሰናድቷል፤ የሚንበለበሉትን ፍላጻዎቹንም አዘጋጅቷል። ክፋትን እያማጠ ያለ ሰው፣ ቅጥፈትን አርግዞ፣ ሐሰትን ይወልዳል። ጕድጓድ ምሶ ዐፈሩን የሚያወጣ፣ በአዘጋጀው ጕድጓድ ራሱ ይገባበታል። ተንኰሉ ወደ ራሱ ይመለሳል፤ ዐመፃውም በገዛ ዐናቱ ላይ ይወርዳል። ስለ ጽድቁ ለእግዚአብሔር ምስጋና አቀርባለሁ፤ የልዑል እግዚአብሔርን ስም በመዝሙር አወድሳለሁ።
መዝሙር 7:12-17 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ባትመለሱ ግን ሰይፉን ይመዝዛል፥ ቀስቱን ገተረ አዘጋጀም፤ የሚገድል መርዝንም አዘጋጀበት፤ ፍላጻዎቹንም የሚቃጠሉ አደረገ። እነሆ፥ ዐመፀኛ በዐመፁ ተጨነቀ፤ ጭንቅን ፀነሰ፤ ኀጢአትንም ወለደ። ጕድጓድንም ማሰ፥ ቈፈረም። ባደረገውም ጕድጓድ ይወድቃል። ጉዳቱ በራሱ ይመለሳል፥ ዐመፃውም በአናቱ ላይ ትወርዳለች። እግዚአብሔርን እንደ ጽድቁ መጠን አመሰግናለሁ፥ ለልዑል እግዚአብሔርም ስም እዘምራለሁ።
መዝሙር 7:12-17 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ክፉዎች ከክፋታቸው የማይመለሱ ከሆነም፥ እግዚአብሔር ሰይፉን ይስላል፤ ቀስቱንም ያመቻቻል። የሚገድሉ የጦር መሣሪያዎችን ያበጃል፤ እንደ እሳት የሚንበለበሉ ፍላጻዎችንም ያዘጋጃል። ኃጢአተኞች በደልን ይፀንሳሉ፤ ተንኰልን ያረግዛሉ፤ ውሸትን ይወልዳሉ። ለሌሎች ወጥመድ የሚሆን ጥልቅ ጒድጓድ ይቈፍራሉ፤ ነገር ግን በቈፈሩት ጒድጓድ ውስጥ እነርሱ ራሳቸው ይገቡበታል። የሚያመጡት ችግር በራሳቸው ላይ ይደርሳል፤ በክፉ ድርጊታቸውም ዐናታቸው ይፈጠፈጣል። ስለ እውነተኛነቱ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ ለልዑል አምላክ ስም የምስጋና መዝሙር አቀርባለሁ።