ምሳሌ 3:1-6
ምሳሌ 3:1-6 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ! ሕጎቼን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትንና ረጅም ዕድሜን ሰላምንም ይጨምሩልሃልና። ምጽዋትና ሃይማኖት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላትም ጻፋቸው፤ ባላሟልነትን ታገኛለህና፥ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መልካምን ዐስብ። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታምነህ ኑር፥ በራስህም ጥበብ አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ ጥበብን ዕወቃት፥ እርስዋም መንገድህን ታቃናልሃለች።
ምሳሌ 3:1-6 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል። ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው። በዚያን ጊዜ ሞገስንና መልካም ስምን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።
ምሳሌ 3:1-6 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! የማስተምርህን አትርሳ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ጠብቅ። የእኔ ትምህርት ረጅም ዕድሜን ከብዙ ተድላና ደስታ ጋር ይሰጥሃል። ታማኝነትና እውነተኛነትን አትተው፤ እንደ አንገት ሐብል ተጠንቅቀህ ያዛቸው፤ በልብህም ሰሌዳ ጻፋቸው። ይህን ብታደርግ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መወደድንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። በሙሉ ልብህ በእግዚአብሔር ታመን እንጂ በራስህ ዕውቀት አትመካ። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔርን መሪ አድርገው፤ እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል።