ምሳሌ 3:13-19
ምሳሌ 3:13-19 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ጥበብን የሚያገኝ፥ ማስተዋልንም የሚያውቅ መዋቲ ሰው ብፁዕ ነው። በወርቅና በብር፥ በብዙም መዛግብት ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ዋጋው ብዙ ከሆነ ዕንቍም የከበረች ናት። ክፉ ነገር አይቃወማትም፥ ለሚቀርቧትም መልካም ናት። ክብርም ሁሉ አይተካከላትም። ረጅም ዕድሜና የሕይወት ዘመን በቀኝዋ ነው። ባለጠግነትና ክብርም በግራዋ፥ ከአፏ ጽድቅ ይወጣል። ሕግንና ምጽዋትንም በአንደበትWa ትለብሳለች። መንገዶችዋ መልካም መንገዶች ናቸው። ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚመረኰዛት ሁሉ የሕይወት ዛፍ ናት፥ የሚታመኑባትም በእግዚአብሔር እንደ ጸና ሰው ናቸው። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አዘጋጀ።
ምሳሌ 3:13-19 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ብፁዕ ነው፤ ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንቍ ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤
ምሳሌ 3:13-19 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ጥበብን የሚያገኝ፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው የተባረከ ነው። ስለዚህ ጥበብ ከብር ይበልጥ ትርፍ ትሰጣለች፤ ከወርቅም የተሻለ ጥቅም ታስገኛለች። ጥበብ ከውድ ዕንቊ ትከብራለች፤ አንተ ለማግኘት ከምትመኛቸው ነገሮች ሁሉ እርስዋን የሚወዳደራት ከቶ የለም። ጥበብ በቀኝ እጅዋ ረጅም ዕድሜን በግራ እጅዋ ደግሞ ብልጽግናንና ክብርን ይዛለች። መንገዶችዋ የደስታ መንገዶች ናቸው፤ መተላለፊያዎችዋም ሁሉ ሰላም የሰፈነባቸው ናቸው። ጥበብ፥ ለሚይዟት ሰዎች ሕይወትን ትሰጣለች፤ እርስዋንም ገንዘብ የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።
ምሳሌ 3:13-19 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጥበብን የሚያገኝ ሰው ብጹዕ ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው፥ በእርሷ የሚገኘው ትርፍ ከብር ከሚገኘው፥ ገቢዋም ከወርቅ ይሻላልና። ከውድ ዕንቁም ትከብራለች፥ ከምትመኘው ነገር አንዳችም አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርሷ ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው። ጌታ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና።