መዝሙር 17:6-12
መዝሙር 17:6-12 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
በጨነቀኝ ጊዜ እግዚአብሔርን ጠራሁት፥ ወደ አምላኬም ጮኽሁ፤ በቤተ መቅደሱም ቃሌን ሰማኝ፥ ጩኸቴም በፊቱ ወደ ጆሮው ገባ። ምድርም ተንቀጠቀጠች፥ ተናወጠችም፥ የተራሮችም መሠረቶች ተነቃነቁ፥ እግዚአብሔር ተቈጥቶአልና ተንቀጠቀጡ። ከቍጣው ጢስ ወጣ፥ ከፊቱም እሳት ነደደ፤ ፍምም ከእርሱ በራ። ሰማዮችን ዝቅ ዝቅ አደረገ፥ ወረደም፥ ጭጋግ ከእግሩ በታች ነበረ። በኪሩቤልም ላይ ተቀምጦ በረረ፥ በነፋስም ክንፍ በረረ። መሰወሪያውን ጨለማ አደረገ፤ በዙሪያውም ድንኳኑ፤ ውኃዎች በደመናዎች ውስጥ ጠቈሩ። በፊቱ ካለው ብርሃን የተነሣ ደመናትና በረዶ የእሳት ፍምም በፊቱ አለፉ።
መዝሙር 17:6-12 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አምላክ ሆይ፤ ስለምትመልስልኝ አንተን እጣራለሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ ጣል አድርገህ ጸሎቴን ስማ። ከጠላቶቻቸው መተገኛ ያደረጉህን፣ በቀኝ እጅህ የምትታደግ ሆይ፤ ጽኑ ፍቅርህን ድንቅ አድርገህ ግለጥ። እንደ ዐይንህ ብሌን ጠብቀኝ፤ በክንፎችህም ጥላ ሰውረኝ፤ ከሚያስጨንቁኝ ከክፉዎች፣ ከሚከብቡኝ አደገኛ ባላንጣዎቼ ጋርደኝ። ደንዳና ልባቸውን ደፈኑት፤ በአፋቸውም ትዕቢት ይናገራሉ። አሳድደው ደረሱብኝ፤ ከበቡኝም፤ መሬት ላይ ሊዘርሩኝም አፈጠጡብኝ። እነርሱ ለንጥቂያ እንደሚጓጓ አንበሳ፣ በስውርም እንደሚያደባ ደቦል አንበሳ ናቸው።
መዝሙር 17:6-12 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አምላክ ሆይ! ልመናዬን ስለምትሰማ፥ ወደ አንተ እጸልያለሁ፤ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፤ ቃሌንም ስማ። የአንተን ከለላ ለሚፈልጉ፥ በቀኝ እጅህ የምታድናቸው አምላክ ሆይ! ዘለዓለማዊ ፍቅርህን በአስደናቂ ሁኔታ ግለጥ። የዐይን ብሌን በጥንቃቄ የሚጠበቀውን ያኽል ጠብቀኝ፤ በጥበቃህ ውስጥ ሰውረኝ። ከበባ አድርገው ከሚያጠፉኝ ጨካኝ ጠላቶቼ ጠብቀኝ። እነርሱ ለርኅራኄ ልባቸውን ዘግተዋል፤ አፋቸውም ትዕቢትን ይናገራል። ጠላቶቼ አስጨነቁኝ፤ ከበባም አደረጉብኝ፤ ወደ መሬት ሊጥሉኝም ዐይናቸውን ጣሉብኝ። እነርሱ እንደ ተራቡ አንበሶች ወይም እንደ ሸመቁ ደቦል አንበሶች ናቸው።
መዝሙር 17:6-12 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
አቤቱ፥ ሰምተኸኛልና ወደ አንተ ጠራሁ፥ ጆሮህን ወደ እኔ አዘንብል፥ ቃሌንም ስማ። የሚያምኑህን ከሚቃወሙ በቀኝህ የምታድናቸው፥ ቸርነትህን ድንቅ አድርገህ ግለጠው። እንደ ዐይን ብሌን ጠብቀኝ፥ በክንፎችህ ጥላ ሰውረኝ ከሚያስጨንቁኝ ከኃጢአተኞች፥ ነፍሴንም ከሚከብቡአት ከጠላቶቼ። አንጀታቸውን በስብ ቋጠሩ፥ በአፋቸውም ትንቢትን ተናገሩ። አሁንም እርምጃችንን ከበቡ፥ ዓይናቸውን ወደ ምድር ዝቅ ዝቅ አደረጉ። እርሱ ንጥቂያን እንደሚናፍቅ አንበሳ ተሸጉጦም እንደሚኖር እንደ አንበሳ ደቦል ነው።