መዝሙር 37:1-6
መዝሙር 37:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
አቤቱ፥ በመዓትህ አትቅሠፈኝ፥ በመቅሠፍትህም አትገሥጸኝ። ፍላጾችህ ወግተውኛልና፥ እጅህንም በእኔ ላይ አክብደህብኛልና። ከቍጣህ ፊት የተነሣ ለሥጋዬ ድኅነት የለውም፤ ከኀጢአቴም ፊት የተነሣ ለአጥንቶቼ ሰላም የላቸውም። ኀጢአቴ ከራሴ ጠጕር በዝቷልና፥ እንደ ከባድ ሸክምም በላዬ ከብዶአልና። ከስንፍናዬም ፊት የተነሣ አጥንቶቼ ሸተቱ፥ በሰበሱም፤ እጅግ ጐሰቈልሁ፥ ጐበጥሁም፥ ሁልጊዜም በትካዜ እመላለሳለሁ፤
መዝሙር 37:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤ በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ። በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤ ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ ያንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል።
መዝሙር 37:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ፤ ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና። እንደ ሣር ቶሎ ይደርቃሉ፤ እንደ ቅጠልም ጠውልገው ይረግፋሉ። በእግዚአብሔር ታምነህ መልካምን አድርግ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራለህ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ እርሱም የልብህን ፍላጎት ሁሉ ይሰጥሃል። አካሄድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ይረዳሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን የጉዳይህንም ትክክለኛነት እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል።
መዝሙር 37:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፥ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። በጌታ ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። በጌታ ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለጌታ አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣዋል።