መዝሙር 103:6-22
መዝሙር 103:6-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጥልቁም እንደ ልብስ ክዳኗ ነው፥ በተራሮችም ላይ ውኆች ይቆማሉ። ከተግሣጽህም የተነሣ ይሸሻሉ፥ ከነጐድጓድህም ድምፅ የተነሣ ይደነግጣሉ፤ ወደ ተራሮች ይወጣሉ፥ ወደ ሜዳ፥ ወዳዘጋጀህላቸው ስፍራም ይወርዳሉ፥ እንዳያልፉትም ድንበር አደረግህላቸው፥ ምድርን ይከድኑ ዘንድ እንዳይመለሱ። ምንጮችን ወደ ቆላዎች የሚልክ፤ በተራሮች መካከል ውኆች ያልፋሉ፤ የዱር አራዊትን ሁሉ ያጠጣሉ፥ የበረሃ አህዮችም ጥማታቸውን ያረካሉ። የሰማይ ወፎችም በዚያ ይኖራሉ፤ በዋሻው መካከልም ይጮኻሉ። ተራሮችን ከውስጣቸው የሚያጠጣቸው፤ ከሥራህ ፍሬ ምድር ትጠግባለች። እህልን ከምድር ያወጣ ዘንድ፥ ለምለሙን ለሰው ልጆች አገልግሎት፥ ሣርንም ለእንስሳ ያበቅላል። ወይን የሰውን ልብ ደስ ያሰኛል፥ ዘይትም ፊትን ለማብራት ነው። እህልም የሰውን ኀይል ያጠነክራል። የዱር ዛፎች ሁሉ፥ የተከልኸው የሊባኖስ ዝግባም ይጠግባሉ። በዚያም ዎፎች ይዋለዳሉ፥ የሸመላ ቤትም ይጐራበታቸዋል። ረጃጅም ተራራዎች ለዋሊያዎች፥ ድንጋዮችም ለአሽኮኮዎች መሸሻ ናቸው። ጨረቃን በጊዜው ፈጠርህ፤ ፀሐይም መግቢያውን ያውቃል። ጨለማን ታመጣለህ ሌሊትም ይሆናል፤ በእርሱም የዱር አራዊት ሁሉ ይወጡበታል። የአንበሶች ግልገሎች ያገሣሉ፥ ይነጥቃሉም፥ ከእግዚአብሔርም ምግባቸውን ይሻሉ። ፀሐይ ስትወጣ ይገባሉ፥ በየዋሻቸውም ይውላሉ።
መዝሙር 103:6-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር ለተጨቈኑ ሁሉ፣ ቅን ፍርድንና ፍትሕን ይሰጣቸዋል። መንገዱን ለሙሴ፣ ሥራውንም ለእስራኤል ሕዝብ አሳወቀ። እግዚአብሔር ርኅሩኅና መሓሪ፣ ለቍጣ የዘገየ፣ ታማኝነቱም የበዛ ነው። እርሱ ሁልጊዜ በደልን አይከታተልም፤ ለዘላለምም አይቈጣም። እንደ ኀጢአታችን አልመለሰልንም፤ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፣ እንዲሁ ለሚፈሩት ምሕረቱ ታላቅ ናት። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፣ መተላለፋችንን በዚያው መጠን ከእኛ አስወገደ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ፣ እግዚአብሔር ለሚፈሩት እንዲሁ ይራራል። እርሱ አፈጣጠራችንን ያውቃልና፤ ትቢያ መሆናችንንም ያስባል። ሰው እኮ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ ያቈጠቍጣል፤ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ግን ድራሹ ይጠፋል፤ ምልክቱም በቦታው አይገኝም። የእግዚአብሔር ምሕረት ግን፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም በሚፈሩት ላይ ነው፤ ጽድቁም እስከ ልጅ ልጅ ድረስ በላያቸው ይሆናል፤ ኪዳኑን በሚጠብቁት ላይ፣ ትእዛዙንም ለመፈጸም በሚተጕት ላይ ይሆናል። እግዚአብሔር ዙፋኑን በሰማይ አጽንቷል፤ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። እናንተ ለቃሉ የምትታዘዙ መላእክቱ፣ ትእዛዙንም የምትፈጽሙ እናንተ ኀያላን፤ እግዚአብሔርን ባርኩ። እናንተ ፈቃዱን የምትፈጽሙ አገልጋዮቹ፣ ሰራዊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። እናንተ በግዛቱ ሁሉ የምትኖሩ፣ ፍጥረቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ።
መዝሙር 103:6-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር በሚሠራው ሁሉ ጻድቅ ነው፤ ለተጨቈኑት ፍትሕን ይሰጣል። ዕቅዱን ለሙሴ ገለጠለት፤ የእስራኤል ሕዝቦች አስደናቂ ሥራዎቹን እንዲያዩ አደረገ። እግዚአብሔር መሐሪና ይቅር ባይ ነው። በቶሎ የማይቈጣና ለዘለዓለም ታማኝ ነው። ዘወትር የሚገሥጽ አይደለም፤ ቊጣውም ለዘለዓለም አይቈይም። በኃጢአታችን መጠን አልቀጣንም፤ በበደላችንም ልክ አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ የሚለውን ያኽል እግዚአብሔር ለሚፈሩት የሚሰጠው ፍቅር ታላቅ ነው። ምሥራቅ ከምዕራብ የሚርቀውን ያኽል እግዚአብሔር ኃጢአታችንን ከእኛ ያርቀዋል። አባት ለልጆቹ የሚራራላቸውን ያኽል እግዚአብሔርም የሚፈሩትን ይራራላቸዋል። እግዚአብሔር ከምን እንደ ተፈጠርን ያውቃል፤ ዐፈር መሆናችንንም ያስታውሳል። የሰው ሕይወት እንደ ሣር ነው፤ እንደሚያድግና እንደሚያብብ እንደ ዱር አበባ ነው። የዱር አበባ ነፋስ በሚነፍስበት ጊዜ ወዲያው ይጠፋል፤ በዚያ ስፍራ እንደ ነበረ እንኳ አይታወቅም። ነገር ግን እግዚአብሔር ለሚያከብሩት ሁሉ ፍቅሩን ለዘለዓለም ያሳያቸዋል፤ ቸርነቱም ከትውልድ ወደ ትውልድ ይተላለፋል። ይህንንም የሚያደርገው ቃል ኪዳኑን ቢጠብቁ፥ ትእዛዙንም በታማኝነት ቢፈጽሙ ነው። የእግዚአብሔር ዙፋን በሰማይ ነው፤ የእርሱም ገዢነት በሁሉም ላይ ነው። ትእዛዞቹን የምትፈጽሙ የሚናገረውን የምታዳምጡ፤ እናንተ ኀያላንና ብርቱዎች መላእክቱ እግዚአብሔርን አመስግኑ። አገልጋዮቹ የሆናችሁ፥ ፈቃዱንም የምትፈጽሙ፥ እናንተ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን አመስግኑ! በግዛቱ ሁሉ የምትገኙ ፍጥረቶቹ እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ነፍሴ ሆይ! እግዚአብሔርን አመስግኚ!
መዝሙር 103:6-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታ ጽድቅን ይፈጽማል፥ ለተበደሉ ሁሉ ይፈርዳል። ለሙሴ መንገዱን አስታወቀ፥ ለእስራኤል ልጆችም ድንቅ ሥራዎቹን። ጌታ ርኅሩኅና ቸር ነው፥ ከቁጣ የራቀ ፍቅሩም የበዛ። ሁልጊዜም አይከስም፥ ለዘለዓለምም አይቈጣም። እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፥ እንደ በደላችንም አልከፈለንም። ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ ምሕረቱን በሚፈሩት ላይ አጠነከረ። ምሥራቅ ከምዕራብ እንደሚርቅ፥ እንዲሁ ኃጢአታችንን ከእኛ አራቀ። አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ ጌታም ለሚፈሩት ይራራል፥ ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን ያስታውሳል። ሰውስ ዘመኑ እንደ ሣር ነው፥ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፥ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፥ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና። የጌታ ጽኑ ፍቅር ግን ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በሚፈሩት ላይ፥ ጽድቁም በልጅ ልጆች ላይ ነው፥ ቃል ኪዳኑን በሚጠብቁ፥ ትእዛዙንም ያደርጉአት ዘንድ በሚያስቡ ላይ ነው። ጌታ ዙፋኑን በሰማይ አዘጋጀ፥ መንግሥቱም ሁሉን ትገዛለች። ቃሉን የምትፈጽሙ መላእክቱ፥ ብርቱዎችና ኃያላን፥ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ። ሠራዊቱ ሁሉ፥ ፈቃዱን የምታደርጉ አገልጋዮቹ፥ ጌታን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፥ ጌታን ባርኩ። ነፍሴ ሆይ፥ ጌታን ባርኪ።