ዘኍል 3:40-51
ዘኍል 3:40-51 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
እግዚአብሔርም ሙሴን፥ “የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን ቍጠር፤ ቍጥራቸውንም በየስማቸው ውሰድ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር አድርጋቸው” አለው። ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ። ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ በየስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሃያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝና። በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ዲድርክም ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ዲድርክም ብዛት ትወስዳለህ፤ ዲድርክም ሃያ አቦሊ ነው። ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣቸዋለህ።” ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ። ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ዲድርክም እንደ መቅደሱ ዲድርክም ሚዛን ወሰደ። እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
ዘኍል 3:40-51 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኵር ሆነው የተወለዱትን፣ አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን እስራኤላውያን ወንዶች ሁሉ ቍጠር፤ ዝርዝራቸውንም ያዝ። በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በኵር በሆኑት በእስራኤላውያን ከብቶች ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን ከብቶች ለእኔ አድርጋቸው፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።” ስለዚህ ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት የእስራኤላውያንን በኵር ሁሉ ቈጠረ፤ አንድ ወርና ከዚያ በላይ ሆኗቸው በየስማቸው የተመዘገቡት ወንድ በኵሮች ሁሉ ብዛታቸው ሃያ ሁለት ሺሕ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር። ደግሞም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በእስራኤላውያን በኵሮች ምትክ ሌዋውያኑን፣ በከብቶቻቸውም ምትክ የሌዋውያኑን ከብቶች ውሰድ፤ ሌዋውያኑም የእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ። ቍጥራቸው ከሌዋውያን ቍጥር በሁለት መቶ ሰባ ሦስት በልጦ የተገኘውን እስራኤላውያን በኵሮች ለመዋጀት፣ ለእያንዳንዱ በኵር ክብደቱ ባለ ሃያ አቦሊ በሆነው በቤተ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ልክ አምስት አምስት ሰቅል ተቀበል፤ የተረፉትንም እስራኤላውያን ለመዋጀት ገንዘቡን ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” ስለዚህ ሙሴ በሌዋውያኑ ተዋጅተው ቍጥራቸው ትርፍ ከሆነው በኵሮች ላይ የመዋጃውን ገንዘብ ተቀበለ፤ ከእስራኤላውያን በኵሮች ላይ በቤተ መቅደሱ ሰቅል ልክ አንድ ሺሕ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል ሰበሰበ። ሙሴም በእግዚአብሔር (ያህዌ) ቃል በታዘዘው መሠረት የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጣቸው።
ዘኍል 3:40-51 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
እግዚአብሔርም ሙሴን፦ የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው። ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ። ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ። በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ። ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ። ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ። እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
ዘኍል 3:40-51 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኲር ሆነው የተወለዱትን የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያም በላይ የሆነውን ቈጥረህ በየስማቸው መዝግብ፤ በእስራኤል የበኲር ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በእስራኤላውያን የእንስሶች በኲር ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን እንስሶች ውሰድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከእስራኤላውያን መካከል በኲር ሆኖ የተወለደውን ሁሉ ቈጠረ። ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ሁሉ በስማቸው ዝርዝር መሠረት ኻያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር። እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “እንግዲህ በኲር ሆነው በሚወለዱት እስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ምትክ ሌዋውያንን ለእኔ ለይልኝ፤ እንዲሁም በኲር ሆነው በሚወለዱት የእስራኤላውያን እንስሶች ምትክ የሌዋውያንን እንስሳት ለእኔ የተለዩ እንዲሆኑ አድርግ። በኲር ሆነው የተወለዱት የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ብዛት፥ ከሌዋውያን ብዛት በሁለት መቶ ሰባ ሦስት ስለሚበልጥ እነዚህን ትርፍ የሆኑትን ወንዶች ልጆች በገንዘብ መዋጀት ይኖርብሃል። ለያንዳንዱ መዋጃ በመቅደሱ ሚዛን መሠረት አምስት ሰቅል የሚመዝን ብር ትወስዳለህ፤ አንዱ ሰቅል ኻያ ጌራ ነው (ጌራ 0.6 ግራም ነው)። ይህንንም የመዋጃ ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት የተረፉት ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ሰዎች የተሰበሰበውን የመዋጃ ገንዘብ ተቀበለ። ከእስራኤላውያን በኲሮች በመቅደሱ ሚዛን መሠረት ገንዘቡን አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሥልሳ አምስት ሰቅል ብር ወሰደ። እግዚአብሔር ባዘዘው ቃል መሠረት ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።
ዘኍል 3:40-51 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ጌታም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእስራኤልን ልጆች የወንድ በኩር ሁሉ ቁጠር፤ ዕድሜቸው አንድ ወር የሞላቸውንና ከዚያም በላይ ያሉትን በየስማቸው ቈጥረህ ቁጥሩን ውሰድ፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኩር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ትወስዳለህ፥ እኔ ጌታ ነኝ።” ሙሴም ጌታ እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኩር ሁሉ ቈጠረ። ከእነርሱም የተቈጠሩ የወንድ በኩር ሁሉ እንደየስማቸው ቍጥር፥ ዕድሜው አንድ ወር የሞላውና ከዚያም በላይ ያለው የተቈጠሩት ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ። ጌታም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ “ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኩር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም የእኔ ናቸው፤ እኔ ጌታ ነኝ። ከሌዋውያን ወንዶች ቍጥር በላይ የሆኑትን ሁለት መቶ ሰባ ሦስት የእስራኤል ልጆች በኵራትን ለመዋጀት፥ ለእያንዳንዱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው። ከቍጥር በላይ የሆኑት የተዋጁበትን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት ቍጥር በላይ ከሆኑት ዘንድ የመዋጃውን ገንዘብ ወሰደ። ከእስራኤል ልጆች በኵራት አንድ ሺህ ሦስት መቶ ስልሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ገንዘቡን ወሰደ። ጌታም ሙሴን እንዳዘዘው፥ እንደ ጌታ ቃል፥ ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።