መዝሙር 56:1-13
መዝሙር 56:1-13 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ የሰዎች መረገጫ ሆኛለሁና ማረኝ፤ ቀኑንም ሙሉ በውጊያ አስጨንቀውኛል። ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በላዬ ቆሙ፤ በትዕቢት የሚዋጉኝ ብዙዎች ናቸውና። ፍርሀት በሚይዘኝ ጊዜ፣ እምነቴን በአንተ ላይ አደርጋለሁ። ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ በእግዚአብሔር ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ቀኑን ሙሉ ቃሌን ያጣምሙታል፤ ዘወትርም ሊጐዱኝ ያሤራሉ። ይዶልታሉ፤ ያደባሉ፤ ርምጃዬን ይከታተላሉ፤ ነፍሴንም ለማጥፋት ይሻሉ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ከቶ እንዳያመልጡ፣ ሕዝቦቹን በቍጣህ ጣላቸው። ሰቈቃዬን መዝግብ፤ እንባዬን በዕቃህ አጠራቅም፤ ሁሉስ በመዝገብህ የተያዘ አይደለምን? ወደ አንተ በተጣራሁ ቀን፣ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ በዚህም፣ አምላክ ከጐኔ መቆሙን ዐውቃለሁ። ቃሉን በማመሰግነው አምላክ፣ ቃሉን በማመሰግነው በእግዚአብሔር፣ በአምላክ ታምኛለሁ፤ አልፈራም፤ ሥጋ ለባሽ ምን ሊያደርገኝ ይችላል? እግዚአብሔር ሆይ፤ የአንተ ስእለት አለብኝ፤ የማቀርብልህም የምስጋና መሥዋዕት ነው፤ በሕያዋን ብርሃን፣ በእግዚአብሔር ፊት እመላለስ ዘንድ፣ ነፍሴን ከሞት፣ እግሬንም ከመሰናክል አድነሃልና።
መዝሙር 56:1-13 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ሰዎች ስለሚያስጨንቁኝና ጠላቶቼም ዘወትር ስለሚያሳድዱኝ ማረኝ። ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ ያጠቁኛል፤ ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፥ የሚያሳድዱኝ ብዙዎች ናቸው። ፍርሀት ቢይዘኝ እንኳ በአንተ እተማመናለሁ። በእግዚአብሔር ስለምታመን አልፈራም፤ ስለ ሰጠኝም ተስፋ አመሰግነዋለሁ፤ በእግዚአብሔር ስለምታመን ከቶ ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል? ጠላቶቼ ቀኑን ሙሉ በእኔ ላይ ስሕተት ለማግኘት ይጥራሉ፤ ዘወትር እኔን ለመጒዳት ያሤራሉ። ተሰባስበው ይሸምቁብኛል፤ እርምጃዬን ሁሉ ይከታተላሉ፤ ሕይወቴንም ለማጥፋት ያደባሉ። አምላክ ሆይ! በምንም መንገድ እንዲያመልጡ አታድርጋቸው! በቊጣህ ሕዝቦችን አዋርዳቸው። የመንከራተት ቀኖቼን ቈጥረሃል፤ እንባዎቼንም በጠርሙስ ውስጥ አስቀምጠሃል፤ እያንዳንዳቸውንም መዝግበሃል። እኔ ወደ አንተ በምጣራበት ቀን፥ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር መሆኑንም በዚህ ዐውቃለሁ። ይህም ከእኔ ጋር የሆነው እግዚአብሔር፥ ቃሉን የማመሰግነውና የማከብረው አምላክ ነው። በእርሱም ስለምታመን አልፈራም፤ ሰውስ ከቶ ምን ሊያደርገኝ ይችላል? አምላክ ሆይ! እኔ ራሴ ለአንተ የስእለት ግዴታ ገብቼአለሁ፤ ስእለቴን ከምስጋና መሥዋዕት ጋር አቀርባለሁ። አንተ ከሞት አድነኸኛል፤ ተሰናክዬ እንዳልወድቅም ረድተኸኛል፤ ስለዚህ በሕያዋን ላይ በሚያበራው ብርሃን በእግዚአብሔር ፊት እመላለሳለሁ።
መዝሙር 56:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፥ ሁልጊዜም ተዋጊ አስጨንቆኛል። የሚዋጉኝ በዝተዋልና ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ። እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ። በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሥጋ ምን ያደርገኛል? ሁልጊዜ ቃሎቼን ይጠመዝዙብኛል፥ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው። ይሸምቁብኛል ይሸሸጋሉ፥ ተረከዜን ይከታተላሉ፥ ነፍሴንም ለማጥፋት ይጠብቃሉ። መቼም አታድናቸውም! አቤቱ አሕዛብን በቁጣ ጣላቸው። አምላክ ሆይ፥ መዋተቴን ነገርሁህ፥ እንባዬን በአቁማዳ ውስጥ አኑር። በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፥ አንተ አምላኬ ከእኔ ጋር እንደሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ። በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፥ በጌታ ቃሉን እወድሳለሁ። በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፥ ሰው ምን ያደርገኛል? አቤቱ፥ በአንተ ዘንድ ሰእለት አለብኝ፥ የምስጋና መሥዋዕት አቀርብልሀለሁ፥