ምሳሌ 3:1-35
ምሳሌ 3:1-35 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ! ሕጎቼን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትንና ረጅም ዕድሜን ሰላምንም ይጨምሩልሃልና። ምጽዋትና ሃይማኖት ከአንተ አይራቁ፤ በአንገትህ እሰራቸው፤ በልብህ ጽላትም ጻፋቸው፤ ባላሟልነትን ታገኛለህና፥ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መልካምን ዐስብ። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታምነህ ኑር፥ በራስህም ጥበብ አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ ጥበብን ዕወቃት፥ እርስዋም መንገድህን ታቃናልሃለች። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፤ እግዚአብሔርን ፍራው፥ ከክፋትም ሁሉ ራቅ፤ ይህም ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንልሃል። እግዚአብሔርን በእውነት በአገኘኸው ሀብትህ አክብረው። ከእውነተኛ ፍሬህም ሁሉ ቀዳምያቱን አግባለት። ጐተራህም እህልን ይሞላል። የወይን መጥመቂያህም ወይን ይሞላል። ልጄ ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ ቸል አትበል፥ በመገሠጹም ከእርሱ የተነሣ አትመረር። አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ እግዚአብሔር የሚወድደውን ይገሥጻል፥ የሚቀበላቸውን ልጆቹን ይገርፋልና። ጥበብን የሚያገኝ፥ ማስተዋልንም የሚያውቅ መዋቲ ሰው ብፁዕ ነው። በወርቅና በብር፥ በብዙም መዛግብት ከመነገድ ይልቅ በእርስዋ መነገድ ይሻላልና። ዋጋው ብዙ ከሆነ ዕንቍም የከበረች ናት። ክፉ ነገር አይቃወማትም፥ ለሚቀርቧትም መልካም ናት። ክብርም ሁሉ አይተካከላትም። ረጅም ዕድሜና የሕይወት ዘመን በቀኝዋ ነው። ባለጠግነትና ክብርም በግራዋ፥ ከአፏ ጽድቅ ይወጣል። ሕግንና ምጽዋትንም በአንደበትWa ትለብሳለች። መንገዶችዋ መልካም መንገዶች ናቸው። ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርስዋ ለሚመረኰዛት ሁሉ የሕይወት ዛፍ ናት፥ የሚታመኑባትም በእግዚአብሔር እንደ ጸና ሰው ናቸው። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አዘጋጀ። በዕውቀቱ ቀላያት መነጩ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። ልጄ ሆይ፥ ቸል አትበል ዐሳቤንና ምክሬን ጠብቅ፤ ነፍስህ ትድን ዘንድ፥ ለአንገትህም ሞገስ ይሆንህ ዘንድ። ለሥጋህ ፈውስ፥ ለአጥንትህም ጠገን ይሆንልሃል። በመንገድህም ሁሉ በመተማመን ትሄዳለህ፥ እግሮችህም አይሰነካከሉም። በተቀመጥህም ጊዜ አትፈራም፤ ብትተኛም መልካም እንቅልፍ ትተኛለህ። ከሚመጣብህም አስደንጋጭ ነገር፥ ከሚመጣውም የክፉዎች ሰዎች አደጋ አትፈራም፤ እግዚአብሔር በመንገድህ ሁሉ ይኖራልና፥ እግሮችህም እንዳይነዋወጡ ያቆማቸዋልና። ለተቸገረው ሰው በጎ ነገር ማድረግን ቸል አትበል፥ በእጅህ ያለውን ያህል ርዳው። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው፥ ነገ የምትወልደውን አታውቅምና። እርሱ ተማምኖብህ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ እንደገና በወዳጅህ ላይ ክፉ አታስብ፤ እርሱ በላይህ የሠራው ክፉ ነገር ከሌለ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። ከክፉ ሰዎች ዘንድ ሽሙጥን ገንዘብ አታድርግ፥ በመንገዳቸውም አትቅና። ኀጢአተኛ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ርኩስ ነውና፤ ከጻድቃንም ጋር አንድ አይሆንም። የእግዚአብሔር መርገም በክፉዎች ቤት ነው፥ በጻድቃን ቤት ግን በረከት አለ። እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማቸዋል፤ ለትሑታን ግን ክብርን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሰነፎች ግን ውርደታቸውን ከፍ ከፍ ያደርጋሉ።
ምሳሌ 3:1-35 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዞቼን በልብህ ጠብቅ፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል። ፍቅርና ታማኝነት ከቶ አይለዩህ፤ በዐንገትህ ዙሪያ እሰራቸው፤ በልብህም ጽላት ላይ ጻፋቸው። በዚያን ጊዜ ሞገስንና መልካም ስምን፣ በእግዚአብሔርና በሰው ዘንድ ታገኛለህ። በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ ነኝ አትበል፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፉም ራቅ። ይህም ለሰውነትህ ጤንነትን፣ ለዐጥንትህም ልምላሜን ያመጣልሃል። እግዚአብሔርን በሀብትህ፣ ከምርትህ ሁሉ በኵራት አክብረው፤ ይህን ብታደርግ፣ ጎተራህ ሞልቶ ይትረፈረፋል፤ መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ቲፍ ብሎ ይሞላል። ልጄ ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በዘለፋውም አትመረር፤ አባት ደስ የሚሰኝበትን ልጁን እንደሚቀጣ ሁሉ፣ እግዚአብሔርም የሚወድደውን ይገሥጻልና። ጥበብን የሚያገኛት፣ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርጋት ሰው ቡሩክ ነው፤ እርሷ ከብር ይልቅ ትርፍ የምታመጣ፣ ከወርቅም ይልቅ ጥቅም የምታስገኝ ናትና። ከቀይ ዕንይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ ከምትመኘውም ሁሉ የሚስተካከላት የለም። በቀኝ እጇ ረዥም ዕድሜ አለ፤ በግራ እጇም ሀብትና ክብር ይዛለች። መንገዷ ደስ የሚያሰኝ ነው፤ ጐዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። ለሚያቅፏት የሕይወት ዛፍ ናት፤ የሚይዟትም ይባረካሉ። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋል ሰማያትን በየስፍራቸው አጸና፤ በዕውቀቱ ቀላያት ተከፈሉ፤ ደመናትም ጠልን አንጠበጠቡ። ልጄ ሆይ፤ ትክክለኛ ፍርድንና አስተውሎ መለየትን ጠብቅ፤ እነዚህ ከእይታህ አይራቁ፤ ለነፍስህ ሕይወት፣ ለዐንገትህም ጌጥ ይሆናሉ። ከዚያም መንገድህን በሰላም ትሄዳለህ፤ እግርህም አይሰናከልም፤ ስትተኛ አትፈራም፤ ትተኛለህ እንቅልፍህም ጣፋጭ ይሆናል። ድንገተኛን መከራ፣ በክፉዎች ላይ የሚደርሰውንም ጥፋት አትፍራ፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፤ እግርህንም በወጥመድ ከመያዝ ይጠብቃል። ማድረግ እየቻልህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። አሁን በእጅህ እያለ፣ ጎረቤትህን፣ “ቈይተህ ተመለስ፤ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣ በጎረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት። ምንም ጕዳት ሳያደርስብህ፣ ያለ ምክንያት ሰውን አትክሰስ። በክፉ ሰው አትቅና፤ የትኛውንም መንገዱን አትምረጥ፤ እግዚአብሔር ጠማማን ሁሉ ይጸየፋልና፤ ለቅን ሰው ግን ምስጢሩን ይገልጥለታል። የእግዚአብሔር ርግማን በክፉዎች ቤት ላይ ነው፤ የጻድቃንን ቤት ግን ይባርካል። እርሱ በዕቡያን ፌዘኞች ላይ ያፌዛል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፤ ሞኞችን ግን ለውርደት ያጋልጣቸዋል።
ምሳሌ 3:1-35 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! የማስተምርህን አትርሳ፤ ትእዛዞቼንም በልብህ ጠብቅ። የእኔ ትምህርት ረጅም ዕድሜን ከብዙ ተድላና ደስታ ጋር ይሰጥሃል። ታማኝነትና እውነተኛነትን አትተው፤ እንደ አንገት ሐብል ተጠንቅቀህ ያዛቸው፤ በልብህም ሰሌዳ ጻፋቸው። ይህን ብታደርግ በእግዚአብሔርና በሰው ፊት መወደድንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። በሙሉ ልብህ በእግዚአብሔር ታመን እንጂ በራስህ ዕውቀት አትመካ። በምታደርገው ሁሉ እግዚአብሔርን መሪ አድርገው፤ እርሱም በትክክለኛው መንገድ ይመራሃል። “እኔ ዐዋቂ ነኝ” አትበል። ይልቅስ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ከክፋትም ራቅ። ይህን ብታደርግ ለሰውነትህ ጤንነትን፥ ለአጥንቶችህም ጥንካሬን ታገኛለህ። ከሀብትህና ምድርህ ከሚያፈራው መልካም ነገር ሁሉ የመጀመሪያውን መባ አድርገህ በመስጠት እግዚአብሔርን አክብር። ይህን ብታደርግ ጐተራዎችህ በእህል የተሞሉ ይሆናሉ፤ የወይን መጥመቂያህም በአዲስ የወይን ጠጅ ሞልቶ ይትረፈረፋል። ልጄ ሆይ! የእግዚአብሔርን ተግሣጽ አትናቅ፤ በሚገሥጽህም ጊዜ አትመረር። አባት የሚወደውን ልጁን እንደሚገሥጽ እግዚአብሔርም የሚወዳቸውን ሰዎች ይገሥጻል። ጥበብን የሚያገኝ፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው የተባረከ ነው። ስለዚህ ጥበብ ከብር ይበልጥ ትርፍ ትሰጣለች፤ ከወርቅም የተሻለ ጥቅም ታስገኛለች። ጥበብ ከውድ ዕንቊ ትከብራለች፤ አንተ ለማግኘት ከምትመኛቸው ነገሮች ሁሉ እርስዋን የሚወዳደራት ከቶ የለም። ጥበብ በቀኝ እጅዋ ረጅም ዕድሜን በግራ እጅዋ ደግሞ ብልጽግናንና ክብርን ይዛለች። መንገዶችዋ የደስታ መንገዶች ናቸው፤ መተላለፊያዎችዋም ሁሉ ሰላም የሰፈነባቸው ናቸው። ጥበብ፥ ለሚይዟት ሰዎች ሕይወትን ትሰጣለች፤ እርስዋንም ገንዘብ የሚያደርጉ የተባረኩ ናቸው። እግዚአብሔር በጥበብ ምድርን መሠረተ፤ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእርሱ ጥበብ ወንዞች ይፈስሳሉ፤ ደመናዎችም ለምድር ዝናብን ይሰጣሉ። ልጄ ሆይ! መልካም ጥበብንና አርቆ ማስተዋልን አጥብቀህ ያዝ፤ ከአንተም እንዲርቁ አታድርግ። እነርሱም ለአንተ ረጅምና የአማረ ሕይወትን ይሰጡሃል። በመንገድህ ያለ ፍርሀት ተማምነህ መሄድ ትችላለህ፤ ከቶም አትሰናከልም። በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ሌሊቱንም ሙሉ የሰላም እንቅልፍ ታገኛለህ። በክፉ ሰዎች ላይ በድንገት የሚደርስ አደጋና ጥፋት ይደርስብኛል ብለህ አትፍራ። እግዚአብሔር መታመኛህ ሆኖ በወጥመድም ከመያዝ ይጠብቅሃል። ርዳታ እንድታደርግለት ለሚገባው ሰው ዐቅምህ በሚፈቅድልህ መጠን በጎ ነገር ከማድረግ አትቈጠብ። የተቸገረ ጐረቤትህን ዛሬውኑ መርዳት ሲቻልህ “እሺ ነገ” እያልክ አታመላልሰው። አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በሚኖረው ጐረቤትህ ላይ በተንኰል ክፉ ነገር ለማድረግ አታስብ። ምንም በደል ያላደረሰብህን ሰው ያለ ምክንያት አትክሰሰው። በግፈኞች ሰዎች አትቅና፤ ክፉ ሥራቸውንም አትከተል። እግዚአብሔር ክፉ አድራጊዎችን ይጠላል፤ ልበ ቅኖችን ግን አጥብቆ ይወዳቸዋል። እግዚአብሔር በክፉ ሰዎች ቤት እርግማንን ያመጣል፤ የደጋግ ሰዎችን ቤት ግን ይባርካል። እግዚአብሔር ፌዘኞችን ይንቃል፤ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን መልካም ክብርን ያገኛሉ፤ ሞኞች ግን ውርደትን ይከናነባሉ።
ምሳሌ 3:1-35 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ ሕጌን አትርሳ፥ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ቀኖች፥ የሕይወት ዓመታትና ሰላምም ይጨምሩልሃልና። ደግነትና እውነት አይተዉህ፥ በአንገትህ ላይ እሰራቸው፥ በልብህ ጽላት ጻፋቸው። በእግዚአብሔርና በሰው ፊትም ሞገስንና መልካም ዝናን ታገኛለህ። በፍጹም ልብህ በጌታ ታመን፥ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፥ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፥ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል። በራስህ አስተያየት ጠቢብ አትሁን፥ ጌታን ፍራ፥ ከክፋትም ራቅ፥ ይህም ለሥጋህ ፈውስ ይሆንልሃል፥ ለአጥንትህም መታደስ። ከሀብትህ አስበልጠህ ጌታን አክብር፥ ከፍሬህም ሁሉ በኵራት ይልቅ፥ ጐተራህም እህልን ይሞላል፥ መጥመቂያህም በወይን ጠጅ ሞልታ ትትረፈረፋለች። ልጄ ሆይ፥ የጌታን ተግሣጽ አትናቅ፥ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር። ጌታ የወደደውን ይገሥጻልና፥ አባት የሚወድደውን ልጁን እንደሚገሥጽ። ጥበብን የሚያገኝ ሰው ብጹዕ ነው፥ ማስተዋልንም ገንዘቡ የሚያደርግ ሰው፥ በእርሷ የሚገኘው ትርፍ ከብር ከሚገኘው፥ ገቢዋም ከወርቅ ይሻላልና። ከውድ ዕንቁም ትከብራለች፥ ከምትመኘው ነገር አንዳችም አይተካከላትም። በቀኝዋ ረጅም ዘመን ነው፥ በግራዋም ባለጠግነትና ክብር። መንገድዋ የደስታ መንገድ ነው፥ ጎዳናዋም ሁሉ ሰላም ነው። እርሷ ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፥ የተመረኰዘባትም ሁሉ ምስጉን ነው። ጌታ በጥበብ ምድርን መሠረተ፥ በማስተዋልም ሰማያትን አጸና። በእውቀቱ ቀላያት ተቀደዱ፥ ደመናትም ጠልን ያንጠባጥባሉ። ልጄ ሆይ፥ እነዚህ ከዐይኖችህ አይራቁ፥ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፥ ለአንገትህም ሞገስ። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፥ እግርህም አይሰነካከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፥ ስትተኛም፥ እንቅልፍህ የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር፥ ከሚመጣውም ከኀጥኣን ጥፋት አትፈራም፥ ጌታ መታመኛህ ይሆናልና፥ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና። ልታደርግለት የሚቻልህ ሲሆን፥ ለተቸገረው ሰው በጎ ነገርን ከማድረግ አትቆጠብ። በጎ ነገርን ማድረግ ሲቻልህ፥ ወዳጅህን፦ “ሂድና ተመለስ፥ ነገ እሰጥሃለሁ” አትበለው። እርሱ ተማምኖ ከአንተ ጋር ተቀምጦ ሳለ፥ በወዳጅህ ላይ ክፉ አትሥራ። እርሱ ክፉ ካልሠራብህ፥ ከሰው ጋር በከንቱ አትጣላ። በግፈኛ ሰው አትቅና፥ መንገዱንም ሁሉ አትምረጥ። ጠማማ ሁሉ በጌታ ፊት ርኩስ ነውና፥ ወዳጅነቱ ግን ከቅኖች ጋር ነው። የጌታ መርገም በክፉ ሰዎች ቤት ነው፥ የጻድቃን ቤት ግን ይባረካል። በፌዘኞች እርሱ ያፌዛል፥ ለትሑታን ግን ሞገስን ይሰጣል። ጠቢባን ክብርን ይወርሳሉ፥ ሞኞች ግን መዋረድን ይቀበላሉ።