ምሳሌ 2:1-22
ምሳሌ 2:1-22 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን ትሰማለች፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ልብህንም ልጅህን ለመምከር ታቀርባለህ፥ ጥበብን ብትጠራት፥ ቃልህንም ለማስተዋል ብትሰጥ፥ ዕውቀትንም በታላቅ ቃል ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እርስዋንም እንደ ተቀበረ ገንዘብ ብትሻት፤ የዚያን ጊዜ እግዚአብሔርን መፍራት ታውቃለህ፥ አምላክን ማወቅንም ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከፊቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፤ እርሱ ቅንነትን ለሚያደርጉ ደኅንነትን ያከማቻል፤ በመንገዳቸውም ይቆምላቸዋል። የጽድቅን ጎዳና ይጠብቃል፤ የሚፈሩትንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ታውቃለህ፤ መልካም መንገድንም ሁሉ ታቃናለህ። ጥበብ ወደ ልብህ በመጣች ጊዜ፥ ዕውቀትም ለነፍስህ መልካምና ክብር በሆነች ጊዜ፥ መልካም ምክር ትጠብቅሃለች፤ የተቀደሰች ማስተዋልም ትጋርድሃለች። አንተን ከክፉ መንገድ፥ ምንም የሚታመን ነገርን ከማይናገር ሰውም ታድንህ ዘንድ፥ እነርሱ በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን ጎዳና ለሚተዉ፥ ክፉ በመሥራት ደስ ለሚላቸው ክፋትንም በመመለስ ሐሤትን ለሚያደርጉ፥ መንገዳቸው ጐጻጕጽ፥ አካሄዳቸው ጠማማ ለሆኑ ወዮላቸው! ከቀናች መንገድ እንዳያርቁህ፥ እውነትንም ከማወቅ የተለየህ እንዳያደርጉህ፤ ልጄ ሆይ፥ በሕፃንነትህ ትምህርትን የምታስተው፥ ክፉ ምክር አታግኝህ፤ ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ጠብቅ፥ ቃሏን ከምታለዝብ ከሌላዪቱ ክፉ ሴት፥ የሕፃንንነት ባልዋን ከምትተው፥ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከምትረሳ፤ ይጠብቅህ ዘንድ፤ ቤቷን በሞት አጠገብ አኖረች፥ አካሄድዋንም ከኀያላን ጋር ከምድር ወደ ሲኦል አቀናች። ወደ እርስዋ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ ቀና መንገዶችንም አያገኙም፥ ሕይወት በአለው ዘመንም አይገኙም። ቀና መንገዶችን ቢሄዱ ለስላሳ የጽድቅ መንገዶችን ባገኙ ነበር። ደጋግ ሰዎች በምድር ላይ ይቀመጣሉ፥ ጻድቃንም በእርስዋ ይኖራሉ፤ የክፉዎች መንገዶች ከምድር ላይ ይጠፋሉ፤ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይሰደዳሉ።
ምሳሌ 2:1-22 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ልጄ ሆይ፤ ቃሌን ብትቀበል፣ ትእዛዜንም በልብህ ብታኖር፣ ጆሮህን ወደ ጥበብ ብታቀና፣ ልብህንም ወደ ማስተዋል ብትመልስ፣ እንዲሁም የመለየት ጥበብን ብትማጠን፣ ድምፅህን ከፍ አድርገህ ማስተዋልን ብትጣራ፣ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፣ እንደ ተሸሸገ ሀብት አጥብቀህ ብትሻት፣ በዚያን ጊዜ ፈሪሀ እግዚአብሔርን ትረዳለህ፤ አምላክንም ማወቅ ታገኛለህ። እግዚአብሔር ጥበብን ይሰጣልና፤ ከአንደበቱም ዕውቀትና ማስተዋል ይወጣል። እርሱ ለቅኖች ድልን ያከማቻል፤ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ይሆናቸዋል፤ የፍትሕን መንገድ ይጠብቃል፤ የታማኞቹንም አካሄድ ያጸናል። በዚያን ጊዜ ጽድቅን፣ ፍትሕን፣ ሚዛናዊነትን፣ መልካሙንም መንገድ ሁሉ ትገነዘባለህ፤ ጥበብ ልብህ ውስጥ ትገባለችና፤ ዕውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለች፤ የመለየት ችሎታ ይጋርድሃል፤ ማስተዋልም ይጠብቅሃል። ጥበብ ንግግራቸው ጠማማ ከሆነ ሰዎች፣ ከክፉዎችም መንገድ ታድንሃለች፤ እነዚህም በጨለማ መንገድ ለመሄድ፣ ቀናውን ጐዳና የሚተዉ ናቸው፤ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው፣ በክፋት ጐዳና ሐሤት የሚያደርጉ፣ መንገዳቸው ጠማማ፣ በአካሄዳቸው ጠመዝማዞች ናቸው። ከአመንዝራ ሴትም ትጠብቅሃለች፤ በአንደበቷም ከምታታልል ዘልዛላ ታድንሃለች፤ ይህችም የልጅነት ባሏን የተወች፣ በአምላኳ ፊት የገባችውን ኪዳን ያቃለለች ናት። ቤቷ ወደ ሞት ያደርሳል፤ መንገዷም ወደ መናፍስተ ሙታን ያመራል። ወደ እርሷ የሚገባ ማንም አይመለስም፤ የሕይወትንም መንገድ አያገኝም። አንተም በደጋግ ሰዎች ጐዳና ትሄዳለህ፤ የጻድቃንንም መንገድ ይዘህ ትጓዛለህ። ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።
ምሳሌ 2:1-22 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልጄ ሆይ! የማስተምርህን ተቀበል፤ ትእዛዞቼንም በልብህ አኑር። የጥበብን ቃል አድምጥ፤ በጥንቃቄም አስተውለው። ማስተዋልን ጥራ፤ ለዕውቀትም ድምፅህን ከፍ አድርግ። ብር ወይም የተሰወረ ሀብት ለማግኘት ጥረት የምታደርገውን ያኽል ተግተህ ጥበብን ፈልጋት። ይህን ሁሉ ብታደርግ እግዚአብሔርን መፍራት ምን እንደ ሆነ ታውቃለህ፤ የአምላክንም ዕውቀት ታገኛለህ። ጥበብን የሚሰጥ እግዚአብሔር ነው፤ ዕውቀትና ማስተዋልም የሚገኙት ከእርሱ ዘንድ ነው። እርሱ ለቀጥተኞች መልካም ጥበብን ይሰጣል፤ በተግባራቸው ነቀፋ ለሌለባቸው ጋሻቸው ነው። የፍትሕን ሂደት ይከታተላል፤ በታማኝነት የሚያገለግሉትንም ይጠብቃል። እኔ የምልህን ሁሉ ብትሰማ፥ ቀጥተኛ፥ ትክክልና ቅን የሆነውን መንገድ ትገነዘባለህ፤ ልታደርገው የሚገባህንም መልካም ነገር ሁሉ ታውቃለህ። ጠቢብ ትሆናለህ፤ ዕውቀትም ደስታን ይሰጥሃል። አርቆ ማስተዋል ይጠብቅሃል፤ መገንዘብም ከክፉ ነገር ይከላከልልሃል። ጥበብ ከክፉ ሰዎች መንገድና ከጠማማ ንግግራቸው ያድንሃል። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች በኃጢአት ጨለማ ውስጥ ለመኖር የጽድቅን መንገድ የተዉ ናቸው። እነርሱን ደስ የሚያሰኛቸው ቀናውን ነገር ማጣመምና ተንኰል የተሞላበት ክፉ ሥራ መሥራት ነው። እነርሱ እምነት የማይጣልባቸውና ጠማሞች ናቸው። እንግዲህ እኔ የምልህን ብትሰማ በልዝብ አነጋገር ከምታጠምድ ከአመንዝራ ሴት ማምለጥ ትችላለህ። እንደዚህ ያለችው ሴት ለልጅነት ባልዋ ያላትን ታማኝነት የምታጓድልና በእግዚአብሔር ፊት የገባችውንም ቃል ኪዳን የምትዘነጋ ናት። ወደ እርስዋ ቤት ብታመራ ጒዞህ ወደ ሞት ይሆናል፤ ወደ እርስዋ መሄድ ወደ ሙታን ዓለም እንደ መውረድ ነው። ወደ እርስዋ የሚሄድ ሁሉ አይመለስም፤ የሕይወትንም ጐዳና ማግኘት አይችልም። ስለዚህ የመልካም ሰዎችን ምሳሌነት ልትከተልና የደጋግ ሰዎችንም አካሄድ ልትጠብቅ ይገባሃል። በዚህች ምድር መኖር የሚችሉት ልበ ቅኖችና ደጋግ ሰዎች ናቸው። ክፉ ሰዎችን ግን እግዚአብሔር ከምድር ላይ በሞት ይነጥቃቸዋል፤ ከዳተኞችንም እንደ አረም ነቃቅሎ ያጠፋቸዋል።
ምሳሌ 2:1-22 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልጄ ሆይ፥ ቃሌን ብትቀበል፥ ትእዛዜንም በአንተ ዘንድ ሸሽገህ ብትይዛት፥ ጆሮህ ጥበብን እንዲያደምጥ ታደርጋለህ፥ ልብህንም ወደ ማስተዋል ታዘነብላለህ። ማመዛዘንን ብትጠራት፥ ለማስተዋልም ድምፅህን ብታነሣ፥ እርሷንም እንደ ብር ብትፈልጋት፥ እንደ ተደበቀ ዕንቁም ብትሻት፥ የዚያን ጊዜ ጌታን መፍራትን ትገነዘባለህ፥ የአምላክንም እውቀት ታገኛለህ። ጌታ ጥበብን ይሰጣልና፥ ከአፉም እውቀትና ማስተዋል ይወጣሉ፥ እርሱ ለቅኖች ስምረትን ያከማቻል፥ ያለ ነቀፋ ለሚሄዱትም ጋሻ ነው፥ የፍርድን ጎዳና ይጠብቃል፥ የቅዱሳኑንም መንገድ ያጸናል። የዚያን ጊዜ ጽድቅንና ፍርድን ቅንነትንና መልካም መንገድን ሁሉ ታስተውላለህ። ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፥ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፥ ማመዛዘን ይጠብቅሃል፥ ማስተዋልም ይከላከልልሃል፥ ከክፉ መንገድ አንተን ለማዳን፥ ጠማማ ነገርን ከሚናገሩም ሰዎች፥ እነርሱም በጨለማ መንገድ ለመሄድ የቀናውን ጎዳና የሚተዉ፥ ክፉ በመሥራት ደስ የሚላቸው በጠማማነትም ሐሤትን የሚያደርጉ፥ መንገዳቸውን የሚጠመዝዙ አካሄዳቸውንም የሚያጣምሙ ናቸው፥ ከእንግዳይቱ ሴት አንተን ለመታደግ፥ ቃሏን ከምታለዝብ ከማትታወቀው ሴት፥ የወጣትነት ወዳጅዋን የምትተወው ሴት የአምላክዋንም ቃል ኪዳን የምትረሳዋ፥ ቤትዋ ወደ ሞት ያዘነበለ ነው፥ አካሄድዋም ወደ ሙታን ጥላ። ወደ እርሷ የሚገቡ ሁሉ አይመለሱም፥ ወደ ሕይወት ጎዳናም አይደርሱም፥ አንተም በመልካም ሰዎች መንገድ እንድትሄድ የጻድቃንንም ጎዳና እንድትጠብቅ። ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፥ ፍጹማንም በእርሷ ይኖራሉና፥ ክፉዎች ግን ከምድር ይጠፋሉ፥ ዓመፀኞችም ከእርሷ ይነጠቃሉ።