መዝሙር 26:2-12
መዝሙር 26:2-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ክፉዎች ሥጋዬን ይበሉ ዘንድ በቀረቡ ጊዜ፥ የሚያሠቃዩኝ እነዚያ ጠላቶቼ ደከሙ፥ ወደቁም። ሠራዊትም ቢጠላኝ ልቤ አይፈራብኝም፤ ሠራዊትም ቢከቡኝ በእርሱ እተማመናለሁ። እግዚአብሔርን አንዲት ነገር ለመንሁት፥ እርስዋንም እሻለሁ፤ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ፥ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም አይ ዘንድ፥ በቤተ መቅደሱም አገለግል ዘንድ። በመከራዬ ቀን በድንኳኑ ሸሽጎኛልና፥ በድንኳኑም መሸሸጊያ ሰውሮኛልና፥ በዓለትም ላይ ከፍ ከፍ አድርጎኛልና። እነሆ፥ አሁን እግዚአብሔር በጠላቶቼ ላይ ራሴን ከፍ ከፍ አደረገ፤ ዞርሁ በድንኳኑም መሥዋዕትን ሠዋሁ፥ እልልም አልሁለት እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፥ እዘምርለትማለሁ። አቤቱ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን ቃሌን ስማኝ፤ ማረኝ፥ አድምጠኝም። ልቤ አንተን አለ፦ ፊትህን ፈለግሁ፥ አቤቱ፥ ፊትህን እሻለሁ። ፊትህን ከእኔ አትመልስ፥ ተቈጥተህ ከባሪያህ ፈቀቅ አትበል፤ ረዳት ሁነኝ፥ አትጣለኝም፥ አምላኪዬና መድኀኒቴ ሆይ፥ ቸል አትበለኝ። አባቴና እናቴ ጥለውኛልና፥ እግዚአብሔር ግን ተቀበለኝ። አቤቱ መንገድህን አስተምረኝ፥ ስለ ጠላቶቼም በቀና መንገድ ምራኝ። ለሚያስጨንቁኝ ፈቃድ አትስጠኝ፥ የዐመፅ ምስክሮች ተነሥተውብኛልና፥ ሐሰትም የዐመፅ ራስ ነው።
መዝሙር 26:2-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ ፈትነኝ፤ መርምረኝም፤ ልቤንና ውስጤን መርምር፤ ምሕረትህ ከፊቴ አልተለየምና፣ በእውነትህም ተመላለስሁ። ከማይረቡ ጋራ አልተቀመጥሁም፤ ከግብዞችም ጋራ አልተባበርሁም። የክፉዎችን ማኅበር ተጸየፍሁ፤ ከዐመፀኞችም ጋራ አልቀመጥም። እጆቼን በየዋህነት እታጠባለሁ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ መሠዊያህንም እዞራለሁ፤ የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፣ ታምራትህንም አወራ ዘንድ ነው። እግዚአብሔር ሆይ፤ የምትኖርበትን ቤት፣ የክብርህን ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። ነፍሴን ከኀጢአተኞች ጋራ፣ ሕይወቴንም ከደም አፍሳሾች ጋራ አታስወግዳት። በእነርሱ እጅ የተንኰል ዕቅድ አለ፤ ቀኝ እጃቸውም ጕቦን ያጋብሳል። እኔ ግን በተአማኒ ሕይወት እጓዛለሁ፤ አድነኝ፤ ምሕረትንም አድርግልኝ። እግሮቼ በደልዳላ ስፍራ ቆመዋል፤ በታላቅ ጉባኤ መካከልም እግዚአብሔርን እባርከዋለሁ።
መዝሙር 26:2-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሆይ! ፈትነኝ፤ ምኞቴንና ሐሳቤንም መርምር። የማያቋርጠው ፍቅርህ በዐይኖቼ ፊት ነው፤ ዘወትር የሚመራኝም የአንተ ታማኝነት ነው። ከአታላዮች ጋር አልወዳጅም፤ ከግብዞችም ጋር አልተባበርም፤ የክፉ አድራጊዎችን ጉባኤ እጠላለሁ፤ ከክፉዎችም ጋር መቀመጥ አልፈቅድም። እግዚአብሔር ሆይ! ንጹሕነቴን ለማሳየት እጆቼን እታጠባለሁ፤ መሠዊያህንም በመዞር አንተን አመልካለሁ። የምስጋና መዝሙር እየዘመርኩ፥ የአንተን ድንቅ ሥራዎች ሁሉ እናገራለሁ። እግዚአብሔር ሆይ! አንተ የምትኖርበትን ቤትና ክብርህ የሚገኝበትን ስፍራ እወዳለሁ። ደም አፍሳሾች ከሆኑ ኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን አትውሰድ፤ ሕይወቴንም አታጥፋ። እነርሱም ጣቶቻቸው ክፉ ሥራን ለመሥራት የነቁ፥ ቀኝ እጆቻቸውም በጉቦ የተሞሉ ናቸው። እኔ በበኩሌ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት እኖራለሁ፤ ምሕረትን አድርግልኝ፤ አድነኝም! እግሮቼ በተስተካከለ ምድር ላይ ቆመዋል፤ እግዚአብሔርንም በጉባኤው ሁሉ ፊት አመሰግነዋለሁ።
መዝሙር 26:2-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ፈትነኝ መርምረኝም፥ ኩላሊቴንና ልቤን መርምር። ቸርነትህ በዓይኔ ፊት ነውና፥ በእውነትህም ተመላለስሁ። ከአታላዮች ጋር አልተቀመጥሁም፥ ከአስመሳዮችም ጋር አልገባሁም። የክፉ አድራጊዎቸን ማኅበር ጠላሁ፥ ከክፉዎችም ጋር አልቀመጥም። እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፥ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ የምስጋናን ድምፅ አሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። አቤቱ፥ የቤትህን ስፍራ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። ከኃጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አታጥፋ። በእጃቸው ተንኰል አለባቸው፥ ቀኛቸውም በጉቦ ተሞልታለች። እኔ ግን በቅንነት ሄጃለሁ፥ አድነኝ ማረኝም። እግሮቼ በቅንነት ቆመዋልና፥ አቤቱ፥ በማኅበር አመሰግንሃለሁ።