ምሳሌ 13:16-21
ምሳሌ 13:16-21 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
ብልህ ሁሉ በዕውቀት ይሠራል፤ ሰነፍ ግን ክፋቱን ይገልጣል። ሰነፍ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፤ ብልህ መልእክተኛ ግን ራሱን ያድናል። ትምህርት ድህነትንና ጕስቍልናን ያስወግዳል፤ ተግሣጽን የሚጠብቅ ግን ይከብራል። የደጋግ ሰዎች ምኞት ነፍስን ያድናል፤ የሰነፎች ሥራ ግን ከዕውቀት የራቀ ነው። ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ ከአላዋቂዎች ጋር የሚሄድ ግን አላዋቂ ይሆናል። በደለኞችን ክፉ ነገር ይከተላቸዋል፤ ጻድቃንን ግን መልካም ነገር ያገኛቸዋል።
ምሳሌ 13:16-21 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
አስተዋይ ሰው ሥራውን በዕውቀት ያከናውናል፤ ተላላ ግን ሞኝነቱን ይገልጣል። ክፉ መልእክተኛ መከራ ውስጥ ይገባል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ፈውስን ያመጣል። ተግሣጽን የሚንቅ ወደ ድኽነትና ኀፍረት ይሄዳል፤ ዕርምትን የሚቀበል ሁሉ ግን ይከበራል። ምኞት ስትፈጸም ነፍስን ደስ ታሰኛለች፤ ተላሎች ግን ከክፋት መራቅን ይጸየፋሉ። ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል። መጥፎ ዕድል ኀጢአተኛን ይከታተላል፤ ብልጽግና ግን የጻድቃን ዋጋ ነው።
ምሳሌ 13:16-21 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
አስተዋይ ሰዎች ለሚሠሩት ሥራ አስቀድመው ዕቅድ ያወጣሉ፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን አላዋቂነታቸውን ይገልጣሉ። ክፉ መልእክተኛ ችግርን ያመጣል፤ ታማኝ መልእክተኛ ግን ሰላምን ያስገኛል። ትምህርት የማይወድ ሰው፥ ድኽነትና ውርደት ይገጥመዋል፤ ተግሣጽን የሚቀበል ግን ይከበራል። የተመኙትን ነገር ማግኘት እጅግ ደስ ያሰኛል፤ ማስተዋል የጐደላቸው ሰዎች ግን ከክፉ ነገር መራቅ አይፈልጉም። ከጥበበኞች የሚወዳጅ ጥበበኛ ይሆናል። ማስተዋል ከጐደላቸው ሰዎች ጋር ጓደኛ የሚሆን ግን ይጐዳል። ኃጢአተኞችን በሄዱበት ስፍራ ሁሉ መከራ ይከተላቸዋል፤ ደጋግ ሰዎች ግን የመልካም ሥራቸውን ዋጋ ያገኛሉ።
ምሳሌ 13:16-21 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ብልህ ሁሉ በእውቀት ይሠራል፥ ሰነፍ ግን ስንፍናውን ይገልጣል። መጥፎ መልእክተኛ በክፉ ላይ ይወድቃል፥ የታመነ መልእክተኛ ግን ፈውስ ነው። ድህነትና ነውር ተግሣጽን ቸል ለሚሉ ነው፥ ዘለፋን የሚሰማ ግን ይከብራል። የተፈጸመች ፈቃድ ሰውነትን ደስ ታሰኛለች፥ ሰነፎች ግን ከክፉ መራቅን ይጸየፋሉ። ከጠቢባን ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፥ የሰነፎች ባልንጀራ ግን ክፉ መከራን ይቀበላል። ክፉ ነገር ኃጢአተኞችን ያሳድዳቸዋል፥ ጻድቃን ግን መልካሙን ዋጋ ይቀበላሉ።