መዝሙር 33:12-22
መዝሙር 33:12-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፥ ከንፈሮችህም ሽንገላን እንዳይናገሩ። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፤ ሰላምን ሻት፥ ተከተላትም። የእግዚአብሔር ዐይኖች ወደ ጻድቃኑ፥ ጆሮቹም ወደ ልመናቸው ናቸውና። መታሰቢያቸውን ከምድር ያጠፋ ዘንድ የእግዚአብሔር ፊት ክፉን በሚያደርጉ ላይ ነው። ጻድቃን ጮኹ፥ እግዚአብሔርም ሰማቸው፥ ከመከራቸውም ሁሉ አዳናቸው። እግዚአብሔር በልባቸው የዋሃን ለሆኑ ቅርብ ነው፥ በመንፈስ ትሑታን የሆኑትንም ያድናቸዋል። የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፥ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል። እግዚአብሔር አጥንቶቻቸውን ሁሉ ይጠብቃል፥ ከእነርሱም አንድ አይሰበርም። የኃጥእ ሞቱ ክፉ ነው ጽድቅንም የሚጠሉ ይጸጸታሉ። የባሪያዎቹን ነፍስ እግዚአብሔር ይቤዣል፥ በእርሱም የሚያምኑ ሁሉ አይጸጸቱም።
መዝሙር 33:12-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብፁዕ ነው፤ እግዚአብሔር አምላኩ የሆነው ሕዝብ፣ ለርስቱ የመረጠውም ወገን፤ እግዚአብሔር ከሰማይ ይመለከታል፤ የሰውንም ልጆች ሁሉ ያያል፤ ከማደሪያው ቦታ ሆኖ፣ በምድር ወደሚኖሩት ሁሉ ይመለከታል፤ እርሱ የሁሉን ልብ የሠራ፣ የሚያደርጉትን ሁሉ የሚያስተውል ነው። ንጉሥ በሰራዊቱ ታላቅነት አይድንም፤ ጀግናም በኀይሉ ብርታት አያመልጥም። በፈረስ ድል አደርጋለሁ ማለት ከንቱ ተስፋ ነው፤ በብርቱ ጕልበቱም ማንንም አያድንም። እነሆ፤ የእግዚአብሔር ዐይኖች በሚፈሩት ላይ ናቸው፤ ምሕረቱንም በሚጠባበቁት ላይ አትኵረዋል። በዚህም ነፍሳቸውን ከሞት ያድናል፤ በራብ ዘመንም በሕይወት ያኖራቸዋል። ነፍሳችን እግዚአብሔርን ተስፋ ታደርጋለች፤ እርሱ ረዳታችንና ጋሻችን ነው። ልባችን በርሱ ደስ ይለዋል፤ በቅዱስ ስሙ ታምነናልና። እግዚአብሔር ሆይ፤ ተስፋ ባደረግንህ፣ በእኛ ላይ ምሕረትህ ትሁን።
መዝሙር 33:12-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር አምላኩ የሆነለትና እግዚአብሔር የራሱ አድርጎ የመረጠው ሕዝብ የተባረከ ነው! እግዚአብሔር ከሰማይ ሆኖ ይመለከታል፤ የሰውንም ዘር ሁሉ ያያል፤ በዙፋኑ ላይ ሆኖ በምድር ላይ ያሉትን ሁሉ ያያል። የሁላቸውንም ልብ የሠራ እርሱ ነው የሚያደርጉትን ሁሉ ይመለከታል። ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፤ አርበኛም በከፍተኛ ኀይሉ አያመልጥም። ፈረስ ለማዳን ከንቱ ተስፋ ነው፤ ከዚያ ሁሉ ኀይሉ ጋር ሊያድን አይችልም። እግዚአብሔር የሚፈሩትንና ዘለዓለማዊ ፍቅሩ ተስፋቸው የሆነውን ይመለከታል። ይህም የሚሆነው ከሞት ሊያድናቸውና ከራብም ሊጠብቃቸው ነው። እግዚአብሔርን በተስፋ እንጠብቀዋለን ረዳታችንና ጋሻችን እርሱ ነው። በቅዱስ ስሙም ስለምንታመን በእርሱ ደስ ይለናል። እግዚአብሔር ሆይ! ተስፋችንን በአንተ እንዳደረግን ዘላቂ ፍቅርህ በእኛ ላይ ይሁን።
መዝሙር 33:12-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ አምላኩ የሚሆንለት ሕዝብ ምስጉን ነው፥ እርሱ ለርስቱ የመረጠው ሕዝብ። ጌታ ከሰማይ ተመለከተ፥ የሰውንም ልጆች ሁሉ አየ። ከማደሪያው ቦታ ሆኖ በምድር ወደሚኖሩ ሁሉ ተመለከተ፥ እርሱ ብቻውን ልባቸውን የሠራ ሥራቸውንም ሁሉ የሚያስተውል። ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፥ ኃያልም በጉልበቱ አያመልጥም። ፈረስም ከንቱ ነው፥ አያድንም፥ በኃይሉም ብዛት አያስመልጥም። እነሆ፥ የጌታ ዐይኖች ወደሚፈሩት ናቸው፥ በቸርነቱም ወደሚታመኑ፥ ነፍሳቸውን ከሞት ያድን ዘንድ፥ በራብም ጊዜ በሕይወት ይጠብቃቸው ዘንድ። ነፍሳችን ጌታን ተስፋ ታደርገዋለች፥ ረዳታችንና ጋሻችን እርሱ ነውና። ልባችን በእርሱ ደስ ይለዋልና፥ በቅዱስ ስሙም ታምነናልና። አቤቱ፥ ቸርነትህ በላያችን ትሁን፥ በአንተ እንደ ታመንን።