ምሳሌ 17:14-28

ምሳሌ 17:14-28 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)

የጠብ መጀመሪያ ውኃን መድፈን ነው። የጽድቅ መጀመሪያ በነገር መሠልጠንን ይሰጣል፥ የችጋር አበጋዝ ጠብና ክርክር ነው። ኃጥኡን ጻድቅ፥ ጻድቁንም ኃጥእ ብሎ መፍረድ በእግዚአብሔር ዘንድ የረከሰና የተናቀ ነው። ለአላዋቂ ሰው ገንዘብ ለምንድን ነው? አላዋቂ ሰው ጥበብን ገንዘብ ማድረግ አይችልምና፥ ቤቱን የሚያስረዝም ሰው ለራሱ ጥፋትን ይሻል፤ ለመማርም የሚጨንቀው ወደ ክፉ ይወድቃል። ሁልጊዜ ወዳጅ ይኑርህ፥ ወንድሞች በመከራ ጊዜ ጠቃሚዎች ይሆናሉ፥ ስለዚህ ይወለዳሉና። አላዋቂ ሰው አጋና ይመታል፥ ለባልንጀራውም ዋስ እንደሚሆን በራሱ ደስ ይለዋል። ክርክርን የሚወድድ በጠብ ደስ ይለዋል። ጠማማ ልብ ያለው መልካም ነገርን አያገኝም፥ አንደበቱን የሚለዋውጥም በክፉ ላይ ይወድቃል። የሰነፍ ልብ ገንዘብ ላደረጋት ኀዘን ናት፥ አባት ባልተማረ ልጁ ደስ አይለውም፥ ብልህ ልጅ ግን እናቱን ደስ ያሰኛል። ደስ ያላት ልብ ፈውስን ታገኛለች፤ ኀዘንተኛ ሰው ግን አጥንቱን ያደርቃል። መማለጃን በዐመፃ በብብቱ የሚቀበል መንገዶቹን አያቀናም፥ ክፉ ሰውም ከጽድቅ መንገዶች ይርቃል። የብልህ ሰው ፊት ዐዋቂ ነው፤ የአላዋቂ ሰው ዐይኖች ግን በምድር ዳርቻ ናቸው። አላዋቂ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ኀዘን ነው። ጻድቅን ሰው ማዋረድ መልካም አይደለም። በእውነት ለሚፈርዱም መዋሸት መልካም አይደለም። ሻካራ ቃልን ከመናገር የሚከለክል ዐዋቂ ነው፥ ትዕግሥተኛ ሰውም ብልህ ነው። አላዋቂ ጥበብን ቢጠይቅ ጥበብ ይሆነዋል፤ ዝም የሚል ሰውም ጥበበኛን ይመስላል።

ምሳሌ 17:14-28 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

ጠብ መጫር ግድብን እንደ መሸንቈር ነው፤ ስለዚህ ጠብ ከመጫሩ በፊት ከነገር ራቅ። በደለኛውን ማጽደቅ ሆነ፣ ጻድቁን በደለኛ ማድረግ፣ ሁለቱም በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ናቸው። ጥበብን ለማግኘት ፍላጎት ስለሌለው፣ ሞኝ እጅ የገባ ገንዘብ ጥቅሙ ምንድን ነው? ወዳጅ ምን ጊዜም ወዳጅ ነው፤ ወንድምም ለክፉ ቀን ይወለዳል። ልበ ቢስ ሰው ሰው ቃል በመግባት እጅ ይመታል፤ ለወዳጁም ዋስ ይሆናል። ጠብ የሚወድድ ኀጢአትን ይወድዳል፤ በሩን ከፍ አድርጎ የሚሠራም ጥፋትን ይጋብዛል። ጠማማ ልብ ያለው ሰው አይሳካለትም፤ በአንደበቱ የሚቀላምድም መከራ ላይ ይወድቃል። ሞኝ ልጅ መውለድ ሐዘን ያስከትላል፤ የተላላም አባት ደስታ የለውም። ደስተኛ ልብ ጥሩ መድኀኒት ነው፤ የተሰበረ መንፈስ ግን ዐጥንትን ያደርቃል። ክፉ ሰው ፍትሕ ለማዛባት፣ በስውር ጕቦ ይቀበላል። አስተዋይ ሰው ጥበብን ከፊቱ አይለያትም፤ የሞኝ ዐይኖች ግን እስከ ምድር ዳርቻ ይንከራተታሉ። ሞኝ ልጅ በአባቱ ላይ ሐዘን ያስከትላል፤ ለወለደችውም ምሬት ይሆንባታል። ንጹሑን ሰው መቅጣት ተገቢ አይደለም፤ ሹሞችን ስለ ቅንነታቸው መግረፍ መልካም አይደለም። ዐዋቂ ሰው ንግግሩ ቍጥብ ነው፤ አስተዋይም መንፈሱ የረጋ ነው። ቂል እንኳ ዝም ቢል ጠቢብ፣ አንደበቱንም ቢገዛ አስተዋይ ይመስላል።

ምሳሌ 17:14-28 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)

የጥል መነሻ መፍረስ እንደ ጀመረ ግድብ ነው፤ ስለዚህ ጥል ከማስከተሉ በፊት ክርክርን አቁም። በንጹሕ ሰው ላይ መፍረድ፥ ወይም በደለኛውን ንጹሕ ማድረግ ሁለቱም እግዚአብሔር የሚጸየፋቸው ድርጊቶች ናቸው። ሞኝ የተፈጥሮ ማስተዋል ስለሌለው ገንዘቡን ጥበብን ለማግኘት ቢያውል ምንም አይጠቅመውም። ወዳጅ ምን ጊዜም ቢሆን ወዳጁን ይወዳል፤ ወንድም የሚወለደው የወንድሙን ችግር ለመካፈል ነው። ማስተዋል የጐደለው ሰው ለሌላ ሰው ዋስ ይሆናል፤ ራሱንም ተያዥ አድርጎ ይሰጣል። ኃጢአትን የሚወድ ጠብን ይወዳል፤ ከፍ ብሎ እንደ ተሠራ ደጃፍ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሰው ውድቀትን ይጋብዛል። ጠማማ ልብ ያለው አይበለጽግም፤ አንደበቱ አታላይ የሆነ ሰው ችግር ላይ ይወድቃል። የሰነፍ ልጅ አባት ከሐዘንና ከብስጭት በቀር ምንም ደስታ የለውም። ደስተኛነት ለልብ መልካም መድኃኒት ነው፤ የመንፈስ ሐዘንተኛ መሆን ግን አጥንትን ይሰብራል። ክፉ ሰው ፍርድን ለማጣመም፥ በምሥጢር ጉቦ ይቀበላል። አስተዋይ ሰው ወደ ጥበብ ያዞራል፤ የሞኝ ዐይኖች ግን በብዙ አቅጣጫ ይባዝናሉ። ሰነፍ ልጅ አባቱን በሐዘን ላይ ይጥላል፤ በእናቱም ላይ መራራ ጸጸት ያመጣል። ንጹሑን ሰው መቀጫ ማስከፈል፥ ወይም ጨዋውን ሰው ማስገረፍ ተገቢ አይደለም። ንግግሩን የሚቈጥብ ዐዋቂ ነው፤ የረጋ መንፈስ ያለውም ሰው አስተዋይ ነው። ሞኝ ዝም ሲል ጥበበኛ ይመስላል፤ ምንም ሳይናገር ቢቀር እንደ ብልኅ ይቈጠራል።

ምሳሌ 17:14-28 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)

የጠብ መጀመሪያ እንደ ውኃ አፈሳሰስ ነው፥ ስለዚህ ጠብ ሳይበረታ አንተ ክርክርን ተው። ኀጥኡን የሚያጸድቅና በጻድቁ ላይ የሚፈርድ፥ ሁለቱ በጌታ ዘንድ አስጸያፊዎች ናቸው። በሰነፍ እጅ የጥበብ መግዣ ገንዘብ መኖሩ ስለ ምንድነው? ጥበብን ይገዛ ዘንድ አእምሮ የለውምና። ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፥ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል። አእምሮ የጐደለው ሰው አጋና ይመታል፥ በባልንጀራውም ፊት ይዋሳል። ዓመፃን የሚወድድ ክርክርን ይወድዳል፥ ደጁንም ዘለግ የሚያደርግ ውድቀትን ይሻል። ጠማማ ልብ ያለው መልካምን አያገኝም፥ ምላሱንም የሚገለብጥ በክፉ ላይ ይወድቃል። ሰነፍን የሚወልድ ኀዘን ይሆንበታል፥ የደንቆሮ ልጅም አባት ደስ አይለውም። ደስ ያላት ልብ መልካም መድኃኒት ናት፥ ያዘነች ነፍስ ግን አጥንትን ታደርቃለች። ኀጥእ የፍርድን መንገድ ለማጥመም ከብብት መማለጃን ይወስዳል። በአስተዋይ ፊት ጥበብ ትኖራለች፥ የሰነፍ ዐይን ግን በምድር ዳርቻ ነው። ሰነፍ ልጅ ለአባቱ ፀፀት ነው፥ ለወለደችውም ምሬት ነው። ጻድቅን መቅጣት፥ ጨዋ ሰውንም በጻድቅነቱ መምታት መልካም አይደለም። ጥቂት ቃልን የሚናገር አዋቂ ነው፥ መንፈሱም ቀዝቃዛ የሆነ አስተዋይ ነው። ሰነፍ ዝም ቢል ጠቢብ ሆኖ ይቈጠራል፥ ከንፈሩንም የሚቈልፍ፦ ባለ አእምሮ ነው ይባላል።