ዘኍል 35:9-34
ዘኍል 35:9-34 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እነሆ፥ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን ትሻገራላችሁ፤ ባላማወቅ ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንተ ለዩ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስከሚቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞችን ትለያላችሁ፤ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞችን ትለያላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞችም ይሆናሉ። ባለማወቅ ነፍስ የገደለ ሁሉ ይሸሽባቸው ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች፥ በመካከላቸውም ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። “በብረት መሣሪያ ቢመታው፥ ቢሞትም ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው፥ የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣሪያ ቢመታው፥ የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኘው ጊዜ ይግደለው። ጥል ቢጣላው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ቢሞትም፥ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ባለ ደሙ ወይም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። “ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥ ማኅበሩ በመቺውና በባለ ደሙ መካከል ፍርድን እንደዚህ ይፍረዱ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከባለ ደሙ እጅ ያድኑታል፤ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛው ከተማ ይመልሱታል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥ ባለ ደሙም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ባለ ደሙም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ በደል የለበትም፤ ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ታላቁ ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። “እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዐትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች ቃል ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። ታላቁ ካህን እስኪሞት ወደ ምድሩ ትመልሱት ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው ዋጋ አትቀበሉ። ምድርን የሚያረክሳት ደም ነውና የምትኖሩባትን ምድር በነፍስ ግድያ አታርክሷት። ምድሪቱም በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። እናንተ በውስጥዋ የምትኖሩባትን፥ እኔም ከእናንተ ጋር የማድርባትን ምድር አታርክሱኣት፤ በእስራኤል ልጆች መካከል የማድር እኔ እግዚአብሔር ነኝና።”
ዘኍል 35:9-34 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “እስራኤላውያንን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ወደ ከነዓን ለመግባት ዮርዳኖስን በምትሻገሩበት ጊዜ፣ ሳያስበው ሰው የገደለ ሰው ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ከተሞች እንዲሆኑ መማጸኛ ከተሞችን ምረጡ። እነዚህም፣ ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ዘንድ ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት እንዳይሞት ከደም ተበቃዩ የሚሸሽባቸው የመማጸኛ ከተሞች ይሆናሉ። እነዚህ ለሌዋውያኑ የምትሰጧቸው ስድስት ከተሞች መማጸኛ ከተሞቻችሁ ይሆናሉ። ስለዚህ ከዮርዳኖስ ወዲህ ሦስቱን እንዲሁም በከነዓን ሦስቱን የመማጸኛ ከተሞች አድርጋችሁ ስጡ። እነዚህም ስድስት ከተሞች ሳያስበው ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው እንዲሸሽባቸው ለእስራኤላውያን፣ ለመጻተኞችና በመካከላቸው ለሚኖር ለማንኛውም ሕዝብ የመማጸኛ ቦታዎች ይሆናሉ። “ ‘አንድ ሰው ሌላውን እንዲሞት በብረት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ድንጋይ በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። ወይም አንድ ሰው መግደል የሚችል ዕንጨት በእጁ ቢይዝና ሌላውን ሰው እንዲሞት ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ በሞትም ይቀጣል። ደም መላሹም ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው፤ ባገኘውም ጊዜ ይግደለው። አንድ ሰው አስቦበት ሌላውን በክፋት ገፍትሮ ቢጥለው ወይም እንዲሞት ሆን ብሎ አንዳች ነገር ቢወረውርበት ወይም ደግሞ በጥላቻ ተነሣሥቶ በእጁ ቢመታውና ቢሞት፣ ያ ሰው በሞት ይቀጣል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም መላሹም ገዳዩን ባገኘው ጊዜ ይግደለው። “ ‘ነገር ግን በጥላቻ ሳይሆን እንዲያው በድንገት አንዱ ሌላውን ገፍትሮ ቢጥለው ወይም ሳያስበው አንዳች ነገር ቢወረውርበት ወይም መግደል የሚችል ድንጋይ ሳያይ ጥሎበት ቢሞት፣ ጠላቱ ስላልሆነና ሊጐዳውም አስቦ ያላደረገው ስለሆነ፣ ማኅበሩ በዚህ ሰውና በደመኛው መካከል በእነዚህ ደንቦች መሠረት ይፍረድ። ማኅበሩም በነፍሰ ገዳይነት የተከሰሰውን ሰው ከደመኛው እጅ በማስጣል ወደ ሸሸበት ወደ መማጸኛው ከተማ ይመልሰው፤ የተቀደሰ ዘይት የተቀባው ሊቀ ካህን እስኪሞትም ድረስ በዚያ ይቈይ። “ ‘ሆኖም ተከሳሹ ሰው ሸሽቶ ከተጠጋበት መማጸኛ ከተማ ክልል ከወጣ፣ ደም ተበቃዩም ከከተማው ውጭ ካገኘው፣ ተከሳሹን ሊገድለው ይችላል፤ በነፍሰ ገዳይነትም አይጠየቅም። ተከሳሹም ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በመማጸኛው ከተማ ይቈይ፤ ወደ ገዛ ርስቱ መመለስ የሚችለው ከሊቀ ካህናቱ ሞት በኋላ ብቻ ነው። “ ‘እንግዲህ በየትኛውም በምትኖሩበት ስፍራ፣ በሚመጡት ትውልዶች ሁሉ የምትፈጽሟቸው ሕጋዊ ግዴታዎቻችሁ እነዚህ ናቸው። “ ‘ሰው የገደለ ማንኛውም ሰው በሞት የሚቀጣው ምስክሮች ሲመሰክሩበት ብቻ ነው፤ ይሁን እንጂ ማንም ሰው በአንድ ምስክር ብቻ በሞት አይቀጣም። “ ‘በሞት መቀጣት ስላለበት ሰው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ ፈጽሞ መሞት አለበት። “ ‘ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ ስለ ገባ ስለ ማንኛውም ሰው የደም ዋጋ በመቀበል ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ አገሩ ተመልሶ ሄዶ እዚያ እንዲኖር አታድርጉ። “ ‘ደም ምድሪቱን ስለሚያረክሳት፣ ደም ለፈሰሰባትም ምድር ስርየት ሊደረግላት የሚችለው በሌላ ሳይሆን በዚያው ደሙን ባፈሰሰው ሰው ደም ብቻ በመሆኑ፣ የምትኖሩባትን ምድር በደም አታርከሷት፤ የምትኖሩባትን፣ እኔም የማድርባትን ምድር አታርክሷት እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእስራኤላውያን መካከል እኖራለሁና።’ ”
ዘኍል 35:9-34 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ ይሸሽ ዘንድ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ከተሞችን ለእናንት ለዩ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹም ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። በስሕተት ነፍስ የገደለ ይሸሽበት ዘንድ እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውም በሚሞትበት በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኛው ጊዜ ይግደለው። እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ቢደፋው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ቢደፋው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰው የሚሞትበትን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ያደርግበት ዘንድ ባይሻ፥ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን እንደዚሁ ይፍረድ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ዘይትም የተቀባው ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ቢወጣ፥ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ዳርቻ ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ ዋነኛው ካህን እስኪሞት ድረሰ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ዋነኛው ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። ነፍሰ ገዳይ ሁሉ በምስክሮች አፍ ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። ዋነኛው ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ ይመለስ ዘንድ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። እኔ እግዚአብሔር በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።
ዘኍል 35:9-34 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ከነዓን ምድር ስትገቡ፥ አንድ ሰው ባለማወቅ ተሳስቶ ሰው ቢገድል አምልጦ የሚደበቅበት የመማጠኛ ከተሞችን ምረጥ። በዚያም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከሚፈልግ ከሟቹ ዘመድ ሊሰወር ይችላል፤ በግድያ ወንጀል የተከሰሰ ሰው ለፍርድ ሳይቀርብ መገደል የለበትም፤ ስድስት ከተሞችን ምረጡ፤ ከእነርሱም ሦስቱ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ፥ ሦስቱ ደግሞ በከነዓን ምድር ይሁኑ፤ እነርሱም ለእስራኤላውያንና ለጊዜውም ሆነ ለዘለቄታው በእስራኤል ለሚኖሩ መጻተኞች የመማጠኛ ከተሞች ይሆናሉ፤ ባለማወቅ ተሳስቶ ሰው የሚገድል ማንኛውም ግለሰብ ከእነርሱ ወደ አንዱ አምልጦ መጠጋት ይችላል። “አንድ ሰው ሌላውን ሰው በብረት መሣሪያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ያ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል። አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሊገድል በሚችል ድንጋይ ቢመታውና ያ የተመታው ሰው ቢሞት ያ የመታው ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል፤ አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሊገድል በሚችል የእንጨት መሣሪያ መትቶ ቢገድለው ያ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል። የሟቹ ቅርብ ዘመድ ነፍሰ ገዳዩን የመግደል መብት ይኖረዋል፤ ስለዚህ ባገኘው ጊዜ ሊገድለው ይችላል። “አንድ ሰው ሌላውን ሰው በጥላቻ ቢገፋው ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢወረውርበትና ይህ አድራጎቱ ሞትን ቢያስከትል፥ ወይም በጠላትነት ተነሣሥቶ በቡጢ በመምታት ቢገድለው የግድያ ወንጀል ስለ ፈጸመ መገደል አለበት፤ የሟች ቅርብ ዘመድ ነፍሰ ገዳዩን የመግደል መብት ይኖረዋል፤ ስለዚህ ባገኘው ጊዜ ሊገድለው ይችላል። “ነገር ግን አንድ ሰው ገፍትሮ በመጣልም ሆነ አንዳች ነገር በላዩ በመወርወር ሌላ ሰው የሚገድለው ከጥላቻ የተነሣ ሳይሆን በድንገት ተሳስቶ ከሆነ፤ ወይም ጠላትነት ሳይኖርና ሰውን ለመጒዳት ታስቦ ሳይሆን ሞትን የሚያስከትል ድንጋይ ወርውሮ ሳይታሰብ በሌላ ሰው ላይ ቢያርፍና ሞትን ቢያስከትል፥ እንዲህ ያለው ሁኔታ በሚፈጸምበት ጊዜ ማኅበሩ በገዳዩና በተበቃዩ መካከል ፍርድ የሚሰጠው በሚከተለው ሥርዓት መሠረት ነው። ማኅበሩ በግድያ ወንጀል የተከሰሰውን ሰው ከተበቃይ እጅ በመታደግ አምልጦ ወደነበረበት ወደ መማጠኛ ከተማዋ መመለስ አለበት፤ በዘመኑ ሊቀ ካህናት የሆነው ሰው እስከሚሞትበት ድረስ እዚያው መቈየት ይኖርበታል። በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ሰው አምልጦ ከመማጸኛው ከተማ ለቆ ከሄደ፥ የሟች ዘመድ አግኝቶ ከገደለው የዚህ ዐይነቱ የበቀል እርምጃ በነፍሰ ገዳይነት አያስጠይቅም። በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ሰው ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በዚያው በመማጸኛ ከተማ መቈየት አለበት፤ ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን ወደ ቤቱ መመለስ ይችላል፤ ይህ ሕግና ሥርዓት በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለእናንተና ለዘሮቻችሁ መመሪያ ይሆናል። “በግድያ ወንጀል የተከሰሰ ማንኛውም ሰው የሞት ፍርድ ሊበየንበት የሚችለው ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች የመሰከሩበት እንደ ሆነ ነው፤ የአንድ ሰው ምስክርነት ግን ለግድያ ወንጀል የተከሰሰውን ሰው ሊያስጠይቀው አይችልም። ማንኛውም ነፍሰ ገዳይ በሞት መቀጣት አለበት፤ ገንዘብ በመክፈል ከዚህ ቅጣት ሊያመልጥ አይችልም። አንድ ሰው ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ ቢያመልጥ ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ ቤቱ መመለስ ይችል ዘንድ ገንዘብ እንዲከፍል አትፍቀዱለት። ይህን ብታደርጉ የምትኖሩበትን ምድር ታረክሳላችሁ፤ የነፍስ ግድያ ወንጀል ምድሪቱን ያረክሳል፤ ስለዚህ የነፍሰ ገዳዩ ደም ካልፈሰሰ በቀር ምድሪቱን ከደም ለማንጻት የሚፈጸም ሌላ ሥርዓት የለም። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ስለ ሆንኩና በእናንተ በእስራኤል ሕዝብም መካከል ስለምኖር የእኔ መኖሪያ የሆነውንና እናንተ የምትኖሩበትን ምድር አታርክሱ።”
ዘኍል 35:9-34 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ለእነርሱ ተናገር፦ ወደ ከነዓን ምድር ዮርዳኖስን በተሻገራችሁ ጊዜ፥ በስሕተት ነፍስ የገደለ ወደዚያ እንዲሸሽ የመማፀኛ ከተሞች እንዲሆኑላችሁ ለእናንተ ከተሞችን ትመርጣላችሁ። ነፍሰ ገዳዩ በማኅበሩ ፊት ለፍርድ እስኪቆም ድረስ እንዳይሞት፥ ከተሞቹ ከደም ተበቃይ የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። የምትሰጡአቸውም ስድስቱ ከተሞች የመማፀኛ ከተሞች ይሁኑላችሁ። በዮርዳኖስ ማዶ ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፥ በከነዓንም ምድር ሦስት ከተሞች ትሰጣላችሁ፤ የመማፀኛ ከተሞች ይሆናሉ። በስሕተት ነፍስ የገደለ ሁሉ እንዲሸሽበት እነዚህ ስድስት ከተሞች ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸው ለሚቀመጡ እንግዶችና መጻተኞች መማፀኛ ይሆናሉ። “ማንኛውም ሰው ሌላውን ሰው በብረት መሣርያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው ድንጋይ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ሰውንም ለሞት በሚያበቃው በእጁ ባለው በእንጨት መሣርያ ቢመታው የተመታውም ቢሞት፥ እርሱ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ፈጽሞ ይገደል። ደም ተበቃዩ ራሱ ነፍሰ ገዳዩን ይግደል፤ ባገኛው ጊዜ ይግደለው። እስኪሞት ድረስ በጥላቻ ገፍትሮ ቢጥለው፥ ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም በጥላቻ እስኪሞት ድረስ በእጁ ቢመታው፥ የመታው ፈጽሞ ይገደል፤ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ደም ተበቃዩ ባገኘው ጊዜ ነፍሰ ገዳዩን ይግደለው። “ነገር ግን ያለ ጥላቻ ድንገት ገፍትሮ ቢጥለው፥ ሳይሸምቅም አንዳች ነገር ቢጥልበት፥ ወይም ሳያየው እስኪሞት ድረስ ሰውን ለሞት የሚያበቃውን ድንጋይ ቢጥልበት፥ ጠላቱም ባይሆን፥ ክፉም ሊያደርግበት ባይሻ፥ ማኅበሩ በመቺውና በደም ተባቃዩ መካከል ፍርድን በዚህ መሠረት ይፍረድ፤ ማኅበሩም ነፍሰ ገዳዩን ከደም ተበቃዩ እጅ ያድነዋል፥ ማኅበሩም ወደ ሸሸበት ወደ መማፀኛ ከተማ ይመልሰዋል፤ በቅዱስ ቅባትም የተቀባው ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በዚያ ይቀመጣል። ነፍሰ ገዳዩ ግን ከሸሸበት ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ቢወጣ፥ ደም ተበቃዩም ከመማፀኛው ከተማ ድንበር ውጭ ቢያገኘው፥ ደም ተበቃዩም ነፍሰ ገዳዩን ቢገድለው፥ የደም ዕዳ አይሆንበትም፤ ታላቁ ካህን እስኪሞት ድረስ በመማፀኛው ከተማ ውስጥ መቀመጥ ይገባው ነበርና። ታላቁ ካህን ከሞተ በኋላ ግን ነፍሰ ገዳዩ ወደ ርስቱ ምድር ይመለሳል። “እነዚህም ነገሮች ለልጅ ልጃችሁ በማደሪያችሁ ሁሉ ሥርዓትና ፍርድ ይሁኑላችሁ። ነፍሰ ገዳይ ሁሉ ምስክሮች በሰሚጡት ቃል ይገደላል፤ በአንድ ምስክር ግን ማናቸውንም ሰው መግደል አይገባም። ሞት የተፈረደበትን ነፍሰ ገዳዩንም ለማዳን የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ፤ እርሱ ፈጽሞ ይገደል። ታላቁ ካህን ሳይሞት ወደ ምድሩ እንዲመለስ ወደ መማፀኛው ከተማ ከሸሸው ሰው የነፍስ ዋጋ አትቀበሉ። ደም ምድሪቱን ያረክሳታልና የምትኖሩባትን ምድር አታርክሱአት፤ በደም አፍሳሹ ደም ካልሆነ በቀር ምድሪቱ ከፈሰሰባት ደም አትነጻም። እኔ ጌታ በእስራኤል ልጆች መካከል አድራለሁና የምትኖሩባትን በመካከልዋም የማድርባትን ምድር አታርክሱአት።”