መዝሙር 25:4-11
መዝሙር 25:4-11 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በከንቱ ሸንጎ አልተቀመጥሁም፥ ከዐመፀኞችም ጋር አልገባሁም። የክፉዎችን ማኅበር ጠላሁ፥ ከከዳተኞች ጋር አልቀመጥም። እጆቼን በንጽሕና አጥባለሁ፤ አቤቱ፥ መሠዊያህን እዞራለሁ፥ የምስጋናህን ቃል እሰማ ዘንድ፥ ተአምራትህንም ሁሉ እነግር ዘንድ። አቤቱ፥ የቤትህን ጌጥ የክብርህንም ማደሪያ ቦታ ወደድሁ። ከኀጢአተኞች ጋር ነፍሴን፥ ከደም ሰዎችም ጋር ሕይወቴን አትጣላት። በእጃቸው ተንኮል አለባቸው፥ ቀኛቸውም መማለጃን ተሞልታለች። እኔ ግን በየዋህነቴ እኖራለሁ፤ አቤቱ፦ አድነኝ ይቅርም በለኝ።
መዝሙር 25:4-11 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ሆይ፤ አካሄድህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ አዳኜ፣ አምላኬም ነህና፣ በእውነትህ ምራኝ፤ አስተምረኝም፤ ቀኑን ሙሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። እግዚአብሔር ሆይ፤ ምሕረትህንና ፍቅርህን ዐስብ፤ እነዚህ ከጥንት የነበሩ ናቸውና። የልጅነቴን ኀጢአት፣ መተላለፌንም አታስብብኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እንደ ቸርነትህ ብዛት፣ እንደ ምሕረትህም መጠን አስበኝ። እግዚአብሔር መልካምና ቅን ነው፤ ስለዚህ ኀጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። ዝቅ ያሉትን በፍትሕ ይመራቸዋል፤ ለትሑታንም መንገዱን ያስተምራቸዋል። ኪዳኑንና ምስክርነቱን ለሚጠብቁ፣ የእግዚአብሔር መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ፤ ኀጢአቴ ታላቅ ነውና፣ ስለ ስምህ ይቅር በልልኝ።
መዝሙር 25:4-11 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ዱካህን እንዳውቅ አድርገኝ፤ መንገድህንም አስተምረኝ። አንተ የምታድነኝ አምላኬ ነህና እውነትህን ተከትዬ እንድኖር አስተምረኝ፤ እኔ ዘወትር የምታመነው በአንተ ነው። እግዚአብሔር ሆይ! ከጥንት ጀምሮ የምታሳየውን ምሕረትና ዘለዓለማዊ ፍቅር አስብ። አምላክ ሆይ! እንደ ቸርነትህ በዘለዓለማዊ ፍቅርህ አስበኝ እንጂ የወጣትነት ኃጢአቴን ወይም በደሌን አታስብብኝ! እግዚአብሔር ደግና ቀጥተኛ ስለ ሆነ፥ ሊከተሉት የሚገባቸውን መንገድ ለኃጢአተኞች ያስተምራል። ትሑቶችንም በትክክለኛው መንገድ ይመራቸዋል፤ መንገዱንም ያስተምራቸዋል። የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትእዛዞች ለሚጠብቁ ሰዎች የእግዚአብሔር መንገዶች ሁሉ ፍቅርና ታማኝነት ናቸው። እግዚአብሔር ሆይ! ስለ ስምህ ክብር እጅግ የበዛውን ኃጢአቴን ይቅር በልልኝ።
መዝሙር 25:4-11 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ መንገድህን አመልክተኝ፥ ፈለግህንም አስተምረኝ። አንተ የመድኃኒቴ አምላክ ነህና በእውነትህ ምራኝ፥ አስተምረኝም፥ ቀኑን ሁሉ አንተን ተስፋ አድርጌአለሁ። አቤቱ፥ ምሕረትህንና ቸርነትህን አስብ፥ ከጥንት ጀምሮ ናቸውና። የልጅነቴን ኃጢአትና መተላለፍ አታስብብኝ፥ አቤቱ፥ ስለ ቸርነትህ ብዛት እንደ ምሕረትህ አስበኝ። ጌታ ቸርና ቅን ነው፥ ስለዚህ ኃጢአተኞችን በመንገድ ይመራቸዋል። ትሑታንን በፍርድ ይመራል፥ ለትሑታን መንገድን ያስተምራቸዋል። የጌታ መንገድ ሁሉ ቸርነትና እውነት ነው ቃል ኪዳኑንና ምስክሩን ለሚጠብቁ። አቤቱ፥ በደሌ ብዙ ነውና ስለ ስምህ ይቅር በለኝ።