ምሳሌ 4:1-9
ምሳሌ 4:1-9 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጆቼ ሆይ፤ የአባትን ምክር አድምጡ፤ ልብ ብላችሁ ስሙ፤ ማስተዋልንም ገንዘብ አድርጉ። በጎ ትምህርት እሰጣችኋለሁ፤ ስለዚህ ትምህርቴን አትተዉ። በአባቴ ቤት ገና ለግላጋ ወጣት፣ ለእናቴም አንድ ልጇ ብቻ በነበርሁ ጊዜ፣ አባቴ እንዲህ ሲል አስተማረኝ፤ “ቃሌን በሙሉ በልብህ ያዝ፤ ትእዛዜንም ጠብቅ፤ በሕይወት ትኖራለህ። ጥበብን አግኛት፤ ማስተዋልን ያዛት፤ ቃሌን አትርሳ፤ ከርሷም ዘወር አትበል። ጥበብን አትተዋት፤ እርሷም ከለላ ትሆንሃለች፤ አፍቅራት፤ እርሷም ትጠብቅሃለች። ጥበብ ታላቅ ነገር ናት፤ ስለዚህ ጥበብን አግኛት፤ ያለህን ሁሉ ብታስከፍልህም ማስተዋልን ገንዘብህ አድርጋት። ክብርን ስጣት፤ ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ዕቀፋት፤ ታከብርሃለች፤ በራስህ ላይ ሞገሳማ አክሊል ትደፋልሃለች፤” የክብር ዘውድም ታበረክትልሃለች።
ምሳሌ 4:1-9 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጆች ሆይ፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፤ መልካም ስጦታን እሰጣችኋለሁና፥ ሕጌን አትተዉ። እኔም አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ፊት እወደድ ነበር። ያስተምሩኝም ነበር፥ እንዲህም ይሉኝ ነበር፦ ቃላችን በልብህ ይኑር፤ ትእዛዞቻችንንም ጠብቅ፥ አትርሳቸውም። የአፌንም ቃል ቸል አትበል። አትተዋት፥ ትደግፍህማለች፤ ውደዳት፥ ትጠብቅህማለች። ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ጠብቃት፥ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ አክብራት፥ እርስዋም ታቅፍሃለች። ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፥ በደስታ አክሊልም ትጠብቅሃለች።
ምሳሌ 4:1-9 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጆቼ ሆይ! የአባታችሁን ምክር ስሙ፤ በጥንቃቄ አዳምጡ፤ ማስተዋልንም ታገኛላችሁ። እኔ የማስተምራችሁ ትምህርት መልካም ስለ ሆነ ቸል አትበሉት። እኔም አንድ ጊዜ ከአባቴ ጋር የምኖር ትንሽ ልጅ ነበርኩ፤ ለእናቴም አንድ ነበርኩ፤ አባቴም እንዲህ እያለ ያስተምረኝ ነበር፤ “ቃሌን በሙሉ ልብህ ያዘው፤ ትእዛዞቼንም ፈጽም፤ በሕይወትም ትኖራለህ። ጥበብንና ማስተዋልን ለማግኘት ትጋ፤ እኔ የምልህን አትርሳ፤ ቸልም አትበለው። ጥበብን አትተዋት፤ እርስዋም ትጠብቅሃለች፤ ውደዳት፤ እርስዋም ከአደጋ ሁሉ ትከላከልልሃለች። ጥበብ ከሁሉ በላይ ስለ ሆነች እርስዋን ገንዘብ አድርግ፤ ያለህን ሁሉ ቢያስከፍልህም ማስተዋልን ለማግኘት ትጋ። ጥበብን አክብራት፤ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ አጥብቀህም ብትይዛት፥ ክብርን ትሰጥሃለች። የክብርን አክሊል ታቀዳጅሃለች፤ የተዋበውንም ዘውድ ትሰጥሃለች።”
ምሳሌ 4:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጆች ሆይ፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፥ መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፥ ሕጌን አትተዉ። እኔም አባቴን የምሰማ ትንሽ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር። ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር፦ “ልብህ ቃሌን በጥብቅ ይያዘው፥ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ። ጥበብን አግኝ፥ ማስተዋልን አግኝ፥ አትርሳም፥ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል። አትተዋት፥ ትጠብቅሃለች፥ ውደዳት፥ ትንከባከብህማለች። የጥበብ መጀመሪያ እነሆ፥ ጥበብን አግኝ፥ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ። ከፍ ከፍ አድርጋት፥ እርሷም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፥ ብታቅፋትም ታከብርሃለች። በራስህ የጸጋ አክሊልን ታኖራለች፥ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትልሃለች።”