የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

መዝሙር 37:1-40

መዝሙር 37:1-40 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ዐመፀኞችን በማየት አትሸበር፤ በክፉ አድራጊዎችም አትቅና፤ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፤ እንደ ለምለም ቅጠልም ይጠወልጋሉ። በእግዚአብሔር ታመን፤ መልካምንም አድርግ፤ በምድሪቱ ተቀመጥ፤ ዘና ብለህ ተሰማራ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ያከናውንልሃል፤ ጽድቅህን እንደ ብርሃን፣ ያንተን ፍትሕ እንደ ቀትር ፀሓይ ያበራዋል። በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ በል፤ በትዕግሥትም ተጠባበቀው፤ መንገዱ በተቃናለት፣ ክፋትንም በሚሸርብ ሰው ልብህ አይሸበር። ከንዴት ተቈጠብ፤ ቍጣንም ተወው፤ ወደ እኵይ ተግባር እንዳይመራህ አትከፋ። ክፉ ሰዎች ይጠፋሉና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ የሚያደርጉ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ለአፍታ እንጂ፣ ክፉ ሰው አይዘልቅም፤ ስፍራውንም ብታሥሥ አታገኘውም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ። ክፉዎች በጻድቃን ላይ ያሤራሉ፤ ጥርሳቸውንም ያፋጩባቸዋል። እግዚአብሔር ግን ይሥቅባቸዋል፣ ቀናቸው እንደ ደረሰ ያውቃልና። ድኾችንና ችግረኞችን ለመጣል፣ አካሄዳቸው ቀና የሆነውንም ለመግደል፣ ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፤ ቀስታቸውንም ገተሩ። ሰይፋቸው የገዛ ልባቸውን ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። የጻድቅ ጥቂት ሀብት፣ ከክፉዎች ብዙ ጥሪት ይበልጣል። የክፉዎች ክንድ ይሰበራልና፣ ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ደግፎ ይይዛቸዋል። እግዚአብሔር የንጹሓንን የሕይወት ዘመን ያውቃል፤ ርስታቸውም ለዘላለም ይኖራል። በክፉ ጊዜ ዐንገት አይደፉም፤ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ መስክ ውበት ይሆናሉ፤ ይጠፋሉ፤ እንደ ጢስም ተነው ይጠፋሉ። ኀጢአተኛ ይበደራል፤ መልሶም አይከፍልም፤ ጻድቅ ግን ይቸራል። እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እርሱ የሚረግማቸው ግን ይጠፋሉ። የሰው አካሄድ በእግዚአብሔር ይጸናል፤ በመንገዱ ደስ ይለዋል። ቢሰናከልም አይወድቅም፣ እግዚአብሔር በእጁ ደግፎ ይይዘዋልና። ጕልማሳ ነበርሁ፤ አሁን አርጅቻለሁ፤ ነገር ግን ጻድቅ ሲጣል፣ ዘሩም እንጀራ ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ቸር ነው፤ ያበድራልም፤ ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ። ከክፉ ራቅ፤ መልካሙንም አድርግ፣ ለዘላለምም ትኖራለህ። እግዚአብሔር ፍትሕን ይወድዳልና፣ ታማኞቹንም አይጥልም፤ ለዘላለምም ይጠብቃቸዋል፤ የኀጢአተኛው ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ይናገራል፤ አንደበቱም ፍትሐዊ ነገር ያወራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ አለ፤ አካሄዱም አይወላገድም። ክፉዎች ጻድቁን ይከታተሉታል፤ ሊገድሉትም ይሻሉ። እግዚአብሔር ግን በእጃቸው አይጥለውም፤ ፍርድ ፊት ሲቀርብም አሳልፎ አይሰጠውም። እግዚአብሔርን ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፤ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ። ክፉና ጨካኙን ሰው፣ እንደ ሊባኖስ ዝግባ ለምልሞ አየሁት፤ ዳግመኛ በዚያ ሳልፍ፣ እነሆ፣ በቦታው አልነበረም፤ ብፈልገውም አልተገኘም። ንጹሓንን ልብ በል፤ ቅኑንም አስተውል፤ የሰላም ሰው ተስፋ አለውና። ኀጢአተኞች ግን በአንድነት ይጠፋሉ፤ የክፉዎችም ዘር ይወገዳል። የጻድቃን ድነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ በመከራ ጊዜም መጠጊያቸው እርሱ ነው። እግዚአብሔር ይረዳቸዋል፤ ይታደጋቸዋልም፤ ከክፉዎች እጅ ነጥቆ ያወጣቸዋል፤ እርሱን መጠጊያ አድርገዋልና ያድናቸዋል።

መዝሙር 37:1-40 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

በክፉዎች ምክንያት አትበሳጭ፤ ኃጢአት በሚሠሩም አትቅና። እንደ ሣር ቶሎ ይደርቃሉ፤ እንደ ቅጠልም ጠውልገው ይረግፋሉ። በእግዚአብሔር ታምነህ መልካምን አድርግ፤ በምድሪቱም በሰላም ትኖራለህ። በእግዚአብሔር ደስ ይበልህ፤ እርሱም የልብህን ፍላጎት ሁሉ ይሰጥሃል። አካሄድህን ለእግዚአብሔር ዐደራ ስጥ፤ በእርሱ ታመን፤ እርሱም ይረዳሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን የጉዳይህንም ትክክለኛነት እንደ ቀትር ፀሐይ ያበራዋል። በትዕግሥት ጸንተህ እግዚአብሔር የሚያደርገውን ለማየት ተጠባበቅ፤ ሌሎች ሰዎች ክፉ ሐሳባቸው ቢሳካላቸው አትበሳጭ። ቊጣ ወደ ክፉ ነገር ስለሚያመራ። ራስህን ከቊጣ መልስ፤ ከንዴትም ተጠበቅ፤ ክፉ አድራጊዎች ይገደላሉ፤ በእግዚአብሔር የሚታመኑ ግን ምድርን ይወርሳሉ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ክፉ አድራጊዎች ፈጥነው ይጠፋሉ፤ ብትፈልጋቸው እንኳ አታገኛቸውም። ትሑቶች ምድርን ይወርሳሉ፤ ብልጽግናንና ሰላምን በማግኘት ይደሰታሉ። ክፉ ሰው ደጉን ሰው ለማጥፋት ያሳድምበታል፤ በጥላቻም ጥርሱን ያፋጭበታል። ክፉዎች ሰዎች የሚጠፉበት ቀን እንደ ተቃረበ ስለሚያውቅ እግዚአብሔር በእነርሱ ይስቃል። ክፉዎች፥ ድኾችንና ምስኪኖችን ለመግደል፥ ደግ ሥራ የሚሠሩትንም ለማረድ፥ ሰይፋቸውን ይመዛሉ፤ ቀስታቸውን ያዘጋጃሉ። ነገር ግን ሰይፋቸው የራሳቸውን ልብ ይወጋል፤ ቀስታቸውም ይሰበራል። ከክፉ ሰው ብዙ ሀብት ይልቅ፥ የደግ ሰው ጥቂት ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ኀይል ይሰበራል ጻድቃንን ግን እግዚአብሔር ያበረታቸዋል። እግዚአብሔር ታዛዦቹን በየቀኑ ይጠብቃቸዋል፤ የሰጣቸውም ስጦታ ለዘለዓለም ከእነርሱ ጋር ይኖራል። ክፉ ቀን ሲመጣ ችግር አይደርስባቸውም፤ በራብ ዘመንም በቂ ምግብ በማግኘት ይጠግባሉ። ክፉዎች ግን ይጠፋሉ፤ የእግዚአብሔር ጠላቶች እንደ በረሓ አበባ ይረግፋሉ፤ እንደ ጢስም ከዓይን ይሰወራሉ። ክፉ ሰው የተበደረውን አይመልስም፤ ደግ ሰው ግን በልግሥና ይሰጣል። እግዚአብሔር የባረካቸው ምድርን ይወርሳሉ፤ እግዚአብሔር የረገማቸው ግን ይጠፋሉ። እግዚአብሔር በሰው አካሄድ ከተደሰተ የእርምጃውን ትክክለኛነት ያረጋግጥለታል። እግዚአብሔር በእጁ ስለሚደግፈው ቢደናቀፍም አይወድቅም። ከወጣትነት እስከ ሽምግልና ኖሬአለሁ፤ ታዲያ፥ እግዚአብሔር ደጉን ሰው ሲተወው፥ ልጆቹም ምግብ አጥተው ሲለምኑ፥ ከቶ አይቼ አላውቅም። ደግ ሰው ሁልጊዜ በልግሥና ይሰጣል፤ እንዲሁም ያበድራል፤ ልጆቹም የተባረኩ ይሆናሉ። ከክፉ ነገር ራቅ፤ መልካም ነገርንም አድርግ፤ አንተም በሰላም ለዘለዓለም ትኖራለህ። እግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድን ይወዳል፤ ታማኞቹንም አይተዋቸውም፤ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል፤ የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርስዋም ለዘለዓለም ይኖራሉ። ከጻድቅ ሰው አፍ ጥበብ ይወጣል፤ አንደበቱም ፍትሕን ይናገራል። የአምላኩም ሕግ በልቡ ነው፤ እግሩም አይደናቀፍም። ክፉ ሰው በጻድቁ ላይ ይሸምቃል፤ ሊገድለውም ይፈልጋል። እግዚአብሔር ግን በጠላቱ እጅ አሳልፎ አይሰጠውም፤ በአደባባይ ክርክርም እንዲሸነፍ አያደርገውም። ተስፋህን በእግዚአብሔር ላይ አድርግ፤ ትእዛዙንም ፈጽም፤ እርሱም ምድርን በማውረስ ያከብርሃል፤ ክፉዎች ሲወገዱም ታያለህ። አንድ ጨካኝና ክፉ ሰው በሀገሩ መሬት እንደ ለመለመ ዛፍ ተጠናክሮ አየሁ። ነገር ግን ቈይቼ ብመለስ ከስፍራው አጣሁት፤ ብፈልገውም ላገኘው አልቻልኩም። ደጉን ሰው ተመልከት፤ ቅን የሆነውንም ሰው እይ፤ ሰላም ወዳድ ሰው ዘር ይወጣለታል። ኃጢአተኞች ግን ፈጽሞ ይደመሰሳሉ፤ ዘራቸውም ይጠፋል። የጻድቃን መዳን የሚመጣው ከእግዚአብሔር ነው፤ በችግር ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። እንዲጠብቃቸው በእርሱ ስለ ተማጸኑም ይረዳቸዋል፤ ያድናቸዋልም፤ ከክፉዎችም እጅ ይታደጋቸዋል።

መዝሙር 37:1-40 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

በክፉዎች ላይ አትቅና፥ ዓመፃንም በሚያደርጉ ላይ አትቅና፥ እንደ ሣር ፈጥነው ይደርቃሉና፥ እንደ ለመለመ ቅጠልም ይረግፋሉና። በጌታ ታመን፥ መልካምንም አድርግ፥ በምድርም ተቀመጥ፥ ታምነህም ተሰማራ። በጌታ ደስ ይበልህ፥ የልብህንም መሻት ይሰጥሃል። መንገድህን ለጌታ አደራ ስጥ፥ በእርሱም ታመን፥ እርሱም ያደርግልሃል። ጽድቅህን እንደ ብርሃን። ፍርድህንም እንደ ቀትር ያመጣዋል። በጌታ ጽና በተዕግሥትም ጠብቀው። መንገዱም በቀናችለትና በሚያደባ ሰው አትቅና። ከቁጣ ራቅ መዓትንም ተው፥ እንዳትበድል አትቅና። ክፉ አድራጊዎች ይጠፋሉና፥ በጌታ ተስፋ የሚያደርጉ ግን እነርሱ ምድርን ይወርሳሉ። ጥቂት ጊዜ ቆይቶ፥ ክፉ አድራጊ አይኖርም፥ ትፈልገዋለህ ቦታውንም አታገኝም። ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፥ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ክፉ በጻድቁ ላይ ያደባል፥ ጥርሱንም በእርሱ ላይ ያንገጫግጫል። ጌታ ግን ይሥቅበታል፥ ቀኑ እንደሚደርስ አይቶአልና። ክፉዎች ሰይፋቸውን መዘዙ፥ ቀስታቸውንም ገተሩ ድሀውንና ችግረኛውን ይጥሉ ዘንድ፥ ልበ ቅኖችንም ይወጉ ዘንድ፥ ሰይፋቸው ወደ ልባቸው ይግባ፥ ቀስታቸውም ይሰበር። በጻድቅ ዘንድ ያለው ጥቂት ነገር ከብዙ ክፉዎች ሀብት ይበልጣል። የክፉዎች ንድ ትሰበራለችና፥ ጌታ ግን ጻድቃንን ይደግፋቸዋል። የንጹሓንን ቀኖች ጌታ ያውቃል፥ ርስታቸውም ለዘለዓለም ትሆናለች፥ በክፉ ዘመንም አያፍሩም፥ በራብ ዘመንም ይጠግባሉ። ክፉዎቸ ግን ይጠፋሉ፥ የጌታ ጠላቶች እንደ መስክ ውበት፥ እንደ ጢስም ተንነው ይጠፋሉ። ክፉ ይበደራል አይከፍልምም፥ ጻድቅ ግን ይራራል ይሰጣልም። እርሱን የሚባርኩት ምድርን ይወርሳሉና፥ የሚረግሙት ግን ይጠፋሉ። መንገዱን በወደደ ጊዜ፥ የሰው አካሄድ በጌታ ይጸናል። ቢወድቅም አይጣልም፥ ጌታ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። ጐለመስሁ አረጀሁም፥ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፥ ለዘለዓለምም ትኖራለህ። ጌታ ፍርድን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፥ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፥ የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘለዓለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ያናገራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም። ክፉ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል። ጌታ ግን በእጁ አይተወውም፥ በፍርድም እንዲሸነፍ አይፈቅድም። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፥ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ። ክፉን በጭቆና ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት፥ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፥ ለሰላም ሰው ተተኪ ይወጣለታልና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፥ የክፉዎቸ ዘር ይጠፋል። የጻድቃን መድኃኒታቸው በጌታ ዘንድ ነው፥ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። ጌታ ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከከፉዎችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ በእርሱ ታምነዋልና።